በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሴቶች ደህንነት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የሴቶች ደህንነት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ለአካለ መጠን የደረሱም ሆኑ ያልደረሱ ሴቶች ጥቃት ይፈጸምባቸዋል። አንቺ ከእነዚህ መካከል አንዷ ነሽ? አምላክ የአንቺ ደህንነት ምን ያህል እንደሚያሳስበውና በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን በደል ለማስቆም ምን እርምጃ እንደሚወስድ እንድታነብቢ እንጋብዝሻለን።

 “ልጅ ሳለሁ ወንድሜ በየቀኑ ይደበድበኝና ይሰድበኝ ነበር። ትዳር ከመሠረትኩ በኋላ አማቴ ብዙ በደል ታደርስብኝ ጀመር። የባለቤቴ ወላጆች እንደ ገረድ ነበር የሚቆጥሩኝ። ራሴን የማጥፋት ሐሳብ በተደጋጋሚ ወደ አእምሮዬ ይመጣ ነበር።”—መዱ፣ a ሕንድ።

 “በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በዓለም ዙሪያ የተስፋፋ ችግር ነው” በማለት የዓለም የጤና ድርጅት አረጋግጧል። ይህ ድርጅት ሪፖርት እንዳደረገው፣ ከሦስት ሴቶች አንዷ በሆነ የዕድሜዋ ክፍል አካላዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት እንደሚፈጸምባት ይገመታል።

 እንዲህ ያለ ጥቃት አጋጥሞሽ የሚያውቅ ከሆነ የትም ቦታ ስትሄጂ የደህንነት ስሜት ላይሰማሽ ይችላል፤ ሰዎች ሊያንቋሽሹኝ አሊያም አካላዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት ሊፈጽሙብኝ ይችላሉ የሚል ስጋት ያድርብሽ ይሆናል። እንዲህ ያለው ፆታ ተኮር ጥቃት ሰለባ መሆንሽ አብዛኞቹ ሰዎች ለሴቶች ምንም ቦታ እንደማይሰጡ እንድታስቢ ሊያደርግሽ ይችላል። ሆኖም ከአምላክ ጋር በተያያዘስ ምን ማለት ይቻላል? በእርግጥ አምላክ ለሴቶች ያስባል?

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሴቶች ደህንነት እንደሚያሳስበው ያሳያል

አምላክ ለሴቶች ምን አመለካከት አለው?

 ጥቅስ፦ “[አምላክ] ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።”—ዘፍጥረት 1:27

 ትርጉሙ፦ አምላክ የፈጠረው ወንዶችን ብቻ ሳይሆን ሴቶችንም ነው። ሁለቱንም አክብሮት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አድርጎ ይቆጥራቸዋል። በተጨማሪም አንድ ባል “ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም [እንዲወድ]” አምላክ ይጠብቅበታል፤ ስለዚህ አንድ ባል ኃይለ ቃል በመናገር ወይም በማስፈራራት ሚስቱን ለመቆጣጠር ሊሞክር አይገባም ማለት ነው። (ኤፌሶን 5:33፤ ቆላስይስ 3:19) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አምላክ የሴቶች ደህንነት ያሳስበዋል።

 “ልጅ ሳለሁ በዘመዶቼ ፆታዊ ጥቃት ተፈጽሞብኛል። በ17 ዓመቴ ደግሞ አሠሪዬ ከእሱ ጋር የፆታ ግንኙነት ካልፈጸምኩ ከሥራ እንደሚያባርረኝ ዛተብኝ። አዋቂ ከሆንኩ በኋላም ባለቤቴ፣ ወላጆቼና ጎረቤቶቼ ያንቋሽሹኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ስለ ፈጣሪያችን ስለ ይሖዋ b ተማርኩ። እሱ ለሴቶች አክብሮት አለው። ይህን ማወቄ ይሖዋ እንደሚወደኝና በእሱ ዘንድ ዋጋ እንዳለኝ ማረጋገጫ ሆኖልኛል።”—ማሪያ፣ አርጀንቲና።

ከደረሰብሽ ቁስል ለማገገም ምን ሊረዳሽ ይችላል?

 ጥቅስ፦ “ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ ጓደኛ አለ።”—ምሳሌ 18:24

 ትርጉሙ፦ እውነተኛ ወዳጅ የብርታት ምንጭ ሊሆንልሽ ይችላል። ስለዚህ ከቻልሽ የሚሰማሽን ስሜት ለምታምኚው ሰው ተናገሪ።

 “ለ20 ዓመት ያህል ለማንም በፆታ እንደተነወርኩ አልተናገርኩም። ይህም ደስታ እንዳጣ እንዲሁም ጭንቀትና ድባቴ ውስጥ እንድገባ አድርጎኝ ነበር። በመጨረሻ ግን ጆሮ ሰጥቶ ሊያዳምጠኝ ፈቃደኛ ለነበረ ሰው የደረሰብኝን ነገር ተናገርኩ፤ ከዚያ በኋላ ትልቅ እፎይታ አገኘሁ።”—ኢሊፍ፣ ቱርክዬ።

 ጥቅስ፦ “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥሮስ 5:7

 ትርጉሙ፦ ስትጸልዪ አምላክ በቁም ነገር ያዳምጥሻል። (መዝሙር 55:22፤ 65:2) ስለሚያስብልሽ ምን ያህል ውድ ዋጋ እንዳለሽ እንድትገነዘቢ ይረዳሻል።

 “ስለ ይሖዋ እየተማርኩ ስሄድ፣ ከነበረብኝ ከባድ ቁስል ቀስ በቀስ ማገገም ጀመርኩ። አሁን የሚሰማኝን ሁሉ በጸሎት አማካኝነት ለአምላክ ልነግረው እችላለሁ። እሱ ስሜቴን በደንብ እንደሚረዳ ወዳጅ ሆኖልኛል።”—አና፣ ቤሊዝ።

አምላክ በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን በደል የሚያስወግድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

 ጥቅስ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ . . . በምድር ላይ ያለ ሟች የሆነ ሰው ከእንግዲህ እንዳያሸብራቸው፣ አባት ለሌለው ልጅና ለተደቆሱ ሰዎች ፍትሕ ታሰፍናለህ።”—መዝሙር 10:17, 18

 ትርጉሙ፦ አምላክ በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጭካኔና በደል ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ኢፍትሐዊ ድርጊት በቅርቡ ያስወግዳል።

 “አምላክ ለአካለ መጠን በደረሱም ሆነ ባልደረሱ ሴቶች ላይ የሚፈጸመውን በደል በቅርቡ እንደሚያስወግድ ማወቄ ለእኔ ልክ ሕመምን እንደሚያስታግስ መድኃኒት ሆኖልኛል። የአእምሮ ሰላም ሰጥቶኛል።”—ሮበርታ፣ ሜክሲኮ።

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ተስፋ እንደሚሰጥ፣ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት መጣል የምንችለው ለምን እንደሆነና የይሖዋ ምሥክሮች በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው ሰዎችን እየረዱ ያሉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ ትፈልጊያለሽ? የይሖዋ ምሥክሮች ያለምንም ክፍያ መጥተው እንዲያነጋግሩሽ መጠየቅ ትችያለሽ።

 ጽሑፉን አውርዶ ለማተም

a ስሞቹ ተቀይረዋል።

b ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:​18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።