በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ራስን መግዛትን ለልጆች ማስተማር

ራስን መግዛትን ለልጆች ማስተማር

ተፈታታኙ ነገር

የስድስት ዓመት ልጃችሁ ራስን መቆጣጠር የሚባል ነገር ጨርሶ አያውቅም። አንድ የሚፈልገው ነገር ካየ አሁኑኑ ማግኘት ይፈልጋል። በሚናደድበት ጊዜ በቁጣ ሊናገር ይችላል። እንዲህ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል፦ ‘ይሄ የልጆች ሁሉ አመል ነው? ሲያድግ ይተወው ይሆን? ወይስ ራሱን እንዲገዛ ከአሁኑ ባስተምረው ይሻላል?’ *

ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

በዘመናችን ያለው ባሕል ራስን መግዛትን አያበረታታም። ዶክተር ዴቪድ ዎልሽ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “እንደፈለጉ መሆንን በሚያበረታታው ባሕላችን አዋቂዎችም ሆንን ልጆች የፈለግነውን እንድናደርግ የሚያነሳሳ መልእክት ሁልጊዜ ይዥጎደጎድብናል። በቅን ልቦና ተነሳስተው ምክር የሚለግሱንም ሆኑ ለገንዘብ ሲሉ የማይረባ ምክር የሚሰጡን ሰዎች ምንጊዜም ስሜታችንን ማስተናገድ እንዳለብን ሲናገሩ እንሰማለን።” *

ራስን መግዛትን በለጋ ዕድሜያቸው ማስተማር አስፈላጊ ነው። ለረጅም ዓመታት በዘለቀ አንድ ጥናት ላይ፣ ተመራማሪዎች አራት ዓመት ለሆናቸው ልጆች ከረሜላ ሰጧቸው፤ ከዚያም ከረሜላውን ወዲያውኑ መብላት እንደሚችሉ፣ ሳይበሉ ትንሽ ከቆዩ ግን ላሳዩት ትዕግሥት ሽልማት የሚሆን ሌላ ከረሜላ እንደሚሰጣቸው ነገሯቸው። የአራት ዓመት ልጆች እያሉ የራስን መግዛት ባሕርይ አሳይተው የነበሩ ልጆች፣ አድገው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ከሌሎች ጋር ተግባብቶ በመኖር እንዲሁም በትምህርት ከእኩዮቻቸው የተሻሉ ሆነው የተገኙ ሲሆን በሳል አስተሳሰብ እንዳላቸውም ታይቷል።

ራስን መግዛትን አለማስተማር ከባድ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። አንድ ልጅ በሕይወቱ በሚያጋጥሙት ነገሮች ሳቢያ የአእምሮው ነርቭ የሚሠራበት መንገድ ሊለወጥ እንደሚችል ተመራማሪዎች ያምናሉ። ዶክተር ዳን ኪንድለን ይህ ምን ማለት እንደሆነ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ልጆቻችንን ካሞላቀቅናቸው እንዲሁም ተራቸው እስኪደርስ ድረስ መጠበቅን፣ ደስታ ወዳድ አለመሆንንና ፈተና መቋቋምን ካላስተማርናቸው ጥሩ ባሕርያትን እንዲያፈሩ የሚረዷቸው የነርቭ ለውጦች ላይከሰቱ ይችላሉ።” *

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ምሳሌ ሁኑ። ራስን በመግዛት ረገድ እናንተ እንዴት ናችሁ? የትራፊክ መጨናነቅ ባለበት ትዕግሥት አጥታችሁ ስትቆጡ፣ ዕቃ ለመግዛት ሄዳችሁ ጣልቃ ስትገቡ ወይም ሌሎች ሳይጨርሱ እናንተ ማውራት ስትጀምሩ ልጃችሁ አይቷችሁ ያውቃል? “ልጆቻችን ራስን መግዛትን እንዲያዳብሩ መርዳት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ይህን ባሕርይ እኛ ራሳችን ማንጸባረቃችን ነው” በማለት ኪንድለን ጽፈዋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ሮም 12:9

ለልጃችሁ የሚያስከትልበትን መዘዝ አስተምሩት። የልጃችሁን ዕድሜ ግምት ውስጥ በማስገባት ራሱን መቆጣጠሩ ጥቅሞች እንዳሉትና ለፍላጎቱ መሸነፉ ግን ጉዳት እንደሚያስከትልበት እንዲገነዘብ እርዱት። ለምሳሌ ያህል፣ ልጃችሁ አንድ ልጅ ተገቢ ያልሆነ ነገር ፈጽሞበት በሚናደድበት ጊዜ ቆም ብሎ ራሱን እንደሚከተለው ብሎ እንዲጠይቅ እርዱት፦ ‘መበቀል ይጠቅማል ወይስ ይጎዳል? ሁኔታውን መያዝ የምችልበት የተሻለ መንገድ ይኖራል? ምናልባት ከ1 እስከ 10 መቁጠር ንዴቱ እንዲበርድልኝ ይረዳኝ ይሆን? ካናደደኝ ልጅ ዞር ማለቴ የተሻለ ይሆን?’—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ገላትያ 6:7

ማበረታቻ ስጡት። ልጃችሁ የራስን መግዛትን ባሕርይ ሲያሳይ አመስግኑት። ስሜቱን መቆጣጠሩ ሁልጊዜ ቀላል እንደማይሆንና ራሱን መግዛቱ ግን የጥንካሬ ምልክት እንደሆነ ንገሩት! መጽሐፍ ቅዱስ “ስሜቱን መቆጣጠር የማይችል ሰው ቅጥር እንደሌላት የፈረሰች ከተማ ነው” ይላል። (ምሳሌ 25:28) በአንጻሩ ደግሞ “ቶሎ የማይቆጣ ሰው ከኃያል ሰው” ይሻላል።—ምሳሌ 16:32

ልምምድ አድርጉ። “አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?” አሊያም “ጥሩ ምርጫ፣ መጥፎ ምርጫ” ወይም ሌላ ተመሳሳይ ጨዋታ ፈጥራችሁ ልጃችሁ አንድን ገጸ ባሕርይ ወክሎ እንዲጫወት አድርጉ። ሊያጋጥሙ በሚችሉ ሁኔታዎችና በሚሰጡ ምላሾች ላይ ተወያዩ፤ እንዲሁም የትኛው “ጥሩ” የትኛው ደግሞ “መጥፎ” እንደሆነ ግለጹ። የተለያዩ ዘዴዎችን ፍጠሩ፦ እንዲህ ያለውን ጨዋታ አስደሳችና ትምህርት ሰጪ ለማድረግ በአሻንጉሊቶች፣ በሥዕሎች ወይም በሌላ ዘዴ መጠቀም ትችላላችሁ። ግባችሁ ራስን መግዛት፣ በስሜት ከመነዳት የተሻለ እንደሆነ ልጃችሁ እንዲገነዘብ መርዳት ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 29:11

ታጋሽ ሁኑ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝነት በልጅ ልብ ውስጥ ታስሯል” ይላል። (ምሳሌ 22:15) በመሆኑም ልጃችሁ በአንድ ጀምበር የራስን መግዛት ባሕርይን እንዲያዳብር አትጠብቁ። ቲች ዩር ችልድረን ዌል የተባለው መጽሐፍ “ይህ አንዴ መሻሻል የሚታይበት፣ በሌላ ጊዜ በድክመቱ የሚሸነፍበት ከዚያ ደግሞ ተጨማሪ መሻሻል የሚያደርግበት ረጅምና አዝጋሚ ሂደት ነው” ይላል። ይሁን እንጂ የሚደረገው ጥረት አያስቆጭም። መጽሐፉ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ራሱን መቆጣጠር የሚችል ልጅ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ዕፅ እንዲወስድ ወይም በአሥራ አራት ዓመቱ የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽም ሲጠየቅ እምቢ ለማለት የሚያስችል የተሻለ አቅም ይኖረዋል።”

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ ልጆች ስንናገር በወንድ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

^ አን.6 ኖ፡ ዋይ ኪድስ—ኦቭ ኦል ኤጅስ—ኒድ ቱ ሂር ኢት ኤንድ ዌይስ ፓሬንትስ ካን ሴይ ኢት ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።

^ አን.8 ቱ ማች ኦቭ ኤ ጉድ ቲንግ—ሬይዚንግ ችልድረን ኦቭ ካራክተር ኢን አን ኢንደልጀንት ኤጅ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።