በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መከራ የሌለበት ሕይወት—አስተማማኝ ተስፋ

መከራ የሌለበት ሕይወት—አስተማማኝ ተስፋ

መከራ የሌለበት ሕይወት—አስተማማኝ ተስፋ

“[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”​—ራእይ 21:4

አስደሳች በሆነው በዚህ ተስፋ ላይ እምነት መጣል ይቻላል? እስቲ ለአዳም ከተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች መካከል አንዱን ተመልከት። አምላክ፣ አዳም ትእዛዙን የሚጥስ ከሆነ ‘በእርግጥ እንደሚሞት’ ነግሮት ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) አምላክ የተናገረው ነገር ምንም መሬት ጠብ ሳይል ተፈጽሟል። አምላክ የተናገረው ነገር መፈጸሙ እንዲሁም የሰው ልጆች የወረሱት ሞትና መከራ አምላክ እምነት ሊጣልበት እንደሚችል የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ታዲያ አምላክ በምድር ላይ ፍጹም የሆኑ ሁኔታዎችን ለማስፈን የገባው ቃል እንደሚፈጸም የምንጠራጠርበት ምክንያት ይኖራል?

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ስለተብራሩት የአምላክ ባሕርያትም አስብ። መከራ እንዲወገድ የምንጓጓው እንደ ርኅራኄ፣ ፍቅርና ፍትሕ ያሉ የአምላክ ባሕርያት እኛም ስላሉን ነው። ከዚህም በላይ በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ የሚታዩት ክስተቶችና የሰዎች ባሕርያት አምላክ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ በፍጥነት እየቀረበ መሆኑን ያሳያሉ።​— “እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ይሖዋ አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን መከራ ለማስወገድ ከማንም በላይ ብቃት አለው የምንለው ለምንድን ነው? ለመከራ ዋነኛ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች አምላክ በልጁ በኢየሱስ አማካኝነት እንዴት እንደሚያስወግድና ይህን ከግቡ ለማድረስ ምን ዝግጅት እንዳደረገ ተመልከት።

ሰዎች የሚያደርጉት ምርጫ።

አባታችን አዳም ያደረገው ምርጫ በዘሮቹ ሁሉ ላይ አስከፊ መዘዝ አስከትሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ በአንድነት ሆኖ በመቃተትና አብሮ በመሠቃየት ላይ እንደሚገኝ” ጽፏል። (ሮም 8:22) አምላክ የሚያመጣው መፍትሔ ፍጹም ፍትሕና ታላቅ ምሕረት የሚንጸባረቅበት እንዲሁም ያልተወሳሰበ ነው። ሮም 6:23 “ኃጢአት የሚከፍለው ደሞዝ ሞት ነው፤ አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” ይላል።

ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ኃጢአት አልሠራም። እንዲያውም በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በመሞት ታዛዥ የሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት እርግማን ነፃ የሚሆኑበትን መሠረት ጥሏል። በመሆኑም ጥበብ የጎደላቸው ምርጫዎች እንድናደርግ የሚገፋፋን የኃጢአት ዝንባሌ በማይኖርበት ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አግኝተናል። በተጨማሪም ‘ክፉ ሰዎች ስለሚጠፉ’ ሆን ብለው በሌሎች ላይ መከራ የሚያደርሱ ሰዎች አይኖሩም።​—መዝሙር 37:9

ያልተጠበቁ ክስተቶችና አለፍጽምና።

አምላክ የሾመው ንጉሥ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ የምድርን የተፈጥሮ ኃይሎች የመቆጣጠር ኃይል አለው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም.፣ ኢየሱስና ሐዋርያቱ በአንዲት የዓሣ ማስገሪያ ጀልባ እየተጓዙ ሳሉ “እጅግ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ተነሳ፤ ማዕበሉም ከጀልባዋ ጋር እየተላተመ ወደ ውስጥ ይገባ ጀመር፤ ከዚህም የተነሳ ጀልባዋ በውኃ ልትሞላ ተቃረበች።” ሐዋርያቱ ኢየሱስን እንዲረዳቸው በጠየቁት ጊዜ “ተነስቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም ‘ጸጥ በል! ረጭ በል!’ አለው። ነፋሱም ቆመ፤ ታላቅ ጸጥታም ሰፈነ።” በዚህ ጊዜ ሐዋርያቱ እጅግ በመደነቅ ‘ነፋስና ባሕር እንኳ ይታዘዙለታል’ አሉ።​—ማርቆስ 4:37-41

ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በኢየሱስ አገዛዝ ሥር ‘በእርጋታ ይቀመጣሉ፣ ከመከራም ሥጋት ያርፋሉ።’ (ምሳሌ 1:33 የ1954 ትርጉም) ይህም የተፈጥሮ አደጋዎች የሚያስከትሉትን መከራ ይጨምራል። ከዚህም ባሻገር ምድርን የሚያበላሹ፣ ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ሕንፃዎችን የሚገነቡና የምድር የተፈጥሮ ኃይሎች የሚሰጡትን ማስጠንቀቂያ ችላ የሚሉ ብሎም ሌሎች ጥፋቶችን የሚሠሩ ሰዎች አይኖሩም። በአጉል ጊዜ አጉል ቦታ ላይ በመሆን ለአደጋ የሚጋለጥ ሰው አይኖርም።

ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ባልተጠበቁ ክስተቶች ሳቢያ ለሚመጡ መከራዎች በእሱ አገዛዝ ሥር መፍትሔ መስጠት እንደሚችል ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አሳይቷል። ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ብሏል። (ዮሐንስ 11:25) አዎ፣ ኢየሱስ በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወታቸውን ያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት ለማስነሳት ኃይሉም ሆነ ፍላጎቱ አለው። ይህ ከንቱ ተስፋ ነው? ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ሰዎችን ከሞት በማስነሳት በእሱ ላይ ያለንን እምነት ይበልጥ አጠናክሮልናል። ሰዎችን ከሞት እንዳስነሳ የሚገልጹ ሦስት ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ።​—ማርቆስ 5:38-43፤ ሉቃስ 7:11-15፤ ዮሐንስ 11:38-44

“የዚህ ዓለም ገዥ።”

አምላክ፣ “ሞት የማስከተል ኃይል ያለውን ዲያብሎስን . . . እንዳልነበረ ያደርገው ዘንድ” ክርስቶስ ኢየሱስን ሾሞታል። (ዕብራውያን 2:14) ኢየሱስ “ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህ ዓለም ገዥ አሁን ወደ ውጭ ይጣላል” ብሏል። (ዮሐንስ 12:31) ኢየሱስ፣ ዲያብሎስ በዓለም ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እንዳይችል ‘የዲያብሎስን ሥራ ያፈርሳል።’ (1 ዮሐንስ 3:8) ዲያብሎስ የሚያስፋፋው የስስትና የራስ ወዳድነት መንፈስ እንዲሁም ምግባረ ብልሹነት በሚወገድበት ጊዜ በሰው ልጅ ኅብረተሰብ ላይ የሚታየውን ለውጥ አስበው!

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 “እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው?”

ሐዋርያቱ “እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ኢየሱስን ጠይቀውት ነበር። (ማቴዎስ 24:3) ኢየሱስ የሰጠው መልስና እሱ ከሞተ በኋላ በመንፈስ መሪነት የተጻፉት ሌሎች ጽሑፎች አምላክ መከራን የሚያስወግድበት ጊዜ ሲቃረብ ምን ነገሮች እንደሚፈጸሙ አሳውቀውናል። * ከታች የተጠቀሱትን ትንቢቶች፣ በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ በስፋት ከሚታዩት ሁኔታዎችና ሰዎች ከሚያንጸባርቁት ባሕርይ ጋር አነጻጽር።

● ዓለም አቀፋዊ ጦርነት​ማቴዎስ 24:7፤ ራእይ 6:4

● ረሃብና በሽታ​ሉቃስ 21:11፤ ራእይ 6:5-8

● ምድርን ማበላሸት​ራእይ 11:18

● “ገንዘብ የሚወዱ”​2 ጢሞቴዎስ 3:2

● “ለወላጆች የማይታዘዙ”​2 ጢሞቴዎስ 3:2

● “አምላክን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ”​2 ጢሞቴዎስ 3:4

የይሖዋ ምሥክሮች በቅርቡ መከራ የሌለበት ሕይወት እንደሚመጣ ማወቅ እንድትችል አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። ይህን ጉዳይ በተመለከተ በአካባቢህ የሚኖሩትን የይሖዋ ምሥክሮች ልታነጋግራቸው ትችላለህ። በራስህ ቤት ወይም ለአንተ አመቺ በሆነ ስፍራ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ፈቃደኞች ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 የበለጠ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ላይ “የምንኖረው ‘በመጨረሻው ዘመን’ ውስጥ ነው?” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ 9⁠ን ተመልከት።