በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነት ልትጥልበት የምትችል መጽሐፍ​—ክፍል 6

ሮም በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ

እምነት ልትጥልበት የምትችል መጽሐፍ​—ክፍል 6

ይህ ርዕስ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የተገለጹትን ሰባት የዓለም ኃያላን መንግሥታት በተመለከተ “በንቁ!” ላይ ከሚወጡት ሰባት ተከታታይ ርዕሶች መካከል ስድስተኛው ነው። ዓላማውም መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበትና በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መጽሐፍ እንደሆነ እንዲሁም ተስፋ የሚፈነጥቅ መልእክት እንደያዘ ማሳየት ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ተስፋ፣ ጭካኔ የተሞላበት የሰው ልጆች አገዛዝ ያስከተለው መከራና ሥቃይ እንደሚያከትም ይገልጻል።

ጳውሎስ በአፒያን ጎዳና ተጉዟል

ኢየሱስ ክርስትናን የመሠረተውም ሆነ ተከታዮቹ የክርስትናን ትምህርት ወደ ተለያዩ አገሮች ያሰራጩት በሮማውያን የግዛት ዘመን ነበር። ዛሬም ቢሆን እንደ ብሪታንያና ግብፅ ባሉት አገሮች ሮማውያን የሠሯቸውን መንገዶች፣ የውኃ መውረጃ ቦዮችና ሐውልቶች ማየት ይቻላል። እነዚህ ነገሮች በገሃዱ ዓለም ያሉ ናቸው። በመሆኑም ኢየሱስና ሐዋርያቱ እንዲሁም የተናገሯቸውና ያደረጓቸው ነገሮች በገሃዱ ዓለም የነበሩ መሆናቸውን ያስታውሱናል። አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፣ በጥንታዊው የአፒያን ጎዳና ብትጓዝ ክርስቲያን የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሲሄድ በተጠቀመበት መንገድ ተጓዝህ ማለት ነው።—የሐዋርያት ሥራ 28:15, 16

እምነት የሚጣልበት ታሪክ

ስለ ኢየሱስና ስለ ደቀ መዛሙርቱ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በአንደኛው መቶ ዘመን የተከናወኑ በርካታ ታሪኮችን ይጠቅሳል። የመጽሐፍ ቅዱስ ፀሐፊ የነበረው ሉቃስ ሁለት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ክንውኖች የተፈጸሙበትን ይኸውም መጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት የጀመረበትንና ኢየሱስ ተጠምቆ መሲሕ ወይም ክርስቶስ የሆነበትን ዓመት ግልጽ በሆነ መንገድ እንዴት እንደዘገበ ልብ በል። ሉቃስ እነዚህ ነገሮች የተፈጸሙት “ጢባርዮስ ቄሳር በነገሠ በአሥራ አምስተኛው ዓመት [በ29 ዓ.ም.]፣ ይኸውም ጳንጥዮስ ጲላጦስ የይሁዳ አገረ ገዥ፣ ሄሮድስ የገሊላ አውራጃ ገዥ” በነበረበት ጊዜ እንደሆነ ጽፏል። (ሉቃስ 3:1-3, 21) በተጨማሪም ሉቃስ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ሌሎች አራት ባለሥልጣናት ይኸውም ፊልጶስን (የሄሮድስ ወንድም)፣ ሊሳኒዮስን፣ ሐናን እና ቀያፋን ጠቅሷል። ሰባቱም ሰዎች በሕይወት የኖሩ መሆናቸውን ዓለማዊ የታሪክ ምሑራን አረጋግጠዋል። እስቲ ስለ ጢባርዮስ፣ ጲላጦስና ሄሮድስ እንመልከት።

ጢባርዮስ ቄሳር በሰፊው የሚታወቅ ሰው ሲሆን ምስሉም በሥነ ጥበብ ሥራዎች ውስጥ ይገኛል። መስከረም 15 ቀን 14 ዓ.ም. ይኸውም ኢየሱስ የ15 ዓመት ወጣት በነበረበት ወቅት የሮም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ጢባርዮስን ንጉሠ ነገሥት አድርጎ ሾመው።

ጢባርዮስ ቄሳር በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ከተጠቀሱት በርካታ የሮም ባለሥልጣናት አንዱ ነው

የጳንጥዮስ ጲላጦስ ስም ታሲተስ የተባለ ሮማዊ ታሪክ ጸሐፊ በጻፈው ዘገባ ላይ ከጢባርዮስ ስም ጋር አብሮ ተጠቅሷል፤ ታሲተስ ይህን ዘገባ የጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ካለቀ ብዙም ሳይቆይ ነው። ታሲተስ “ክርስቲያን” ስለሚለው ቃል ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “[ክርስቲያን] ለሚለው ስም መገኛ የሆነው ክራይስቱስ በጢባርዮስ የንግሥና ዘመን ከአስተዳዳሪዎቻችን አንዱ በነበረው በጳንጥዮስ ጲላጦስ እጅ ከፍተኛ ቅጣት ተቀብሏል።”

የጳንጥዮስ ጲላጦስ ስም የተቀረጸበት ድንጋይ

ሄሮድስ አንቲጳስ በገሊላ ወንዝ ዳርቻ የምትገኘውን ጥብርያዶስ የምትባለውን ከተማ በመሥራቱ ይታወቃል። መኖሪያውንም በዚህች ከተማ አድርጓል። ሄሮድስ፣ የመጥምቁ ዮሐንስን አንገት ያስቆረጠው በጥብርያዶስ ሳይሆን አይቀርም።

የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በሮማውያን ዘመን የተፈጸሙ ጎላ ብለው የሚታዩ ክንውኖችንም ይጠቅሳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ስለተወለደበት ጊዜ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “በዚያ ዘመን፣ አውግስጦስ ቄሳር የዓለም ሕዝብ ሁሉ እንዲመዘገብ አዋጅ አወጣ፤ (ይህ የመጀመሪያ ምዝገባ የተካሄደው ቄሬኔዎስ የሶርያ አገረ ገዥ በነበረበት ጊዜ ነው፤) ስለዚህ ሁሉም ሰው ለመመዝገብ ወደየራሱ ከተማ ሄደ።”—ሉቃስ 2:1-3

ታሲተስም ሆነ አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ ስለ ቄሬኔዎስ ጠቅሰዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ምዝገባ ተካሂዶ እንደነበረ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አንድ ሮማዊ አገረ ገዥ ባወጣው አዋጅ ላይ ተገኝቷል። በብሪትሽ ቤተ መጻሕፍት የሚገኘው ይህ አዋጅ እንዲህ ይነበባል፦ “ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው የሕዝብ ቆጠራ የሚካሄድበት ጊዜ ስለደረሰ በተለያዩ ምክንያቶች በሌላ አውራጃ የሚገኙ ሁሉ . . . ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ማሳሰብ አስፈላጊ ሆኗል።”

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሮም ንጉሠ ነገሥት በሆነው “በቀላውዴዎስ ዘመን” ስለ ተከሰተ “ታላቅ ረሃብ” ይጠቅሳል። (የሐዋርያት ሥራ 11:28) በአንደኛው መቶ ዘመን የነበረው ጆሴፈስ የተባለ ታሪክ ጸሐፊ ይህ ዘገባ እውነት መሆኑን አረጋግጧል። “በዚያ ዘመን ከባድ ረሃብ የተከሰተ ሲሆን ብዙ ሰዎች ሞተዋል” ሲል ጽፏል።

ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ “ቀላውዴዎስ አይሁዳውያን ሁሉ ከሮም እንዲወጡ [እንዳዘዘ]” በሐዋርያት ሥራ 18:2 ላይ ይናገራል። ይህን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ስዊቶኒየስ የተባለ ሮማዊ የታሪክ ምሑር በ121 ዓ.ም. በጻፈው የቀላውዴዎስ ሕይወት ታሪክ ላይ ተገኝቷል። ስዊቶኒየስ በዘገባው ላይ ቀላውዴዎስ “አይሁዳውያንን በሙሉ ከሮም አባረረ” ብሏል፤ አክሎም አይሁዳውያኑ ለክርስቲያኖች ባላቸው ጥላቻ ምክንያት “ሁልጊዜ ረብሻ ይፈጥሩ” እንደነበር ገልጿል።

ከላይ የተጠቀሰው ረሃብ በተከሰተበት ጊዜ አካባቢ ሄሮድስ አግሪጳ “ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ” አድናቂው ለነበረ ሕዝብ ንግግር እንዳደረገና ሕዝቡም “ይህ የአምላክ ድምፅ ነው እንጂ የሰው አይደለም” እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ከዚያ በኋላ አግሪጳ ‘በትል ተበልቶ እንደሞተ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (የሐዋርያት ሥራ 12:21-23) ይህን ሁኔታ ጆሴፈስም የዘገበ ሲሆን አንዳንድ ተጨማሪ ሐሳቦችንም ጠቅሷል። አግሪጳ ንግግር ያደረገው “ሙሉ በሙሉ ከብር የተሠራ ልብስ” ለብሶ እንደሆነ ጽፏል። በተጨማሪም ‘አግሪጳ የሆድ ሕመም ያሠቃየው እንደጀመርና ሕመሙ በጣም ከባድ እንደነበር’ ጆሴፈስ ጽፏል። አክሎም ከአምስት ቀን በኋላ አግሪጳ መሞቱን ገልጿል።

እምነት የሚጣልበት ትንቢት

መጽሐፍ ቅዱስ በሮማውያን ዘመን ተጽፈው በዚያው ዘመን ፍጻሜያቸውን ያገኙ አስገራሚ ትንቢቶችንም ይዟል። ለምሳሌ ኢየሱስ በውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በገባበት ጊዜ ስለዚህች ከተማ ያለቀሰ ከመሆኑም ሌላ የሮማውያን ሠራዊት እንዴት እንደሚያጠፋት ትንቢት ተናግሯል። ኢየሱስ “ጠላቶችሽ በሾለ እንጨት ዙሪያሽን ቅጥር ቀጥረው . . . አንቺን የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣል” ብሏል። አክሎም “በአንቺ ውስጥም ሳያፈርሱ እንደተነባበረ የሚተዉት ድንጋይ አይኖርም፤ ምክንያቱም በአንቺ ላይ ምርመራ የሚካሄድበትን ጊዜ አልተገነዘብሽም” ሲል ተንብዮአል።​—ሉቃስ 19:41-44

ይሁን እንጂ የኢየሱስ ተከታዮች ለማምለጥ አጋጣሚ ያገኛሉ። እንዴት? ኢየሱስ ግልጽ የሆነ መመሪያ አስቀድሞ ሰጥቷቸዋል። እንዲህ በማለት አስጠንቅቋቸው ነበር፦ “ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ተከባ ስታዩ መጥፊያዋ እንደቀረበ እወቁ። በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በከተማይቱ ውስጥ ያሉም ከዚያ ይውጡ።” (ሉቃስ 21:20, 21) የኢየሱስ ተከታዮች ‘ከተከበበች ከተማ ሸሽተን ልንወጣ የምንችለው እንዴት ነው?’ ብለው ግራ ሳይጋቡ አይቀሩም።

ጆሴፈስ በዚያ ወቅት የተፈጸመውን ሁኔታ መዝግቦልናል። በ66 ዓ.ም. አንድ ሮማዊ አገረ ገዥ አይሁዳውያን ለሮም መንግሥት መክፈል የነበረባቸውን ውዝፍ ግብር ከቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት በወሰደ ጊዜ በሁኔታው የተቆጡ የአይሁድ ዓማፂያን የሮም ወታደሮችን ፈጇቸው፤ ከዚያም ይሁዳ ከሮም አገዛዝ ነፃ እንደወጣች አወጁ። በዚያው ዓመት የሶርያ አገረ ገዥ የነበረው ሮማዊው ሴስቲየስ ጋለስ 30,000 ወታደሮችን አስከትሎ በስተደቡብ በመዝመት በአይሁድ በዓል ወቅት ኢየሩሳሌም ደረሰ። ጋለስ በከተማዋ ዙሪያ ያለውን አካባቢ ዘልቆ ወደ ኢየሩሳሌም በመግባት ዓማፂያኑ የተሸሸጉበትን የቤተ መቅደሱን ግንብ እስከ ማፍረስ ደርሶ ነበር። ከዚያም ጋለስ ባልታወቀ ምክንያት ሠራዊቱን ይዞ ወደኋላ ተመለሰ! ሁኔታው ያስደሰታቸው አይሁዳውያን በማፈግፈግ ላይ የሚገኘውን ሠራዊት ተከታትለው ጥቃት ሰነዘሩ።

ታማኝ ክርስቲያኖች ሁኔታው በዚህ መንገድ መለዋወጡን በማየት አልተታለሉም። ኢየሱስ የተናገረው አስገራሚ ትንቢት ሲፈጸም እንደተመለከቱ ተገነዘቡ፦ ከተማዋ በጦር ሠራዊት ተከባ ነበር! አሁን ሠራዊቱ ስላፈገፈገ ታማኝ ክርስቲያኖች በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም ከከተማዋ ሸሹ። ብዙዎቹ ከዮርዳኖስ ወንዝ ባሻገር በተራራው ላይ ወደምትገኝ ፔላ የተባለች ገለልተኛ የሆነች የአሕዛብ ከተማ ሄዱ።

ኢየሩሳሌምስ ምን ደረሰባት? በቨስፔዥያንና በልጁ ቲቶ የሚመራው የሮማውያን ሠራዊት ከ60,000 ወታደሮች ጋር ተመለሰ። ሮማውያኑ በ70 ዓ.ም. ከዋለው የፋሲካ በዓል በፊት በኢየሩሳሌም ላይ በመዝመት የከተማይቱን ነዋሪዎችና በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማይቱ የመጣውን ሕዝብ ከበቧቸው። የሮም ወታደሮች በአካባቢው የነበረውን ደን መንጥረው ባዘጋጇቸው የሾሉ እንጨቶች ተጠቅመው ልክ ኢየሱስ እንደተነበየው በከተማዋ ዙሪያ ቅጥር ሠሩ። ከአምስት ወር ገደማ በኋላ ከተማዋ ወደቀች።

በሮም የሚገኘው የቲቶ ቅስት በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌም ለመጥፋቷ መታሰቢያ ነው

ቲቶ በኢየሩሳሌም ያለው ቤተ መቅደስ እንዳይነካ አዝዞ የነበረ ቢሆንም አንድ ወታደር እሳት ስለለኮሰበት ሙሉ በሙሉ ወደመ፤ ልክ ኢየሱስ እንደተነበየው ሳይፈርስ እንደተነባበረ የቀረ ድንጋይ አልነበረም። ጆሴፈስ እንደዘገበው 1,100,000 የሚያህሉ አይሁዳውያንና ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች አለቁ፤ አብዛኞቹ የሞቱት በረሃብና በቸነፈር ምክንያት ነው። ከእነዚህ ሌላ 97,000 የሚያህሉ ደግሞ በግዞት ተወሰዱ። ብዙዎች በባርነት ወደ ሮም ተላኩ። ዛሬ ሮምን ብትጎበኝ ቲቶ በይሁዳ ላይ ከዘመተ በኋላ ያጠናቀቀውን ዝነኛውን ኮሎሲየም ማየት ትችላለህ። በተጨማሪም ቲቶ ኢየሩሳሌምን ድል በማድረጉ ለመታሰቢያነት የቆመውን የቲቶ ቅስት መመልከት ትችላለህ። አዎን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በዝርዝር ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር እምነት የሚጣልበት ነው። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለሚናገረው ትንቢት ትኩረት መስጠታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

እምነት ልትጥልበት የምትችል ተስፋ

ኢየሱስ በሮማዊው አገረ ገዥ በጳንጥዮስ ጲላጦስ ፊት በቀረበ ጊዜ “የዚህ ዓለም ክፍል [ስላልሆነ]” አንድ መንግሥት ወይም መስተዳድር ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 18:36) ኢየሱስ፣ በንጉሥ ስለሚተዳደረው ስለዚህ መንግሥት እንዲጸልዩ ለተከታዮቹ አስተምሯል። “በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ . . . መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” ብለው እንዲጸልዩ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ እንዲፈጸም የሚያደርገው የአምላክን ፈቃድ እንጂ ትዕቢተኛና የሥልጣን ጥመኛ የሆኑ የሰው ልጆችን ፈቃድ እንዳልሆነ ልብ በል።

ኢየሱስ በሰማይ የሚገኘው የዚህ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ይገዛል። እንዲሁም ከአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ምድርን ከዳር እስከ ዳር ገነት ያደርጋታል።​—ሉቃስ 23:43

የአምላክ መንግሥት ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ እርምጃ የሚወስደው መቼ ነው? ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለሐዋርያው ዮሐንስ ባስተላለፈው መልእክት ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ የሚጠቁም ነገር ተናግሯል፤ ይህ የሆነው የሮም ንጉሠ ነገሥት በነበረው በደሚሸን (የቲቶ ወንድም) ዘመን ሲሆን በወቅቱ ዮሐንስ በጳጥሞስ ደሴት ታስሮ ነበር። ኢየሱስ ለዮሐንስ እንዲህ ብሎታል፦ “ሰባት ነገሥታት ናቸው፦ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አለ፤ ሌላው ደግሞ ገና አልመጣም፤ በሚመጣበት ጊዜ ግን ለአጭር ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል።”​—ራእይ 17:10

ዮሐንስ ይህን መልእክት በመዘገበበት ወቅት አምስት “ነገሥታት” ወይም መንግሥታት ወድቀው ነበር፤ እነሱም ግብፅ፣ አሦር፣ ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስና ግሪክ ናቸው። በሐዋርያው ዮሐንስ ዘመን የሚገዛው ወይም “አለ” የተባለው ሮም ነበር። ስለዚህ የሚቀረው አንድ መንግሥት ብቻ ሲሆን እሱም በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የመጨረሻ የሆነው የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። ታዲያ ይህ መንግሥት ማን ነው? ምን ያህል ጊዜስ ይገዛል? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው የንቁ! እትም ላይ ይብራራሉ።