በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነት ልትጥልበት የምትችል መጽሐፍ—ክፍል 1

ግብፅ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ

እምነት ልትጥልበት የምትችል መጽሐፍ—ክፍል 1

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው 1,600 በሚያህሉ ዓመታት ውስጥ ነው። በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙት ታሪኮችና ትንቢቶች ከሰባት የዓለም ኃያላን መንግሥታት ማለትም ከግብፅ፣ ከአሦር፣ ከባቢሎን፣ ከሜዶ ፋርስ፣ ከግሪክ፣ ከሮምና ከአንግሎ አሜሪካ ጋር የተያያዙ ናቸው። ከዚህ እትም ጀምሮ በሚወጡ ሰባት ተከታታይ እትሞች ላይ ስለ እነዚህ መንግሥታት አንድ በአንድ እንመለከታለን። ይህን የምናደርግበት ዓላማ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበትና በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መጽሐፍ እንደሆነ እንዲሁም ተስፋ የሚፈነጥቅ መልእክት እንደያዘ ለማሳየት ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ተስፋ የሰው ልጆች ብልሹ አገዛዝ ያስከተለው መከራና ሥቃይ እንደሚያከትም ይገልጻል።

በፒራሚዶቿና በናይል ወንዝ የምትታወቀው ግብፅ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ የዓለም ኃያል መንግሥት ነበረች። የእስራኤል ብሔር የተወለደው በዚህች መንግሥት ጥላ ሥር ነበር። የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የጻፈው ሙሴም የተወለደውና የተማረው በግብፅ ነበር። ታዲያ የዓለም ታሪክና የአርኪኦሎጂ ጥናት ሙሴ ስለዚያች ጥንታዊት አገር የጻፈውን ዘገባ ይደግፋሉ? እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

እምነት የሚጣልበት ታሪክ

ማዕረጎችና ስያሜዎች።

አንድ ታሪክ ስለ ባሕሎች፣ ስለ ወጎች፣ ስለ ስሞች፣ ለባለሥልጣናት ስለሚሰጡ ማዕረጎችና ስለመሳሰሉት ነገሮች ዝርዝር መረጃ መያዙ ብዙውን ጊዜ ትክክለኛ መሆኑን ይጠቁማል። ታዲያ የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ማለትም ዘፍጥረትና ዘፀአት ከዚህ መመዘኛ አንጻር ሲታዩ እንዴት ናቸው? ጆን ጋሮ ደንከን፣ ኒው ላይት ኦን ሂብሪው ኦሪጅንስ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ የያዕቆብ ልጅ የሆነውን ዮሴፍን አስመልክቶ ስለሚናገረው ስለ ዘፍጥረት ዘገባ እንዲሁም ስለ ዘፀአት መጽሐፍ ሲናገሩ “[የመጽሐፍ ቅዱሱ ጸሐፊ] የግብፅን ቋንቋ፣ ባሕል፣ እምነት፣ የቤተ መንግሥት ኑሮና ወግ እንዲሁም የመንግሥት ባለሥልጣናትን በደንብ ያውቅ ነበር” ብለዋል። አክለው እንዲህ ብለዋል፦ “[ጸሐፊው] በወቅቱ ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን ትክክለኛ የማዕረግ ስም በተገቢው ሁኔታ ይጠቀም ነበር። . . . ጸሐፊዎቹ ፈርዖን የሚለውን ስም በተለያዩ ዘመናት መጠቀማቸው በብሉይ ኪዳን ጊዜ ስለነበሩት ግብፃውያን የጠለቀ እውቀት እንደነበራቸው ብሎም ተአማኒነት እንዳላቸው የሚጠቁም ከሁሉ የላቀ ማስረጃ ነው።” በተጨማሪም ደንከን “[ጸሐፊው] ባለታሪኮቹ በፈርዖን ፊት ሲቀርቡ ትክክለኛውን የቤተ መንግሥት ወግ እንደተከተሉና ተገቢውን ቋንቋ እንደተጠቀሙ አድርጎ ጽፏል” በማለት ተናግረዋል።

የጡብ ሥራ።

እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት በነበሩበት ጊዜ የሸክላ ጭቃና ጭድ በማደባለቅ ለግንባታ የሚያገለግሉ ጡቦችን ይሠሩ የነበረ ሲሆን ጭዱ ጭቃውን ለማያያዝ ይረዳቸው ነበር። (ዘፀአት 1:14፤ 5:6-18) * ኤንሸንት ኢጂብሺያን ማቴሪያልስ ኤንድ ኢንዱስትሪስ የተሰኘው መጽሐፍ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የግብፅን ያህል [ጡብ መሥራት] የተለመደ የሆነባቸው ቦታዎች ጥቂት ናቸው፤ በፀሐይ የደረቁ ጡቦች በቀድሞው ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም በዚህች አገር ዋነኛ የግንባታ ቁሳቁስ ሆነው ያገለግላሉ።” በተጨማሪም መጽሐፉ “ግብፃውያን ጡብ ሲሠሩ ጭድ ይጠቀሙ እንደነበረ” ይጠቅሳል፤ ይህም መጽሐፍ ቅዱስ በግብፅ ጡብ ስለሚሠራበት መንገድ የሚገልጸው ሐሳብ እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጣል።

መላጨት።

በጥንት ዘመን ዕብራውያን ወንዶች ጢማቸውን ያሳድጉ ነበር። ሆኖም ዮሴፍ፣ ፈርዖን ፊት ከመቅረቡ በፊት እንደተላጨ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ዘፍጥረት 41:14) ዮሴፍ የተላጨው ለምን ነበር? በግብፃውያን ባሕልና ወግ መሠረት አንድ ሰው ፊቱ ላይ ፀጉር ካለ ንጹሕ እንዳልሆነ ተደርጎ ይታይ ስለነበር ነው። “[ግብፃውያን] ሙልጭ አድርገው በመላጨታቸው ይኩራሩ ነበር” በማለት ኤቭሪዴይ ላይፍ ኢን ኤንሸንት ኢጂፕት የተሰኘው መጽሐፍ ይናገራል። እንዲያውም ምላጭ፣ ፀጉር መንቀያና መስታወት የያዙ የመዋቢያ ዕቃ መያዣዎች በመቃብር ውስጥ ተገኝተዋል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሙሴ ጠንቃቃ ታሪክ ጸሐፊ ነበር። ከጥንታዊቷ ግብፅ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የጻፉ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም ቢሆኑ እንዲሁ ጠንቃቆች ነበሩ።

ንግድ ነክ ጉዳዮች።

የአንደኛና የሁለተኛ ነገሥት መጻሕፍትን የጻፈው ኤርምያስ፣ ንጉሥ ሰለሞን ከግብፃውያንና ከኬጢያውያን ጋር ፈረሶችንና ሠረገላዎችን እንዴት ይገበያይ እንደነበር የሚገልጽ ዝርዝር ዘገባ አስፍሯል። የአንዱ ሠረገላ ዋጋ “ስድስት መቶ ሰቅል ብር” ሲሆን የአንድ ፈረስ ዋጋ ደግሞ “መቶ አምሳ ሰቅል ብር” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ ይህ ሲባል የአንድ ፈረስ ዋጋ የሠረገላው ዋጋ ሩብ ነበር ማለት ነው።—1 ነገሥት 10:29

አርኪኦሎጂ ኤንድ ዘ ሪሊጂን ኦቭ ኢዝሪኤል የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ከሆነ የግሪኩ ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶተስና የአርኪኦሎጂ ግኝቶች፣ በንጉሥ ሰለሞን የግዛት ዘመን የደራ የፈረሶችና የሠረገሎች ንግድ ይካሄድ እንደነበር ያረጋግጣሉ። እንዲያውም ይህ መጽሐፍ “አንድ የግብፃውያን ሠረገላ በአራት . . . ፈረሶች የሚለወጥበት መደበኛ የግብይት ሥርዓት ነበር” ብሏል፤ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው አኃዝ ትክክለኛ መሆኑን ያረጋግጣል።

ጦርነት።

ፈርዖን ሺሻቅ፣ ይሁዳን እንደወረረ ኤርምያስና ዕዝራ የዘገቡ ሲሆን ይህንንም ያደረገው የይሁዳ ንጉሥ የሆነው “ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት” (በ993 ዓ.ዓ. ማለት ነው) እንደነበረ ለይተው ጠቅሰዋል። (1 ነገሥት 14:25-28፤ 2 ዜና መዋዕል 12:1-12) ለረጅም ጊዜ ያህል፣ ስለዚህ ወረራ የሚጠቅስ ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ አይገኝም ነበር። በኋላ ላይ ግን በካርናክ (የጥንቷ ቴብስ) በሚገኝ አንድ የግብፃውያን ቤተ መቅደስ ግድግዳ ላይ የተቀረጸ አንድ ምስል ተገኘ።

በምስሉ ላይ ሺሻቅ፣ አሞን በሚባለው አምላኩ ፊት እንደቆመና ምርኮኞቹን ለመምታት እጁን እንደዘረጋ ይታያል። በተጨማሪም ሺሻቅ ድል ያደረጋቸው የእስራኤላውያን ከተሞች ስም ተመዝግቦ ተገኝቷል፤ ከእነዚህ ከተሞች ውስጥ አብዛኞቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ጋር ተመሳሳይ እንደሆኑ ታውቋል። ከዚህም ሌላ “የአብራም እርሻ” የሚል ሐሳብ ተጽፎ ተገኝቷል፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው የጥንቱ አብርሃም በግብፃውያን መዛግብት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የተገኘው እዚህ ላይ ነው።—ዘፍጥረት 25:7-10

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ያሰፈሩት ዘገባ ልብ ወለድ ታሪክ አይደለም። ጸሐፊዎቹ በአምላክ ፊት ተጠያቂ እንደሆኑ በመገንዘብ የእስራኤላውያንን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ታሪኮችንም እንኳ ሳይሸሽጉ እውነቱን ጽፈዋል፤ ሺሻቅ በይሁዳ ላይ ስለተቀዳጃቸው ድሎች የሚገልጸውን ዘገባ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። እንዲህ ዓይነቱ ሐቀኝነት፣ መሪዎቻቸውን ወይም ሕዝባቸውን ከሚያሞጋግስ ነገር ውጭ ሌላ ምንም ዓይነት ዘገባ መጻፍ የማይፈልጉት የጥንት ግብፃውያን ጸሐፊዎች ካሰፈሯቸው የተቀባቡና የተጋነኑ ታሪኮች ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ የጎላ ነው።

እምነት የሚጣልበት ትንቢት

ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል መናገር የሚችለው የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ለምሳሌ ኤርምያስ፣ ሜምፎስና ቴብስ ስለሚባሉት ሁለት የግብፅ ከተሞች በይሖዋ መንፈስ መሪነት የተናገረውን ትንቢት ልብ በል። ሜምፎስ ወይም ኖፍ በአንድ ወቅት በጣም የታወቀች የንግድ፣ የፖለቲካና የሃይማኖት ማዕከል ነበረች። ሆኖም አምላክ “ሜምፎስ ፈራርሳ፣ ሰው የማይኖርባት ባድማ ትሆናለች” ብሎ ነበር። (ኤርምያስ 46:19) ይህም በትክክል ተፈጽሟል። ኢን ዘ ስቴፕስ ኦቭ ሞሰስ ዘ ሎውጊቨር የተሰኘው መጽሐፍ የዓረብ ወራሪዎች ‘ግዙፍ የሆኑትን የሜምፎስ ፍርስራሾች’ በመውሰድ ለግንባታ እንደተጠቀሙባቸው ይናገራል። አክሎም በዛሬው ጊዜ “የጥንቷ ከተማ በነበረችበት ሰፊ ቦታ ላይ አንድ ድንጋይ እንኳ አይታይም” ብሏል።

ቀደም ሲል ኖእ አሞን ወይም ኖእ ተብላ ትጠራ የነበረችው ቴብስና ምንም ማድረግ የማይችሉት አማልክቶቿም ተመሳሳይ ዕጣ ደርሶባቸዋል። በአንድ ወቅት የጥንቷ ግብፅ ዋና ከተማ እንዲሁም አሞን የሚባለው አምላክ ዋነኛ የአምልኮ ማዕከል የነበረችውን ይህችን ከተማ አስመልክቶ ይሖዋ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በቴብስ አምላክ በአሞን ላይ፣ በፈርዖን ላይ፣ በግብፅና በአማልክቷ ላይ . . . ቅጣት አመጣለሁ፤ . . . ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር . . . አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።” (ኤርምያስ 46:25, 26) በትንቢት እንደተነገረውም የባቢሎን ንጉሥ ግብፅንና ስመ ጥር የሆነችውን ከተማዋን ኖእ አሞንን ድል አደረጋቸው። ከዚያም በ525 ዓ.ዓ. የፋርሱ ንጉሥ ዳግማዊ ካምቢሰስ በከተማዋ ላይ በድጋሚ ጥቃት ሰነዘረ፤ ከዚያ በኋላ ከተማዋ ቀስ በቀስ እየተዳከመች የሄደች ሲሆን በመጨረሻም ሮማውያን ሙሉ በሙሉ ደመሰሷት። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ትንቢት የሚናገር መሆኑ ከሌሎች መጻሕፍት የተለየ እንዲሆን ያደርገዋል፤ ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጪው ጊዜ በሚናገረው ትንቢት ላይ ለመተማመን ያስችለናል።

እምነት ልትጥልበት የምትችል ተስፋ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበውን የመጀመሪያውን ትንቢት የጻፈው ሙሴ ሲሆን በዚያ ወቅት ግብፅ የዓለም ኃያል መንግሥት ነበረች። * በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ይህ ትንቢት አምላክ ሰይጣንንና ‘ዘሩን’ ማለትም የሰይጣንን ክፉ መንገዶች የሚከተሉትን ሁሉ የሚቀጠቅጥ ‘ዘር’ እንደሚያስነሳ ይናገራል። (ዮሐንስ 8:44፤ 1 ዮሐንስ 3:8) የአምላክ ‘ዘር’ ዋነኛ ክፍል መሲሕ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—ሉቃስ 2:9-14

ክርስቶስ መላውን ምድር የሚገዛ ከመሆኑም ሌላ ክፋትንና ጨቋኝ ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ ያስወግዳል። ከዚያ በኋላ “ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ” መሆኑ ያከትማል። (መክብብ 8:9) ከዚህም በላይ በጥንት ዘመን የኖረው ኢያሱ፣ እስራኤልን እየመራ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳስገባ ሁሉ ኢየሱስም ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ከጥንቷ “ተስፋይቱ ምድር” እጅግ ወደምትልቀውና ሙሉ በሙሉ ገነት ወደምትሆነው የጸዳች ምድር እየመራ ያስገባቸዋል።—ራእይ 7:9, 10, 14, 17፤ ሉቃስ 23:43

ይህ አስደናቂ ተስፋ የጥንቷ ግብፅ ኃያል በነበረችበት ዘመን የተነገረ አንድ ሌላ ትንቢት ያስታውሰናል። በኢዮብ 33:24, 25 ላይ የሚገኘው ይህ ትንቢት አምላክ በትንሣኤ አማካኝነት ሰዎችን ‘ከጉድጓድ’ ወይም ከመቃብር እንኳ እንደሚያወጣቸው ይናገራል። አዎን፣ በክፉዎች ላይ ከሚመጣው ጥፋት ከሚተርፉት ሰዎች በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በሕይወት የሌሉ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ግለሰቦች ትንሣኤ የሚያገኙ ከመሆኑም በላይ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖራቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ራእይ 21:3, 4 እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው። . . . እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”

እምነት የሚጣልበት ታሪክና ትንቢት—ይህ ጭብጥ በቀጣዩ እትም ላይም የሚቀርብ ሲሆን ርዕሰ ትምህርቱ ከግብፅ ቀጥሎ የዓለም ኃያል መንግሥት በነበረው በጥንቱ የአሦር መንግሥት ላይ የሚያተኩር ይሆናል።

^ አን.7 ኢንተርኔት መጠቀም የምትችል ከሆነ www.watchtower.org ከሚለው ድረ ገጻችን ላይ መጽሐፍ ቅዱስን በተለያዩ ቋንቋዎች ማግኘት ትችላለህ። (ለጊዜው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ድረ ገጽ ውስጥ አይገኝም።)

^ አን.18 በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተመዘገበው ትንቢት አምላክ በኤደን ገነት የተናገረው ሲሆን ከጊዜ በኋላ ሙሴ በጽሑፍ አስፍሮታል።