በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነት ልትጥልበት የምትችል መጽሐፍ​—ክፍል 4

ሜዶ ፋርስ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ

እምነት ልትጥልበት የምትችል መጽሐፍ​—ክፍል 4

ይህ ርዕስ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የተገለጹትን ሰባት የዓለም ኃያላን መንግሥታት በተመለከተ “ንቁ!” መጽሔት ላይ ከሚወጡት ሰባት ተከታታይ ርዕሶች መካከል አራተኛው ነው። ዓላማውም መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበትና በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መጽሐፍ እንደሆነ እንዲሁም ተስፋ የሚፈነጥቅ መልእክት እንደያዘ ማሳየት ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ተስፋ፣ ጭካኔ የተሞላበት የሰው ልጆች አገዛዝ ያስከተለው መከራና ሥቃይ እንደሚያከትም ይገልጻል።

የታላላቅ ቤተ መንግሥቶችና የንጉሣዊ መቃብሮች ፍርስራሾች ስለ ጥንቱ የሜዶንና የፋርስ ጥምር መንግሥት ግርማ፣ ኃይልና ብልጽግና ትንሽ ፍንጭ ከመስጠት ባለፈ ያን ያህል መረጃ አይሰጡንም። ሁለቱ መንግሥታት ተጣምረው አንድ መንግሥት ከመሆናቸው በፊት ኃያል የነበረው የሜዶን መንግሥት ነበር። ይሁን እንጂ በ550 ዓ.ዓ. ሜዶናውያን በፋርሳዊው ንጉሥ በዳግማዊ ቂሮስ አገዛዝ ሥር ወደቁ፤ ከዚያም ቂሮስ ሜዶ ፋርስ የተባለው ጥምር መንግሥት ገዥ ሆነ። ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ በስተሰሜን የሚገኘውን አካባቢ ማዕከል ያደረገው ይህ መንግሥት እያደር ግዛቱን በማስፋት ከኤጅያን ባሕር እስከ ግብፅና እስከ ሰሜን ምዕራብ ሕንድ ያለውን አካባቢ ያካተተ ሲሆን ይሁዳንም ይጨምር ነበር።

ሜዶ ፋርስ ከ200 ለሚበልጡ ዓመታት ይኸውም ባቢሎን ከወደቀችበት ከ539 ዓ.ዓ. ጀምሮ ሜዶ ፋርስ ራሱ በግሪካውያን ድል እስከተነሳበት ጊዜ እስከ 331 ዓ.ዓ. ድረስ የአይሁድን ብሔር ገዝቷል። የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በዚህ ዘመን ስለተፈጸሙ ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ክንውኖች ዘግበዋል።

እምነት የሚጣልበት ታሪክ

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዳግማዊ ቂሮስ በባቢሎን ግዞት የነበሩትን አይሁዳውያን ነፃ እንዳወጣቸው እንዲሁም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ባቢሎናውያን በ607 ዓ.ዓ. አፍርሰውት የነበረውን የአምላክ ቤተ መቅደስ እንደገና እንዲሠሩ እንደፈቀደላቸው ይናገራል። (ዕዝራ 1:1-7፤ 6:3-5) በ1879 በጥንቷ ባቢሎን ፍርስራሾች መካከል በተገኘው የቂሮስ ሲሊንደር በመባል በሚታወቀው የሸክላ ቅርጽ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ ይህ ታሪክ እውነት መሆኑን ያረጋግጣል። በዚህ ጽሑፍ ላይ የቂሮስ ስም የተጠቀሰ ከመሆኑም ሌላ ይህ ገዥ ከእሱ በፊት የነበረው መንግሥት በግዞት የወሰዳቸውን ሕዝቦች ነፃ በማውጣት ሃይማኖታዊ ዕቃዎቻቸውን ይዘው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይፈቅድ እንደነበር ተገልጿል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የነበረው ኢሳይያስ ይሖዋ ስለ ቂሮስ የተናገረውን የሚከተለውን ትንቢት መዝግቧል፦ “ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል፤ ኢየሩሳሌምም፣ ‘እንደ ገና ትሠራ’፣ ቤተ መቅደሱም፣ ‘መሠረቱ ይጣል’ ይላል።”—ኢሳይያስ 44:28

እንዲያውም ቂሮስ ለቤተ መቅደሱ ሥራ የሚሆነው ወጪ “ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ይከፈል” ሲል አዝዞ እንደነበረ ዕዝራ 6:3, 4 ይናገራል። ይህ አስገራሚ ሐሳብ ከዓለማዊ ታሪክ ጋር ይስማማል። ፐርሽያ ኤንድ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ “ፋርሳውያን ነገሥታት ምንጊዜም ቢሆን በግዛታቸው ውስጥ የሚገኙ የአምልኮ ቤቶች እንደገና እንዲገነቡ እገዛ የማድረግ ፖሊሲ ነበራቸው” ይላል።

አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱን መልሰው እንዲሠሩ ቂሮስ እንደፈቀደላቸው ቢገልጹም የአይሁድ ተቃዋሚዎች ስላላመኗቸው ይህ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ እነዚህ ተቃዋሚዎች ከጊዜ በኋላ ለታላቁ ዳርዮስ (ቀዳማዊ ዳርዮስ ተብሎም ይጠራል) ደብዳቤ ጽፈው እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ዳርዮስም የመጀመሪያው ትእዛዝ የሰፈረበት መዝገብ እንዲፈለግ አዘዘ። ውጤቱ ምን ሆነ? የቂሮስ ትእዛዝ የሰፈረበት ጥቅልል የግዛቱ ዋና ከተማ በነበረችው በአሕምታ (ኤክባታና) ተገኘ። በመሆኑም ዳርዮስ “እኔ ዳርዮስ [የቤተ መቅደሱ ግንባታ] በትጋት እንዲፈጸም ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ” የሚል መልስ ሰጠ። ከዚያ በኋላ የአይሁድ ተቃዋሚዎች ሥራውን ለማስተጓጎል ጥረት ማድረጋቸውን አቆሙ። *ዕዝራ 6:2, 7, 12, 13

በዝርዝር የሰፈረው ይህ ዘገባ እውነት መሆኑን ዓለማዊ ታሪክ ያረጋግጣል። አንደኛ ነገር፣ አሕምታ የቂሮስ የበጋ መኖሪያ ስለነበረች እዚያ ሆኖ ትእዛዙን አስተላልፎ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም የሜዶ ፋርስ ነገሥታት ግዛታቸውን የሚመለከቱ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን በጥብቅ እንደሚከታተሉና አለመግባባቶች በሚነሱበት ጊዜም ደብዳቤ በመጻፍ መፍትሔ ይሰጡ እንደነበረ በአርኪኦሎጂ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

እምነት የሚጣልበት ትንቢት

ነቢዩ ዳንኤል፣ በአምላክ መንፈስ መሪነት በተመለከተው ሕልም ላይ አራት አራዊት ተከታትለው ከባሕር ሲወጡ አይቶ ነበር፤ እነዚህ አራዊት በተከታታይ የሚነሱ የዓለም ኃያላን መንግሥታትን ያመለክታሉ። የመጀመሪያው አውሬ፣ ክንፍ ያለው አንበሳ ሲሆን እሱም ባቢሎንን ያመለክታል። ሁለተኛው “ድብ ይመስል ነበር።” ዘገባው በመቀጠል ይህ አውሬ “ተነሥ፤ እስክትጠግብ ድረስ ሥጋ ብላ!” እንደተባለ ይገልጻል። (ዳንኤል 7:5) ይህ አስፈሪ ድብ ሜዶ ፋርስን ያመለክታል።

ዳንኤል በትንቢቱ እንደተናገረው የሜዶ ፋርስ መንግሥት ሌሎች ብሔራትን ድል አድርጎ የመቆጣጠር ከፍተኛ ጥማት ነበረው። ዳንኤል ራእዩን ካየ ብዙም ሳይቆይ ቂሮስ ሜዶንን ድል ያደረገ ሲሆን ቀጥሎም አጎራባቾቿ በነበሩት በሊዲያና በባቢሎን ላይ ጦርነት አወጀ። ልጁ ዳግማዊ ካምቢሰስ ደግሞ ግብፅን ድል አደረገ። ከጊዜ በኋላም የሜዶ ፋርስ ነገሥታት ግዛታቸውን ይበልጥ አስፋፉ።

በትንቢቱ ላይ የተገለጸው ድብ ሜዶ ፋርስን እንደሚያመለክት እንዴት እናውቃለን? ከላይ ከተጠቀሰው ሕልም ጋር ተያያዥነት ባለው ሌላ ራእይ ላይ ዳንኤል አንድ አውራ በግ “ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ በቀንዱ ሲጐሽም” ተመልክቶ ነበር። ይህ ትንቢት የተፈጸመው ሜዶ ፋርስ ኃያሏን ባቢሎንን ጨምሮ ሌሎች ብሔራትን “ሲጐሽም” ነበር። አንድ መልአክ እንደሚከተለው በማለት ለዳንኤል የራእዩን ፍቺ ነግሮታል፦ “ያየኸው ሁለት ቀንዶች የነበሩት አውራ በግ፣ የሜዶንና የፋርስን መንግሥታት ያመለክታል።”ዳንኤል 8:3, 4, 20

በዛሬዋ ኢራን ውስጥ በምትገኘው ፓሳርጋዲ በተባለች ጥንታዊት ከተማ ፍርስራሾች መካከል የቂሮስ መቃብር ዛሬም ይታያል

ከዚህም በላይ ባቢሎን ከመሸነፏ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ ይህችን ከተማ ድል የሚያደርጋትን የፋርስ ንጉሥ በስሙ ጠቅሶ ትንቢት የተናገረ ሲሆን ይህ ንጉሥ ባቢሎንን ለመጣል የሚጠቀምበትን የጦር ስልትም ጠቅሷል፤ በዚያ ወቅት ይህ የፋርስ ንጉሥ ገና አልተወለደም ነበር። ኢሳይያስ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ለቀባሁት፣ ቀኝ እጁን ለያዝሁት፣ . . . ሕዝብን ሁሉ ላስገዛለት፣ ደጆች እንዳይዘጉ፣ በሮቹን በፊቱ ለምከፍትለት፣ ለቂሮስ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።” (ኢሳይያስ 45:1) የባቢሎን “ወንዞች” ይኸውም ከተማዋን ከጥቃት ለመከላከል ሲባል የኤፍራጥስን ወንዝ በመጠቀም በከተማዋ ዙሪያ የተሠራው ቦይ እንደሚደርቅ ኢሳይያስም ሆነ ኤርምያስ ተንብየው ነበር። (ኢሳይያስ 44:27፤ ኤርምያስ 50:38) ሄሮዶተስና ዜኖፎን የተባሉት ግሪካውያን ታሪክ ጸሐፊዎች፣ ቂሮስ ባቢሎንን በያዘበት ሌሊት ባቢሎናውያን ታላቅ ግብዣ አድርገው ፈንጠዝያ ላይ እንደነበሩ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጨምሮ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በትክክል መፈጸማቸውን አረጋግጠዋል። (ኢሳይያስ 21:5, 9፤ ዳንኤል 5:1-4, 30) የቂሮስ ሠራዊት የኤፍራጥስ ወንዝ የሚፈስበትን አቅጣጫ ካስቀየረ በኋላ ወንዙን ተሻግሮ መዋጋት ሳያስፈልገው ክፍት በተተወው በር ዘው ብሎ ገባ። ኃያሏ ባቢሎን በአንድ ሌሊት ወደቀች!

ይህ ክንውን ደግሞ ሌላ አስደናቂ ትንቢት እንዲፈጸም መንገድ ከፍቷል። ነቢዩ ኤርምያስ ቀደም ሲል የአምላክ ሕዝቦች ለ70 ዓመት በባቢሎን በግዞት እንደሚቆዩ ተንብዮ ነበር። (ኤርምያስ 25:11, 12፤ 29:10) ይህ ትንቢት በትክክለኛው ጊዜ የተፈጸመ ሲሆን በግዞት የነበሩት አይሁዳውያንም ወደ አገራቸው ሊመለሱ ችለዋል።

እምነት ልትጥልበት የምትችል ተስፋ

ሜዶ ፋርስ ባቢሎንን ድል ካደረገ ብዙም ሳይቆይ ዳንኤል፣ አምላክ ለሰው ልጆች ባለው ዓላማ አፈጻጸም ረገድ በጣም አስፈላጊ የሆነን አንድ ክንውን ለመረዳት የሚያስችለን ትንቢት ጽፏል። መሲሑ ማለትም በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተገለጸው ‘ዘር’ የሚገለጥበትን ትክክለኛ ጊዜ መልአኩ ገብርኤል ለዳንኤል ገልጾለታል። ይህ የአምላክ መልአክ እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ ገዥው መሲሕ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ፣ ሰባት ሱባዔና ሥልሳ ሁለት ሱባዔ [በድምሩ 69 ሱባዔ] ይሆናል።” (ዳንኤል 9:25) በትንቢት የተነገረው ይህ ጊዜ የጀመረው መቼ ነበር?

ቂሮስ አይሁዳውያኑ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የፈቀደው ባቢሎን ከወደቀች ብዙም ሳይቆይ ቢሆንም በርካታ ዓመታት ካለፉ በኋላም ቢሆን ኢየሩሳሌምና ቅጥሮቿ እንደፈራረሱ ነበሩ። በ455 ዓ.ዓ. ንጉሥ አርጤክስስ፣ ጠጅ አሳላፊው ለነበረው ነህምያ የተባለ አይሁዳዊ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ከተማዋንና ቅጥሮቿን እንደገና የመገንባቱን ሥራ በኃላፊነት እንዲመራ ፈቃድ ሰጠው። (ነህምያ 2:1-6) ስልሳ ዘጠኙ ሱባዔ ወይም ሳምንታት የጀመሩት በዚህ ጊዜ ነበር።

ይሁን እንጂ 69ኙ ሳምንታት ቃል በቃል የሰባት ቀን ርዝመት ያላቸው ሳምንታት ሳይሆኑ የዓመታት ሳምንታት ነበሩ። እንዲያውም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ሱባዔ” ወይም ሳምንት የሚለውን ቃል “የዓመታት ሳምንታት” ብለው ተርጉመውታል። * (ዳንኤል 9:24, 25) መሲሑ የሚገለጠው እያንዳንዳቸው የ7 ዓመት ርዝመት ያላቸው 69 ሳምንታት ይኸውም 483 ዓመታት ካለፉ በኋላ ነው። ይህ ትንቢት የተፈጸመው በ29 ዓ.ም. ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ ነው፤ ከ455 ዓ.ዓ. ጀምረን 483 ዓመታት ብንቆጥር 29 ዓ.ም. ላይ እንደርሳለን። *

በትክክል የተፈጸመው የዳንኤል ትንቢት የኢየሱስን ማንነት ከሚያረጋግጡት በርካታ ማስረጃዎች አንዱ ነው። ይህ ማስረጃ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የተሰጡን ተስፋዎችም እንደሚፈጸሙ ያረጋግጥልናል። በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ በጭካኔ የተሞላውን ሰብዓዊ አገዛዝ ያስወግዳል። ከዚያም ሙታን ተነስተው ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ የሚናገረውን ትንቢት ጨምሮ ሌሎች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ይፈጽማል።—ዳንኤል 12:2፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 21:3-5

^ አን.9 ዳርዮስ በሚለው ስም ቢያንስ ሦስት ነገሥታት ይጠሩበታል።

^ አን.20 “ሱባዔ” የሚለውን ቃል “የዓመታት ሳምንታት” ብለው ከተረጎሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ፦ ታናክ—ኤ ኒው ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ሆሊ ስክሪፕቸርስ፣ ዘ ኮምፕሊት ባይብል—አን አሜሪካን ትራንስሌሽን እንዲሁም በጀምስ ሞፋት የተዘጋጀው ዘ ባይብል—ኮንቴይኒንግ ዚ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንትስ። በአማርኛው የ1980 ትርጉም ላይ ደግሞ አንድ ሱባዔ ወይም ሳምንት ሰባት ዓመት እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል።—ዳንኤል 9:24

^ አን.20 ስለ ስልሳ ዘጠኙ የዓመታት ሳምንታት የሚያብራራ ሥዕላዊ መግለጫን ጨምሮ ይህን ትንቢት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የሚለውን መጽሐፍ ከገጽ 197-199 ተመልከት።