በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | ወጣቶች

ወላጅ ሲሞት

ወላጅ ሲሞት

ተፈታታኙ ነገር

ዳሚ፣ አባቷ ከደም ቧንቧ ጋር በተያያዘ የጤና ችግር በሞተበት ወቅት ገና የስድስት ዓመት ልጅ ነበረች። ዴሪክ፣ አባቱ በልብ ሕመም ሲሞት ዘጠኝ ዓመቱ ነበር። ጂኒ ደግሞ እናቷ ለአንድ ዓመት ያህል በማህፀን ካንሰር ስትሠቃይ ቆይታ ሕይወቷ ሲያልፍ ገና የሰባት ዓመት ልጅ ነበረች። *

እነዚህ ልጆች የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡት ገና በልጅነታቸው ነው። አንተስ ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞሃል? ከሆነ ይህ ርዕስ የደረሰብህን ሐዘን መቋቋም እንድትችል ይረዳሃል። * በመጀመሪያ ግን ከሐዘን ጋር የተያያዙ አንዳንድ እውነታዎችን እንመልከት።

ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

ሐዘን በተለያዩ መንገዶች ሊገለጽ ይችላል። አንተ ሐዘንህን የምትገልጽበት መንገድ ሌሎች ሐዘናቸውን ከሚገልጹበት መንገድ ሊለይ ይችላል። ኸልፒንግ ቲንስ ኮፕ ዊዝ ዴዝ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ አንድ ዓይነት ሕግ ወይም ደንብ ማውጣት አይቻልም።” ዋናው ነገር ሐዘንህን አፍነህ ለመያዝ አለመሞከርህ ነው። ለምን? ምክንያቱም . . .

ሐዘንን አምቆ መያዝ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። መግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ጂኒ እንዲህ ብላለች፦ “ለታናሽ እህቴ ስል ጠንካራ መሆን እንዳለብኝ ስለተሰማኝ . . . ስሜቴን አፍኜ ለመያዝ ተገደድኩ። አሁንም ድረስ የሚያሳዝን ነገር ሲያጋጥመኝ ስሜቴን አፍኜ ለመያዝ እሞክራለሁ፤ ይህ ደግሞ ጎጂ ነው።”

ባለሙያዎችም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ዘ ግሪቪንግ ቲን የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ታፍኖ የተያዘ ወይም የታመቀ ስሜት ሁልጊዜ እንደታመቀ አይቀጥልም። ጤንነታችሁ ሊቃወስ ወይም ባልጠበቃችሁት ጊዜ ስሜታችሁ ፈንቅሎ ሊወጣ ይችላል።” አንድ ሰው ስሜቱን አፍኖ ለመያዝ የሚሞክር ከሆነ ሥቃዩን ለማደንዘዝ ሲል ወደ አልኮል መጠጥ ወይም ወደ አደንዛዥ ዕፅ ዞር ሊል ይችላል።

ሐዘን የተደበላለቀ ስሜት ሊፈጥር ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች በሞት የተለያቸው ግለሰብ “ትቷቸው በመሄዱ” በእሱ ላይ ሊበሳጩ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ ‘አምላክ ለምን ይህን ፈቀደ?’ በማለት በአምላክ ላይ ያማርራሉ። ሐዘን የደረሰባቸው በርካታ ሰዎች ግለሰቡ ከመሞቱ በፊት ባደረጉት ወይም በተናገሩት ነገር የተነሳ በጥፋተኝነት ስሜት ይሠቃያሉ፤ ምክንያቱም አሁን በደሉን ማስተካከል የሚችሉበት አጋጣሚ የላቸውም።

ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው፣ የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ የሚሰማንን ስሜት ይህ ነው ብሎ መግለጽ ያስቸግራል። ታዲያ ከሚሰማህ ሐዘን ለመጽናናት ምን ሊረዳህ ይችላል?

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ስሜትህን አውጥተህ ለሌላ ሰው ተናገር። እንዲህ ያለ ከባድ ነገር ሲያጋጥምህ ራስህን ከሌሎች ማግለል ይቀናህ ይሆናል። ነገር ግን ለቤተሰብህ አባል ወይም ለጓደኛህ ስሜትህን አውጥተህ መናገርህ ሐዘንህን መቋቋም እንድትችል ይረዳሃል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 18:24

ስሜትህን በጽሑፍ አስፍር። በሞት ስላጣኸው ወላጅህ አንዳንድ ነገሮችን ለመጻፍ ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ ስለዚያ ሰው ምን ጥሩ ትዝታዎች አሉህ? የነበሩትን መልካም ባሕርያት ጻፍ። አንተ በግልህ ግለሰቡ ካሉት መልካም ባሕርያት መካከል የትኞቹን ማዳበር ትፈልጋለህ?

አሉታዊ ስሜቶች ወደ አእምሮህ እየመጡ ካስቸገሩህ፣ ለምሳሌ አባትህ ወይም እናትህ ከመሞታቸው በፊት የተናገርከው መጥፎ ንግግር ከአእምሮህ አልወጣ ካለ የሚሰማህ ስሜት ምን እንደሆነና እንደዚያ የተሰማህ ለምን እንደሆነ ጻፍ። እንዲህ ብለህ ልትጽፍ ትችላለህ፦ “አባቴ ከመሞቱ በፊት በነበረው ዕለት ከእሱ ጋር ተጨቃጭቄ ስለነበር የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል።”

ከዚያም የሚሰማህ የጥፋተኝነት ስሜት ተገቢ መሆን አለመሆኑን አስብ። ዘ ግሪቪንግ ቲን የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ይቅርታ መጠየቅ የምትችልበት አጋጣሚ እንደማይኖርህ አስቀድመህ ልታውቅ አትችልም፤ በመሆኑም ለዚህ ራስህን ልትወቅስ አይገባም። አንድ ሰው ይቅርታ መጠየቅ የሚያስፈልገው ነገር መናገር ወይም ማድረግ የለበትም ብሎ ማሰብም የማይሆን ነገር ነው።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ኢዮብ 10:1

ራስህን ተንከባከብ። በቂ እረፍት ለማግኘት ሞክር፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ፤ እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ ተመገብ። የምግብ ፍላጎት ከሌለህ ቢያንስ የምግብ ፍላጎትህ እስኪመለስልህ ድረስ ቁርስ፣ ምሳና ራት ጠብቀህ ከመብላት ይልቅ በቀኑ ውስጥ በተለያየ ጊዜ ቀለል ያሉ ሆኖም ጤናማ ምግቦችን ተመገብ። አሸር ባሸር የሆኑ ምግቦችን በመብላት ወይም የአልኮል መጠጥ በመጠጣት ሐዘንህን ለማስታገስ አትሞክር፤ እንዲህ ማድረግህ ችግሩን ይበልጥ ከማባባስ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም።

ወደ አምላክ ጸልይ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል” ይላል። (መዝሙር 55:22) ወደ አምላክ የምንጸልየው ሐዘናችን ቀለል እንዲለን ለማድረግ ስንል ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጸሎት “በሚደርስብን መከራ ሁሉ” ከሚያጽናናን አምላክ ጋር መነጋገር የምንችልበት መንገድ ነው።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

አምላክ ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ያጽናናቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ስለሚገኙበት ሁኔታና ስለ ትንሣኤ ተስፋ ምን እንደሚያስተምር ለምን አትመረምርም? *የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ መዝሙር 94:19

^ አን.4 የዳሚን፣ የዴሪክንና የጂኒን ተሞክሮ በቀጣዩ ርዕስ ላይ ማንበብ ትችላለህ።

^ አን.5 ይህ ርዕስ በዋነኝነት የሚያተኩረው በወላጅ ሞት ላይ ቢሆንም በውስጡ ያሉት ሐሳቦች ሌላ የቤተሰባችን አባል ወይም ጓደኛችን በሚሞትበት ጊዜም ይሠራሉ።

^ አን.19 ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1 የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 16 ተመልከት። መጽሐፉን ከwww.pr418.com/am ላይ በነፃ ማውረድ ይቻላል። የሕትመት ውጤቶች በሚለው ሥር ተመልከት።