በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆች ሐዘን ሲደርስባቸው

ልጆች ሐዘን ሲደርስባቸው

የቤተሰብህን አባል በሞት በማጣትህ ምክንያት በሐዘን ተውጠሃል? ከሆነ የደረሰብህን ሐዘን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ሐዘን የደረሰባቸውን ሦስት ወጣቶች እንዴት እንደረዳቸው እስቲ እንመልከት።

የዳሚ ታሪክ

ዳሚ

መጀመሪያ ላይ፣ አባቴን ያመመው ቀላል ራስ ምታት መስሎን ነበር። ሕመሙ እየባሰበት ሲሄድ ግን እናቴ አምቡላንስ ጠራች። አምቡላንሱ መጥቶ ሲወስደው የነበረው ሁኔታ እስካሁን ድረስ ከአእምሮዬ አልጠፋም። በዚያን ጊዜ አባቴን ዳግመኛ እንደማላየው አላወቅኩም ነበር። ከሦስት ቀን በኋላ አባቴ ከደም ቧንቧ ጋር በተያያዘ በሽታ ሕይወቱ አለፈ። በወቅቱ ገና የስድስት ዓመት ልጅ ነበርኩ።

ለአባቴ ሞት ተጠያቂ የሆንኩት እኔ እንደሆንኩ በማሰብ ለበርካታ ዓመታት ራሴን ስወቅስ ኖሬያለሁ። አባቴን ወደ አምቡላንሱ ሲያስገቡት የነበረው ሁኔታ በተደጋጋሚ ወደ አእምሮዬ ይመጣል፤ ‘ለምን ዝም ብዬ ቆምኩ? ለምን የሆነ ነገር አላደረግኩም?’ እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። የጤና ችግር ያለባቸውን በዕድሜ የገፉ ሰዎች ሳይ ‘እነሱ እንኳ በሕይወት እያሉ አባቴ የሞተው ለምንድን ነው?’ እያልኩ አስባለሁ። ከጊዜ በኋላ እናቴ ስሜቴን አውጥቼ እንድናገር ረዳችኝ። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ጉባኤውም ትልቅ ድጋፍ አድርጎልናል።

አንዳንድ ሰዎች አሳዛኝ ነገር ሲያጋጥምህ ወዲያው እንደምታዝን ከዚያም ሐዘኑ እንደሚወጣልህ ያስባሉ፤ የእኔ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነበር። ሐዘኑ ይበልጥ እየተሰማኝ የመጣው አሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ስደርስ ነው።

ወላጃቸውን በሞት ላጡ ወጣቶች የሚከተለውን ምክር መስጠት እፈልጋለሁ፦ “ለሌላ ሰው ስሜታችሁን አውጥታችሁ ተናገሩ። ቶሎ ብላችሁ ስሜታችሁን አውጥታችሁ መናገራችሁ በተሻለ ፍጥነት እንድትጽናኑ ሊረዳችሁ ይችላል።”

እርግጥ በሕይወቴ ውስጥ በሚያጋጥሙኝ አንዳንድ ትላልቅ ክንውኖች ላይ አባቴ ከጎኔ አለመኖሩን ሳስብ በጣም ይሰማኛል። ሆኖም በራእይ 21:4 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ያጽናናኛል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”

የዴሪክ ታሪክ

ዴሪክ

ስለ አባቴ ካሉኝ ጥሩ ትዝታዎች መካከል አብረን ዓሣ ያጠመድንባቸው እንዲሁም ተራራ ላይ ወጥተን ድንኳን ውስጥ ያደርንባቸው ጊዜያት ይገኙበታል። አባቴ ለተራሮች ልዩ ፍቅር ነበረው።

አባቴ የልብ ሕመም ነበረበት፤ ልጅ ሳለሁ አንዴ ወይም ሁለቴ ሆስፒታል ሄጄ እንደጠየቅኩት ትዝ ይለኛል። ሆኖም ሕመሙ ያን ያህል ከባድ መሆኑን አላወቅኩም ነበር። የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ በልብ ሕመም ሕይወቱ አለፈ።

አባቴ ሲሞት በጣም እንዳለቀስኩ አስታውሳለሁ። ትንፋሽ እንዳጠረኝ ሆኖ ይሰማኝ ነበር፤ እንዲሁም ከማንም ሰው ጋር ማውራት አስጠላኝ። በሕይወቴ እንደዚያ አዝኜ አላውቅም፤ ምንም ነገር የማድረግ ፍላጎት አልነበረኝም። የነበርኩበት ቤተ ክርስቲያን የወጣቶች ቡድን አባላት መጀመሪያ ላይ እየመጡ ይጠይቁኝ የነበረ ቢሆንም ቀስ በቀስ መምጣታቸውን አቆሙ። አንዳንዶቹ “አባትህ ቀኑ ደርሶ ነው” እንዲሁም “አምላክ ጠርቶት ነው” ይሉኝ ነበር፤ “አባትህ አሁን ያለው በሰማይ ነው” የሚሉኝ ሰዎችም ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚያስተምር የማውቀው ነገር ባይኖርም ሰዎቹ የሚናገሩት ነገር አልተዋጠልኝም ነበር።

ከዚያም እናቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ጀመረች፤ በኋላ ላይ እኔና ወንድሜም መጽሐፍ ቅዱስን መማር ጀመርን። ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ እንዲሁም አምላክ ስለሰጠውና አጽናኝ ስለሆነው የትንሣኤ ተስፋ ተማርን። (ዮሐንስ 5:28, 29) በጣም የረዳኝ በኢሳይያስ 41:10 ላይ የሚገኘው አምላክ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ ነው፦ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ። እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ።” ይሖዋ አብሮኝ እንዳለ ማወቄ ሐዘን በደረሰብኝ ወቅት በጣም አጽናንቶኛል፤ አሁንም እያጽናናኝ ነው።

የጂኒ ታሪክ

ጂኒ

የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ በካንሰር ሞተች። በዚያን ዕለት የተከናወኑትን ነገሮች ሳስብ ሕልም ሕልም ይመስለኛል። እናቴ የሞተችው ቤት ውስጥ ነበር፤ አያቶቼም አብረውን ነበሩ። ሁሉም ሰው ጸጥ ብሎ እንደነበር አስታውሳለሁ። ራት የበላነው እንቁላል ፍርፍር ነበር። በአንድ ጊዜ ሕይወቴ በሙሉ እንደተመሰቃቀለ ተሰማኝ።

ለታናሽ እህቴ ስል ጠንካራ መሆን እንዳለብኝ ስለተሰማኝ በዚያን ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ስሜቴን አፍኜ ለመያዝ ተገደድኩ። አሁንም ድረስ የሚያሳዝን ነገር ሲያጋጥመኝ ስሜቴን አፍኜ ለመያዝ እሞክራለሁ፤ ይህ ደግሞ ጎጂ ነው።

በአካባቢው የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ያሳየንን ፍቅርና ያደረገልንን ድጋፍ መቼም ቢሆን አልረሳውም። በወቅቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብ ከጀመርን ብዙም ያልቆየን ቢሆንም የእምነት ባልንጀሮቻችን ለዓመታት እንደሚተዋወቅ ቤተሰብ ከጎናችን አልተለዩም። አባቴ ለአንድ ዓመት ያህል ራት መሥራት አላስፈለገውም ነበር፤ ምክንያቱም ወንድሞችና እህቶች ሁልጊዜ ምግብ ይዘውልን ይመጡ ነበር።

በጣም የምወደው ጥቅስ መዝሙር 25:16, 17 ነው። በዚህ ጥቅስ ላይ መዝሙራዊው አምላክን እንደሚከተለው በማለት ለምኗል፦ “ብቸኛና ምስኪን ስለሆንኩ ፊትህን ወደ እኔ መልስ፤ ቸርነትም አሳየኝ። የልቤ ጭንቀት በዝቷል፤ ከሥቃዬ ገላግለኝ።” በሐዘን በምንዋጥበት ጊዜ ብቻችንን እንዳልሆንን ማወቄ አጽናንቶኛል። አምላክ ምንጊዜም ከጎናችን ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኘሁት እርዳታ መጽናናትና እንደ ትንሣኤ ተስፋ ባሉ አዎንታዊ የሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር ችያለሁ። እናቴን ገነት በሆነች ምድር ላይ ሙሉ በሙሉ ጤናማ ሆና የማግኘት ተስፋ አለኝ።—2 ጴጥሮስ 3:13

መጽሐፍ ቅዱስ ሐዘን ለደረሰባቸው ሰዎች ስለሚሰጠው አጽናኝ መልእክት ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? “የምትወዱት ሰው ሲሞት” የተባለውን ብሮሹር በነፃ አውርድ። www.pr418.com/am ላይ የሕትመት ውጤቶች > መጻሕፍትና ብሮሹሮች በሚለው ሥር ይገኛል።