በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትዳር አጋርሽ ፖርኖግራፊ የሚመለከት ከሆነ

የትዳር አጋርሽ ፖርኖግራፊ የሚመለከት ከሆነ
  • “ባለቤቴ በተደጋጋሚ ምንዝር የፈጸመ ያህል ሆኖ ተሰማኝ።”

  • “እንደተዋረድኩ፣ ቆንጆ እንዳልሆንኩና ዋጋ እንደሌለኝ ተሰማኝ።”

  • “ስለ ጉዳዩ ማንንም ማነጋገር አልቻልኩም። ብቻዬን ተሠቃየሁ።”

  • “ይሖዋ እንደማያስብልኝ ሆኖ ተሰማኝ።”

ከላይ ያሉት ሐሳቦች አንድ ባል ፖርኖግራፊ የሚመለከት ከሆነ ሚስቱ ምን ያህል እንደምትሠቃይ ያሳያሉ። ለወራት ወይም ለዓመታት በድብቅ ይህን ሲያደርግ ከቆየ ደግሞ ጨርሶ ልታምነው እንደማትችል ሊሰማት ይችላል። አንዲት ሚስት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴን ጨርሶ እንደማላውቀው ሆኖ ተሰማኝ። ‘ሌሎች ነገሮችንስ ደብቆኝ ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ።”

ይህ ርዕስ የተዘጋጀው ፖርኖግራፊ የሚመለከት ባል ላላቸው ሚስቶች ነው። a ይህ ርዕስ እነዚህን ሚስቶች የሚያጽናኑ፣ የይሖዋ ድጋፍ እንደማይለያቸው የሚያረጋግጡ እንዲሁም በመንፈሳዊም ሆነ በስሜታዊ እንዲያገግሙ የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። b

ተበዳይዋ ሚስት ምን ማድረግ ትችላለች?

ባለቤትሽ የሚያደርጋቸውን ነገሮች በሙሉ መቆጣጠር ባትችዪም ሥቃይሽን ለመቀነስና የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ማድረግ የምትችያቸው ነገሮች አሉ። የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በዪ፦

ራስሽን አትውቀሺ። አንዲት ሚስት ባለቤቷ ፖርኖግራፊ ማየቱ የእሷ ጥፋት እንደሆነ ሊሰማት ይችላል። አሊስ c ባለቤቷ ፖርኖግራፊ የሚመለከተው እሷ ቆንጆ ባለመሆኗ ምክንያት እንደሆነ ተሰምቷት ነበር። ‘ባሌ እኔ እያለሁ ሌሎች ሴቶችን የሚመለከተው ለምንድን ነው?’ ብላ አሰበች። አንዳንድ ሚስቶች ደግሞ ለችግሩ መባባስ ተጠያቂዎቹ እነሱ እንደሆኑ በማሰብ ራሳቸውን ይወቅሳሉ። ዳንዬል እንዲህ ብላለች፦ “ቁጣዬን መቆጣጠር ባለመቻሌ ምክንያት ትዳራችንን እያፈረስኩ እንዳለሁ ተሰማኝ።”

አንቺም እንዲህ የሚሰማሽ ከሆነ ይሖዋ ለባለቤትሽ ድርጊት ተጠያቂ እንደማያደርግሽ አስታውሺ። ያዕቆብ 1:14 “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል” ይላል። (ሮም 14:12፤ ፊልጵ. 2:12) ይሖዋ አንቺን አይወቅስሽም፤ እንዲያውም ለእሱ ያለሽን ታማኝነት ከፍ አድርጎ ይመለከታል።—2 ዜና 16:9

በተጨማሪም አንድ ባል ፖርኖግራፊ መመልከቱ ሚስቱ የጎደላት ነገር እንዳለ የሚጠቁም እንዳልሆነ ማስታወስ ይገባል። ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ፖርኖግራፊ የትኛዋም ሴት ልታረካው የማትችል ተገቢ ያልሆነ የፆታ ምኞት ይፈጥራል።

ከልክ በላይ አትጨነቂ። ካትሪን በባለቤቷ የፖርኖግራፊ ልማድ ላይ ማውጠንጠኗ መላ ሕይወቷን እንደተቆጣጠረው ተናግራለች። ፍራንሲስ እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ የት እንዳለ በማላውቅበት ጊዜ ሁሉ ስጋት ያድርብኛል። ቀኑን ሙሉ ስሳቀቅ ነው የምውለው።” ሌሎች ሚስቶች ደግሞ የባላቸውን ችግር ከሚያውቁ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ሲሆኑ እንደሚሸማቀቁ ገልጸዋል። ያሉበትን ሁኔታ ማንም ስለማይረዳላቸው ብቸኝነት እንደሚሰማቸው የገለጹ ሚስቶችም አሉ።

እነዚህ ስሜቶች ተፈጥሯዊ ናቸው። ሆኖም በእነዚህ ስሜቶች ላይ ማተኮርሽ ጭንቀትሽን ከመጨመር በቀር የሚጠቅምሽ ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ ከይሖዋ ጋር ባለሽ ዝምድና ላይ ለማተኮር ሞክሪ። እንዲህ ማድረግሽ ውስጣዊ ጥንካሬ ለማዳበር ይረዳሻል።—መዝ. 62:2፤ ኤፌ. 6:10

መጽሐፍ ቅዱስ በጭንቀት በተዋጡበት ጊዜ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ማጽናኛ ያገኙ ሴቶችን ታሪክ ይዟል። የእነሱን ታሪክ ማንበብሽና ማሰላሰልሽ ሊጠቅምሽ ይችላል። ይሖዋ የአንዳንዶቹን ሴቶች ችግር ሙሉ በሙሉ አልቀረፈላቸውም፤ ሆኖም ውስጣዊ ሰላም ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ ሐና ባጋጠማት ችግር የተነሳ “በጣም ተማርራ ነበር።” ነገር ግን “በይሖዋ ፊት ለረጅም ሰዓት ስትጸልይ” ከቆየች በኋላ ችግሯ መፍትሔ ማግኘት አለማግኘቱን ባታውቅም ሰላም አግኝታለች።—1 ሳሙ. 1:10, 12, 18፤ 2 ቆሮ. 1:3, 4

ባልየውም ሆነ ሚስትየዋ የሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቅ ሊያስፈልጋቸው ይችላል

የጉባኤ ሽማግሌዎችን እርዳታ ጠይቂ። “ከነፋስ እንደ መከለያ፣ ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ” ሊሆኑልሽ ይችላሉ። (ኢሳ. 32:2) እንዲሁም ሚስጥርሽን ልታካፍያትና ልታጽናናሽ የምትችል እህት ሊጠቁሙሽ ይችላሉ።—ምሳሌ 17:17

ልትረጂው ትችዪ ይሆን?

ባለቤትሽ ፖርኖግራፊ የመመልከት ልማዱን እንዲያሸንፍ ልትረጂው ትችዪ ይሆን? ምናልባት። መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ችግር ከመፍታት ወይም አንድን ኃያል ጠላት ከማሸነፍ ጋር በተያያዘ “አንድ ከመሆን ሁለት መሆን [እንደሚሻል]” ይገልጻል። (መክ. 4:9-12) ጥናቶች እንደሚያሳዩት ባለትዳሮች ተባብረው መሥራታቸው ባልየው የፖርኖግራፊ ሱሱን እንዲያሸንፍና በመካከላቸው ያለው መተማመን እንዲታደስ ሊረዳቸው ይችላል።

እርግጥ ነው የሚገኘው ውጤት በዋነኝነት የተመካው የትዳር ጓደኛሽ የፖርኖግራፊ ሱሱን ለማሸነፍ ባለው ቁርጠኝነትና ልባዊ ፍላጎት ላይ ነው። ይሖዋ ጥንካሬ እንዲሰጠው ምልጃ አቅርቧል? ሽማግሌዎች እንዲረዱትስ ጠይቋል? (2 ቆሮ. 4:7፤ ያዕ. 5:14, 15) ወደ ፈተና እንዳይገባ የሚያደርጉትን ዘዴዎች ቀይሷል? ለምሳሌ በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አጠቃቀሙ ረገድ ገደብ አበጅቷል? ፍላጎቱ እንዲቀሰቀስበት ከሚያደርጉ ሁኔታዎችስ ይርቃል? (ምሳሌ 27:12) የአንቺን እርዳታ ለመቀበልና ሁሉንም ነገር ለአንቺ በሐቀኝነት ለመናገር ፈቃደኛ ነው? ከሆነ ልትረጂው ትችዪ ይሆናል።

እንዴት? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። የፌሊሲያ ባል ኤታን በልጅነቱ ፖርኖግራፊ የመመልከት ሱስ ያዘው። ፌሊሲያ ባሏ ፖርኖግራፊ የመመልከት ፍላጎቱ ሲያገረሽበት እሷን ማናገር ቀላል እንዲሆንለት ታደርጋለች። ኤታን እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴን በግልጽና በሐቀኝነት አነጋግራታለሁ። ከሚፈትኑኝ ሁኔታዎች እንድርቅ በፍቅር ትረዳኛለች። እንዲሁም ያለሁበትን ሁኔታ ትከታተላለች። በኢንተርኔት አጠቃቀሜም ላይ ገደብ እንዳበጅ ትረዳኛለች።” ኤታን ፖርኖግራፊ የመመልከት ፍላጎት ያለው መሆኑ የፌሊሲያን ስሜት እንደሚጎዳው ጥያቄ የለውም። ያም ቢሆን እንዲህ ብላለች፦ “መበሳጨቴና ማዘኔ ከሱሱ እንዲላቀቅ አያግዘውም። በመጀመሪያ ተነጋግረን የእሱን ችግር ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን። ከዚያም ባለቤቴ ጉዳዩ ካደረሰብኝ የስሜት ሥቃይ እንዳገግም ይረዳኛል።”

እንዲህ ያለውን ውይይት ማድረጋቸው ባልየው ከፖርኖግራፊ ሱሱ እንዲላቀቅ ብቻ ሳይሆን ሚስትየው በድጋሚ እሱን ማመን እንድትጀምርም ሊረዳት ይችላል። ደግሞም ባልየው ስለሚያጋጥመው ፈተና፣ ስለ ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው እንዲሁም ስለሚውልበት ቦታ ለሚስቱ ለመናገር ፈቃደኛ ከሆነ ምንም የሚደብቃት ነገር እንደሌለ ስለምታውቅ እሱን ማመን ቀላል ይሆንላታል።

አንቺስ ባልሽን በተመሳሳይ መንገድ መርዳት የምትችዪ ይመስልሻል? ከሆነ ይህን ርዕስ አንድ ላይ አንብባችሁ ለምን አትወያዩበትም? የእሱ ግብ የፖርኖግራፊ ልማዱን ማሸነፍና መልሰሽ እንድታምኚው የሚያደርግ መሠረት መጣል መሆን አለበት። ይህን ጉዳይ አንስተሽ ለመወያየት በመፈለግሽ ከመበሳጨት ይልቅ ችግሩ በአንቺ ላይ ምን ተጽዕኖ እያሳደረ እንዳለ ለመረዳት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። የአንቺ ግብ ደግሞ ልማዱን ለማሸነፍ ጥረት ሲያደርግ እሱን መደገፍና እምነት የሚጣልበት መሆኑን እንዲያስመሠክር አጋጣሚ መስጠት መሆን አለበት። ሁለታችሁም፣ ሰዎች ወደ ፖርኖግራፊ ወጥመድ እንዲገቡ የሚያደርጋቸው ምክንያት ምን እንደሆነና ይህን ችግር ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ መማር ይኖርባችኋል። d

ውይይታችሁ ወደ ጭቅጭቅ ሊያመራ እንደሚችል ከተሰማችሁ ሁለታችሁም የምታምኑት አንድ ሽማግሌ ለተወሰነ ጊዜ ያህል አብሯችሁ ሆኖ እንዲያወያያችሁ ልትጋብዙ ትችላላችሁ። የትዳር ጓደኛሽ የፖርኖግራፊ ሱሱን ካሸነፈ በኋላም እንኳ በእሱ ላይ መልሰሽ እምነት ለመገንባት የተወሰነ ጊዜ ሊወስድብሽ እንደሚችል አትዘንጊ። ተስፋ አትቁረጪ! ግንኙነታችሁ እየተሻሻለ እንደሆነ የሚጠቁሙ ትናንሽ ምልክቶችን ለማስተዋል ሞክሪ። ጊዜና ትዕግሥት ቢጠይቅም ትዳራችሁ እንደገና መጠናከር እንደሚችል ተስፋ ማድረግ ትችያለሽ።—መክ. 7:8፤ 1 ቆሮ. 13:4

ችግሩ ባይፈታስ?

ባለቤትሽ ችግሩ ቢያገረሽበት ንስሐ አልገባም ወይም ሁኔታው ተስፋ የለውም ማለት ነው? ላይሆን ይችላል። በተለይ ፖርኖግራፊ ሱስ ከሆነበት የዕድሜ ልክ ትግል ማድረግ ሊጠይቅበት ይችላል። ከፖርኖግራፊ ርቆ ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላም ችግሩ ሊያገረሽበት ይችላል። ወደፊት እንዲህ ያለ ችግር እንዳያጋጥመው ጠንከር ያሉ ገደቦችን መጣል ሊያስፈልገው ይችላል። ምናልባትም ችግሩን እንዳሸነፈው ከተሰማው በኋላም ራሱን ለመቆጣጠር የሚወስዳቸውን እርምጃዎች መቀጠል ሊኖርበት ይችላል። (ምሳሌ 28:14፤ ማቴ. 5:29፤ 1 ቆሮ. 10:12) ‘አእምሮውን የሚያሠራውን ኃይል ማደስ’ እንዲሁም ፖርኖግራፊንና እንደ ማስተርቤሽን ያሉ ተያያዥ ርኩስ ልማዶችን ጨምሮ ‘ክፉ የሆነውን ነገር መጥላትን’ መማር አለበት። (ኤፌ. 4:23፤ መዝ. 97:10፤ ሮም 12:9) እንዲህ ያለውን ጥረት ለማድረግ ፈቃደኛ ነው? ከሆነ ሁኔታው አሁንም ተስፋ ሊኖረው ይችላል። e

ከይሖዋ ጋር ባለሽ ዝምድና ላይ አተኩሪ

ይሁንና ባለቤትሽ ይህን ችግር ለመዋጋት ምንም ፍላጎት ባያሳይስ? የተስፋ መቁረጥ፣ የብስጭት ወይም የመከዳት ስሜት በተደጋጋሚ ሊሰማሽ ይችላል። ጉዳዩን ለይሖዋ በመተው ውስጣዊ ሰላምሽን ለመጠበቅ ጥረት አድርጊ። (1 ጴጥ. 5:7) በማጥናት፣ በመጸለይና በማሰላሰል ወደ ይሖዋ መቅረብሽን ቀጥዪ። ይህን ስታደርጊ እሱም ወደ አንቺ እንደሚቀርብ ተማመኚ። ኢሳይያስ 57:15 እንደሚገልጸው ይሖዋ “የተሰበረ ልብ ካለውና መንፈሱ ከተደቆሰው ጋር” ይኖራል። ደስታቸውን መልሰው እንዲያገኙም ይረዳቸዋል። አቅምሽ በፈቀደው መጠን ጥሩ ክርስቲያን ለመሆን ጥረት አድርጊ። ሽማግሌዎች እንዲረዱሽ ጠይቂ። እንዲሁም ባለቤትሽ ወደፊት ለውጥ ለማድረግ ሊነሳሳ እንደሚችል ተስፋ አድርጊ።—ሮም 2:4፤ 2 ጴጥ. 3:9

a ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በዚህ ርዕስ ውስጥ የምናተኩረው ፖርኖግራፊ የሚመለከት ባል ባላቸው ሚስቶች ላይ ነው። ሆኖም ብዙዎቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ፖርኖግራፊ የምትመለከት ሚስት ላላቸው ባሎችም ጠቃሚ ናቸው።

b ፖርኖግራፊ መመልከት ቅዱስ ጽሑፋዊ ፍቺ ለመፈጸም መሠረት አይሆንም።—ማቴ. 19:9

c ስሞቹ ተቀይረዋል።

d በ​jw.org እና በጽሑፎቻችን ላይ ጠቃሚ ምክር ማግኘት ይቻላል። ለምሳሌ jw.org ላይ የሚገኘውን “ፖርኖግራፊ ትዳራችሁን ሊያናጋው ይችላል” የሚለውን ርዕስ፣ በሚያዝያ 1, 2014 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 10-12 ላይ የሚገኘውን “ፈታኝ ስሜቶችን ማሸነፍ ትችላለህ!” የሚለውን ርዕስ እንዲሁም በነሐሴ 1, 2013 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 3-7 ላይ የሚገኘውን “የብልግና ምስሎች—ጎጂ ናቸው?” የሚል ርዕስ መመልከት ትችላላችሁ።

e ፖርኖግራፊ በባሕርይው ሱስ የሚያስይዝ ስለሆነ አንዳንድ ባለትዳሮች ሽማግሌዎች ከሚሰጡት መንፈሳዊ እረኝነት በተጨማሪ የባለሙያ እገዛ ለማግኘት የግል ውሳኔ አድርገዋል።