በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትዳር ጓደኛ ክህደት ሲፈጽም

የትዳር ጓደኛ ክህደት ሲፈጽም

“ባለቤቴ ከእኔ በዕድሜ የምታንስ ሴት ስላፈቀረ ጥሎኝ እንደሚሄድ ሲነግረኝ ሞቴን ተመኝቼ ነበር። ለእሱ ስል የከፈልኳቸውን መሥዋዕቶች ሳስብ ደግሞ ክህደቱ ይባስ አንገበገበኝ።”—ማሪያ፣ ስፔን

“ባለቤቴ በድንገት ጥላኝ ስትሄድ፣ አንድ የሰውነቴ ክፍል ተቆርጦ የሄደ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። ሕልማችን፣ ተስፋችንና ዕቅዳችን ሁሉ በኖ ጠፋ። አንዳንድ ጊዜ ጭንቀቱ ለቆኛል ብዬ ሳስብ ራሴን መልሼ እዚያው የጭንቀት አዘቅት ውስጥ አገኘዋለሁ።”—ቢል፣ ስፔን

የትዳር ጓደኛ ክህደት፣ ስሜትን ክፉኛ የሚጎዳ ነገር ነው። እርግጥ ነው፣ ክህደት የተፈጸመባቸው አንዳንድ ባለትዳሮች በድርጊቱ የተጸጸተውን የትዳር ጓደኛቸውን ይቅር ማለትና ግንኙነታቸውን ማደስ ችለዋል። * ሆኖም እንዲህ ያለ በደል የተፈጸመባቸው ባለትዳሮች፣ በትዳሩ አብረው ለመቀጠል ወሰኑም አልወሰኑ ከባድ የስሜት ሥቃይ እንደሚደርስባቸው የታወቀ ነው። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ከደረሰባቸው የስሜት ስብራት ማገገም የሚችሉት እንዴት ነው?

ሊረዱህ የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች

ክህደት የተፈጸመባቸው በርካታ ባለትዳሮች ከባድ ሐዘን ቢደርስባቸውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማጽናኛ ማግኘት ችለዋል። አምላክ እንባቸውን እንደሚመለከትና ሐዘናቸውን እንደሚጋራ ተገንዝበዋል።—ሚልክያስ 2:13-16

“በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ።”መዝሙር 94:19

ቢል እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ይህን ጥቅስ ሳነብ ይሖዋ ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት በርኅራኄ ሲያረጋጋኝ በዓይነ ሕሊናዬ ይታየኛል።”

“ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ትሆናለህ።”መዝሙር 18:25

ባለቤቷ ለበርካታ ወራት ያህል ለትዳራቸው ታማኝ እንዳልነበረ ያወቀች ካርመን የተባለች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ በትዳራችን ላይ ክህደት ፈጽሟል። ይሖዋ ግን ምንጊዜም ታማኝ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ። እሱ መቼም ቢሆን እንደማያሳፍረኝ አውቃለሁ።”

“ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ . . . ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”ፊልጵስዩስ 4:6, 7

ሳሻ የተባለች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ይህን ጥቅስ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ። ወደ አምላክ አብዝቼ በጸለይኩ መጠን እሱ ይበልጥ ውስጣዊ ሰላም እንደሚሰጠኝ አስተውያለሁ።”

ከላይ የተጠቀሱት ግለሰቦች በሙሉ፣ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርገው መተው የፈለጉበት ጊዜ እንደነበር አይካድም። ሆኖም በይሖዋ አምላክ ላይ እምነት የጣሉ ከመሆኑም ሌላ ቃሉን ያነብቡ ነበር፤ ይህም ብርታት ሰጥቷቸዋል። ቢል እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል፦ “ሁሉ ነገር ያበቃለት በሚመስልበት ወቅት ለሕይወቴ ትርጉም የሰጠው እምነቴ ነው። ለተወሰነ ጊዜ ያህል ‘ድቅድቅ ጨለማ በዋጠው ሸለቆ ውስጥ ብሄድም’ አምላክ ከእኔ ጋር ነበር።”—መዝሙር 23:4

^ ክህደት የፈጸመን የትዳር ጓደኛ ይቅር ማለትን ወይም አለማለትን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት “የትዳር ጓደኛ ሲከዳ” የሚል ርዕስ ባለው በመስከረም 1999 ንቁ! ላይ የወጡትን ተከታታይ ርዕሶች ተመልከት።