በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ይሰማሃል?

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ይሰማሃል?

የዓለማችን ሁኔታ ምን የሚሆን ይመስልሃል?

  • ባለበት የሚቀጥል?

  • እየተባባሰ የሚሄድ?

  • ወይስ እየተሻሻለ የሚሄድ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:3, 4 አዲስ ዓለም ትርጉም

ይህን ማወቅህ ለአንተ ምን ጥቅም አለው?

ትርጉም ያለውና አርኪ ሥራ ይኖርሃል።—ኢሳይያስ 65:21-23

ከሕመምና ከመከራ ነፃ የሆነ ሕይወት ይኖርሃል።—ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24

ከቤተሰብህና ከወዳጆችህ ጋር ለዘላለም በደስታ ትኖራለህ።—መዝሙር 37:11, 29

መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ነገር ላይ እምነት መጣል እንችላለን?

አዎ፣ ቢያንስ ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፦

  • አምላክ የገባውን ቃል የመፈጸም ችሎታ አለው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሁሉን ቻይ” ተብሎ የተጠራው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም እሱ ገደብ የለሽ ኃይል አለው። (ራእይ 15:3) በመሆኑም ዓለማችንን እንደሚለውጥ የገባውን ቃል መፈጸም ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “በአምላክ ዘንድ . . . ሁሉ ነገር ይቻላል።”—ማቴዎስ 19:26

  • አምላክ የገባውን ቃል ለመፈጸም ፍላጎቱ አለው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት ‘ይናፍቃል።’—ኢዮብ 14:14, 15

በተጨማሪም የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ የታመሙትን እንደፈወሰ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ሰዎችን የመርዳት ፍላጎት ስላለው ነው። (ማርቆስ 1:40, 41) ኢየሱስ ችግር ላይ የወደቁትን የመርዳት ልባዊ ፍላጎት ያለው መሆኑ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ እንዳንጸባረቀ ያሳያል።—ዮሐንስ 5:19

በመሆኑም ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ የወደፊቱ ጊዜ አስደሳች እንዲሆንልን የሚፈልጉ መሆናቸውን እርግጠኞች መሆን እንችላለን! —መዝሙር 72:12-14፤ 145:16፤ 2 ጴጥሮስ 3:9

ምን ይመስልሃል?

አምላክ ዓለማችን የተሻለች እንድትሆን የሚያደርገው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ማቴዎስ 6:9, 10 እና ዳንኤል 2:44 ላይ ይገኛል።