የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

ምን ትላለህ?

  • ልባችን ውስጥ ያለ ነገር?

  • ምሳሌያዊ ነገር?

  • ወይስ በሰማይ ያለ መስተዳድር?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስ . . . መንግሥት ይመሠርታል።”—ዳንኤል 2:44 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

“ወንድ ልጅ ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። . . . ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም።”—ኢሳይያስ 9:6, 7

ይህን ማወቅህ ለአንተ ምን ጥቅም አለው?

  • በጽድቅ የሚገዛው ይህ መንግሥት በግለሰብ ደረጃ ለአንተ ብዙ ጥቅሞች ያስገኝልሃል።—ኢሳይያስ 48:17, 18

  • በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ ፍጹም ጤንነትና ደስታ ይኖርሃል።—ራእይ 21:3, 4

መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ነገር ላይ እምነት መጣል እንችላለን?

አዎ፣ ቢያንስ ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፦

  • ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ምን እንደሚያከናውን አሳይቷል። ኢየሱስ ‘መንግሥትህ ይምጣ፤ ፈቃድህ በምድር ይሁን’ ብለው እንዲጸልዩ ተከታዮቹን አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10) እንዲሁም ኢየሱስ ይህ ጸሎት መልስ በሚያገኝበት ጊዜ የሚኖረውን ሁኔታ አሳይቷል።

    ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ የተራቡትን መግቧል፤ የታመሙትን ፈውሷል፤ እንዲሁም የሞቱትን አስነስቷል! (ማቴዎስ 15:29-38፤ ዮሐንስ 11:38-44) በዚህ መንገድ፣ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በሚሆንበት ወቅት ለተገዢዎቹ የሚያመጣቸውን ግሩም በረከቶች በትንሹም ቢሆን አሳይቶ ነበር።—ራእይ 11:15

  • በዓለም ላይ የሚታዩት ሁኔታዎች የአምላክ መንግሥት የሚመጣበት ጊዜ መቅረቡን ያረጋግጣሉ። የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ ሰላምን ከማስፈኑ በፊት ዓለማችን በጦርነት፣ በረሃብና በምድር መናወጥ እንደሚጠቃ ኢየሱስ ትንቢት ተናግሯል።—ማቴ. 24:3, 7

    በዛሬው ጊዜ እነዚህ ክስተቶች ሲፈጸሙ እየተመለከትን ነው። በመሆኑም የአምላክ መንግሥት እነዚህን ችግሮች በሙሉ የሚያስወግድበት ጊዜ መቅረቡን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ምን ይመስልሃል?

በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምን ዓይነት ሕይወት ይኖረናል?

መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ መዝሙር 37:29 እና ኢሳይያስ 65:21-23 ላይ ይገኛል።