በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

“የምፈልገው ነገር በሙሉ ያለኝ ይመስለኝ ነበር”

“የምፈልገው ነገር በሙሉ ያለኝ ይመስለኝ ነበር”
  • የትውልድ ዘመን፦ 1962

  • የትውልድ አገር፦ ካናዳ

  • የኋላ ታሪክ፦ ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት ይመራ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ

 የተወለድኩት በካናዳ የምትገኘው የኩዊቤክ ግዛት ትልቋ ከተማ በሆነችው በሞንትሪያል ነው። አፍቃሪ ወላጆቻችን እኔን፣ እህቴንና ሁለት ወንድሞቼን ተንከባክበው ያሳደጉን ሲሆን ቤታችን ደስ በሚለው በሮዝሞንት አካባቢ ነበር። ሕይወታችን ሰላምን ደስታ የሰፈነበት ነበር።

 በልጅነቴ መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ፍላጎት ነበረኝ። የ12 ዓመት ልጅ እያለሁ ስለ ኢየሱስ ሕይወት ከአዲስ ኪዳን ላይ አነብ እንደነበር ትዝ ይለኛል፤ ታሪኩ በጣም ያስደስተኝ ነበር። ኢየሱስ ለሌሎች ያለው ፍቅርና ርኅራኄ በጣም ስለነካኝ እንደ እሱ መሆን እፈልግ ነበር። የሚያሳዝነው ግን እያደግኩ ስሄድ ከመጥፎ ልጆች ጋር ጓደኝነት ስለገጠምኩ ይህ ፍላጎቴ እየጠፋ መጣ።

 አባቴ የሳክስፎን ተጫዋች ሲሆን የሙዚቃ መሣሪያውን ብቻ ሳይሆን ለሙዚቃ ያለውን ከፍተኛ ፍቅርም አውርሶኝ ነበር። ሙዚቃ በጣም ስለምወድ ወዲያውኑ ጊታር መማር ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ከተወሰኑ ጓደኞቼ ጋር አንድ የሮክ ሙዚቃ ባንድ አቋቋምን። በተለያዩ ቦታዎች የሙዚቃ ዝግጅታችንን እናቀርብ ነበር። አንዳንድ ታዋቂ የሙዚቃ አሳታሚ ድርጅቶች ዓይን ውስጥ መግባት የቻልኩ ሲሆን አብሬያቸው እንድሠራም ጠይቀውኛል። በኋላም ከአንድ ትልቅ የሙዚቃ አሳታሚ ድርጅት ጋር ውል ፈረምኩ። የምጫወተው ሙዚቃ በጣም ተወዳጅነት ያተረፈ ሲሆን ኩዊቤክ ውስጥ ዘወትር በሬዲዮ ይተላለፍ ነበር።

 የምፈልገው ነገር በሙሉ ያለኝ ይመስለኝ ነበር። ወጣትና ዝነኛ ነበርኩ፤ ብዙ ገንዘብ ያለኝ ሲሆን የምሠራውም የምወደውን ሥራ ነው። ቀን ቀን ስፖርት እሠራለሁ፤ ቃለ መጠይቅ ይደረግልኛል፤ አድናቂዎቼ እንድፈርምላቸው ይጠይቁኛል፤ እንዲሁም ቴሌቪዥን ላይ እቀርባለሁ። ማታ ማታ ደግሞ የሙዚቃ ዝግጅቴን አቀርባለሁ እንዲሁም ግብዣዎች ላይ እገኛለሁ። አድናቂዎቼ ፊት ስቀርብ እንዳልፈራ አልኮል መጠጣት የጀመርኩት ገና በወጣትነቴ ነበር፤ ከዚያም ዕፅ መውሰድ ጀመርኩ። ግድ የለሽ ሆንኩ፤ በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ሕይወትም እመራ ነበር።

 ስታይ ደስተኛ ስለምመስል አንዳንዶች ይቀኑብኝ ነበር። እኔ ግን የባዶነት ስሜት ይሰማኝ ነበር፤ በተለይ ብቻዬን ስሆን ይህ ስሜት ያስቸግረኛል። በመንፈስ ጭንቀት እሠቃይ ነበር። የሚያሳዝነው ደግሞ ከፍተኛ ስኬት ላይ በደረስኩበት ወቅት፣ ሙዚቃዬን የሚያሳትሙልኝ ሁለት ሰዎች በኤድስ በሽታ ተይዘው ሞቱ። በጣም ደነገጥኩ። ሙዚቃ የምወድ ቢሆንም በዚህ ሥራ ምክንያት ለመምራት የተገደድኩትን ሕይወት በጣም እጠላው ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

 በሥራዬ ስኬታማ የነበርኩ ቢሆንም ይህ ዓለም በአስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አውቅ ነበር። ‘የፍትሕ መጓደል ይህን ያህል የበዛው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ነበረኝ። አምላክ እስካሁን እርምጃ ያልወሰደው ለምን እንደሆነ ግራ ይገባኝ ነበር። እንዲያውም ለእነዚህ ጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘት ወደ አምላክ ጸልዬ ነበር። ወደተለያየ ቦታ ከማደርገው ጉዞ እረፍት ሳገኝ መጽሐፍ ቅዱስን በድጋሚ ማንበብ ጀመርኩ። የማነበውን አብዛኛውን ነገር መረዳት ባልችልም የዚህ ዓለም መጨረሻ እንደቀረበ ካነበብኩት ነገር ተረዳሁ።

 መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ ኢየሱስ በአንድ ወቅት ምድረ በዳ ውስጥ ለ40 ቀናት እንደጾመ አወቅኩ። (ማቴዎስ 4:1, 2) ስለዚህ ‘እኔም እኮ እንዲህ ባደርግ አምላክ ራሱን ይገልጥልኝ ይሆናል’ ብዬ አሰብኩ፤ ከዚያም ጾም የምጀምርበትን ቀን ወሰንኩ። የምጾምበት ቀን ከመድረሱ ከሁለት ሳምንት በፊት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው በሬን አንኳኩ። እኔም ልክ ሲጠብቃቸው እንደነበረ ሰው ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዝኳቸው። ቤቴ ከመጡት የይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ዣክ ይባል ነበር፤ እኔም ዣክን ዓይኑን ትክ ብዬ እያየሁ “ያለነው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደሆነ እንዴት እናውቃለን?” ብዬ ጠየቅኩት። እሱም መጽሐፍ ቅዱሱን አውጥቶ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5ን አነበበልኝ። ከዚያም በርካታ ጥያቄዎች ጠየቅኳቸው፤ በሰጡኝ ምክንያታዊና አጥጋቢ መልስ በጣም ተደነቅኩ፤ ደግሞም መልሳቸው በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነበር። ለተወሰነ ቀናት ውይይት ካደረግን በኋላ መጾም እንደማያስፈልገኝ ተገነዘብኩ።

 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ማጥናት ጀመርኩ። ከጊዜ በኋላ ረጅሙን ፀጉሬን ተቆረጥኩ፤ እንዲሁም በአካባቢዬ በሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። ወደ ስብሰባ ስሄድ የተደረገልኝ ሞቅ ያለ አቀባበል እውነትን እንዳገኘሁ ይበልጥ አረጋገጠልኝ።

 እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና ያወቅኳቸውን ነገሮች በሥራ ላይ ለማዋል በሕይወቴ ውስጥ ትላልቅ ለውጦችን ማድረግ ነበረብኝ። ለምሳሌ ዕፅ ከመውሰድ መታቀብና ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗሬን እርግፍ አድርጌ መተው ነበረብኝ። በተጨማሪም ራስ ወዳድነትን ትቼ ለሌሎች ልባዊ አሳቢነት ማሳየትን መማር ያስፈልገኝ ነበር። ሁለቱን ልጆቼን የማሳድገው ለብቻዬ እንደመሆኑ መጠን የእነሱን ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት ነበረብኝ። ስለዚህ የሙዚቃ ሥራዬን በመተው በአንድ ፋብሪካ ውስጥ በአነስተኛ ክፍያ ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ።

 እነዚህን ለውጦች ማድረግ ቀላል አልነበረም። ዕፅ መውሰዴን ለማቆም ጥረት በማደርግበት ወቅት ዕፅ መውሰድ ከማቆም ጋር ተያይዞ የሚመጣ የስሜት ቀውስ አጋጥሞኝ ነበር፤ እንዲሁም ድጋሚ ዕፅ መውሰድ የጀመርኩባቸው ወቅቶች ነበሩ። (ሮም 7:19, 21-24) ከሁሉ በላይ የከበደኝ ግን የነበረኝን ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር መተው ነበር። በተጨማሪም አዲስ የጀመርኩት ሥራ በጣም አድካሚ ሲሆን የማገኘው ገቢ ደግሞ በጣም አነስተኛ ነው። በሙዚቃው ዓለም እያለሁ በሁለት ሰዓት ውስጥ የማገኘውን ገቢ ለማግኘት ሦስት ወራት መሥራት ያስፈልገኝ ነበር።

 እነዚህን አስቸጋሪ ለውጦች ለማድረግ ጸሎት በእጅጉ ረድቶኛል። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበቤም በጣም ጠቅሞኛል። በተለይ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በጣም አበረታተውኛል። አንደኛው ጥቅስ 2 ቆሮንቶስ 7:1 ሲሆን ክርስቲያኖች “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ [ራሳቸውን እንዲያነጹ]” ያበረታታል። ያሉብኝን መጥፎ ልማዶች ማስወገድ እንደምችል እርግጠኛ እንድሆን ያደረገኝ ሌላው ጥቅስ ደግሞ ፊልጵስዩስ 4:13 ሲሆን ጥቅሱ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ” ይላል። ይሖዋ ጸሎቴን ሰምቶ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዳውቅና ተግባራዊ ማድረግ እንድችል ረድቶኛል። (1 ጴጥሮስ 4:1, 2) በመጨረሻም በ1997 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

ያገኘሁት ጥቅም

 በበፊቱ አኗኗሬ ብቀጥል ኖሮ ዛሬ በሕይወት እንደማልገኝ እርግጠኛ ነኝ። አሁን ግን እውነተኛ ደስታ ያለው ሕይወት እየመራሁ ነው። ይሖዋ ኤልቪ የተባለች ግሩም ሚስት ሰጥቶኛል። እኔና ኤልቪ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በመሆን ለሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እናስተምራለን። ይህም ደስታና እርካታ እንድናገኝ አስችሎናል። ይሖዋ ወደ ራሱ ስለሳበኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ።—ዮሐንስ 6:44