በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ግልጽና አሳማኝ መልስ አስደነቀኝ

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ግልጽና አሳማኝ መልስ አስደነቀኝ
  • የትውልድ ዘመን: 1948

  • የትውልድ አገር: ሃንጋሪ

  • የኋላ ታሪክ: ለነበሩት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይጓጓ ነበር

የቀድሞ ሕይወቴ፦

የተወለድኩት ሴኬሽፌሄርቫር በምትባል ከ1,000 ዓመታት በላይ ረጅም ታሪክ ባላት የሃንጋሪ ከተማ ውስጥ ነው። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በከተማዋ ላይ ያደረሰው ውድመት አሁንም ድረስ ትዝ ይለኛል።

በሕፃንነቴ ያሳደጉኝ አያቶቼ ነበሩ። አያቶቼን በተለይም ሴት አያቴን ኤልሳቤትን እንዳስታውስ የሚያደርጉኝ ብዙ አስደሳች ትዝታዎች አሉኝ። አያቴ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረኝ ረድታኛለች። ከሦስት ዓመቴ ጀምሮ ሁልጊዜ ምሽት ላይ የጌታ ጸሎት እየተባለ የሚጠራውን ጸሎት ከእሷ ጋር እደግም ነበር። ያም ቢሆን የዚህን ጸሎት ትርጉም የተረዳሁት በ20ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ሳለሁ ነበር።

ወላጆቼ ቤት ለመግዛት የሚያስችላቸውን ገንዘብ ለማጠራቀም ሲሉ ቀን ከሌት ይለፉ ስለነበር በልጅነቴ ያሳደጉኝ አያቶቼ ናቸው። በየሁለት ሳምንቱ ቅዳሜ ላይ ግን መላው ቤተሰብ አንድ ላይ ተሰባስቦ ይመገብ ነበር። አብረን እናሳልፋቸው የነበሩት እነዚያ ጊዜያት በጣም ያስደስቱኝ ነበር።

በ1958 ወላጆቼ የራሳቸውን ቤት ሲገዙ ሕልማቸው እውን ሆነ። በመጨረሻ፣ ከወላጆቼ ጋር መኖር በመጀመሬ በጣም ተደሰትኩ! ከስድስት ወር በኋላ ግን ያ ደስታዬ በንኖ ጠፋ። አባቴ በካንሰር በሽታ ሞተ።

እጅግ አዘንኩ። እንዲህ እያልኩ እጸልይ እንደነበር አስታውሳለሁ፦ “አምላክ ሆይ፣ አባቴን እንድታድንልኝ ለምኜህ ነበር። አባቴ እንዲለየኝ አልፈልግም። ታዲያ ጸሎቴን ያልሰማኸኝ ለምንድን ነው?” አባቴ ያለበትን ቦታ ለማወቅ እጅግ ጓጉቼ ነበር። ‘ወደ ሰማይ ሄዶ ይሆን? ወይስ ከዚህ በኋላ ጨርሶ ዳግም በሕይወት የመኖር ተስፋ አይኖረውም?’ እያልኩ አስብ ነበር። አባት ባላቸው ልጆች እቀና ነበር።

ለብዙ ዓመታት፣ በየቀኑ ማለት ይቻላል አባቴ ወደተቀበረበት ቦታ እሄድ ነበር። ከዚያም በአባቴ መቃብር ላይ እንበረከክና “አምላክ ሆይ፣ እባክህ አባቴ ያለበትን ቦታ አሳውቀኝ” እያልኩ እጸልያለሁ። በተጨማሪም የሕይወትን ትርጉም ማወቅ እንድችል እንዲረዳኝ አምላክን እለምነው ነበር።

አሥራ ሦስት ዓመት ሲሆነኝ ጀርመንኛ ለመማር ወሰንኩ። ብዙ ጉዳዮችን በሚዳስሱት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጀርመንኛ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ ለጥያቄዎቼ መልስ ማግኘት እችል ይሆናል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። በ1967 በዬና ከተማ (በወቅቱ የምሥራቅ ጀርመን ክፍል ነበረች) ትምህርቴን መከታተል ጀመርኩ። የጀርመን ፈላስፎች የጻፏቸውን በተለይም ስለ ሕይወት ትርጉም የሚገልጹ መጻሕፍትን በጉጉት አነበብኩ። በእነዚህ መጻሕፍት ላይ አንዳንድ የሚገርሙ ሐሳቦችን ባገኝም አንዳቸውም ቢሆኑ ሙሉ በሙሉ የሚያረካ መልስ አልሰጡኝም። በመሆኑም ለጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘት መጸለዬን ቀጠልኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

በ1970 ወደ ሃንጋሪ ተመለስኩ፤ ከባለቤቴ ከሮዝ ጋር የተገናኘነው በዚህ ጊዜ ነበር። በወቅቱ ሃንጋሪ በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር ነበረች። እኔና ሮዝ ከተጋባን ብዙም ሳይቆይ ሸሽተን ወደ ኦስትሪያ ገባን። ይህን ያደረግነው አጎቴ ወደሚኖርበት ወደ ሲድኒ፣ አውስትራሊያ ለመሄድ ስላሰብን ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ኦስትሪያ ውስጥ ሥራ አገኘሁ። አንድ ቀን የሥራ ባልደረባዬ ለጥያቄዎቼ በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ ማግኘት እንደምችል ነገረኝ። ከዚያም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያብራሩ ሁለት መጻሕፍት ሰጠኝ። መጻሕፍቱን ወዲያውኑ አንብቤ የጨረስኳቸው ሲሆን ተጨማሪ ነገር ለማወቅ ፈለግሁ። በመሆኑም የመጻሕፍቱ አዘጋጆች ወደሆኑት ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ደብዳቤ በመጻፍ ተጨማሪ ጽሑፍ እንዲልኩልኝ ጠየቅሁ።

የጋብቻችንን የመጀመሪያ ዓመት ባከበርንበት ዕለት የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ ኦስትሪያዊ ወጣት ወደ ቤታችን መጣ። እሱም የጠየቅሁትን ጽሑፍ ያመጣልኝ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን አብሬው እንዳጠና ጋበዘኝ፤ እኔም ግብዣውን ተቀበልኩ። ከፍተኛ የማወቅ ጉጉት ስለነበረኝ በሳምንት ሁለት ጊዜ እናጠና ነበር፤ እያንዳንዱ የጥናት ፕሮግራምም አራት ሰዓት ይፈጅ ነበር!

የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያስተማሩኝ ነገር በጣም አስደሰተኝ። ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም በሃንጋሪኛ ቋንቋ በተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱሴ ላይ ሲያሳዩኝ ማመን አቃተኝ። ለ27 ዓመታት ቤተ ክርስቲያን እመላለስ የነበረ ቢሆንም አንድም ቀን የአምላክ ስም ሲጠቀስ ሰምቼ አላውቅም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄዎቼ የሰጠኝ ግልጽና አሳማኝ መልስ አስደነቀኝ። ለምሳሌ ያህል፣ የሞቱ ሰዎች ልክ በከባድ እንቅልፍ ላይ ያሉ ያህል ምንም እንደማያውቁ ተማርኩ። (መክብብ 9:5, 10፤ ዮሐንስ 11:11-15) በተጨማሪም ‘ሞት የማይኖርበት’ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ አወቅኩ። (ራእይ 21:3, 4) የሞቱ ሰዎች በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ ‘ስለሚነሱ’ አባቴን እንደገና እንደማየው ተስፋ አደርጋለሁ።—የሐዋርያት ሥራ 24:15

ባለቤቴ ሮዝም አብራኝ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። በጥናታችን ፈጣን እድገት ያደረግን ሲሆን በሁለት ወር ውስጥ የማስጠኛ መጽሐፉን አጥንተን ጨረስን! የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ዘወትር እንገኝ ነበር። በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ባየነው ፍቅር፣ መረዳዳትና አንድነት እጅግ ተደነቅን።—ዮሐንስ 13:34, 35

በ1976 እኔና ሮዝ ወደ አውስትራሊያ ለመግባት ፈቃድ አገኘን። እኛም ወዲያውኑ በዚያ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘን። እነሱም ሞቅ ባለ የወዳጅነት መንፈስ ተቀበሉን። በኋላም በ1978 የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን።

ያገኘሁት ጥቅም፦

ለረጅም ጊዜ ሲያሳስቡኝ ለነበሩት ጥያቄዎች መልስ አግኝቻለሁ። በተጨማሪም ወደ ይሖዋ አምላክ ስለቀረብኩ ከሁሉ የተሻለ አባት አለኝ። (ያዕቆብ 4:8) እንዲሁም ወላጅ አባቴን በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ እንደገና እንደማገኘው ተስፋ አደርጋለሁ፤ ይህ ለእኔ እጅግ ትልቅ ነገር ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29

በ1989 እኔና ሮዝ ወደ ሃንጋሪ ተመልሰን ለወዳጅ ዘመዶቻችን እንዲሁም ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ ስለ እምነታችን ለመናገር ወሰንን። መጽሐፍ ቅዱስን በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የማስተማር መብት አግኝተናል። መጽሐፍ ቅዱስን ካስተማርናቸው ሰዎች መካከል እናቴን ጨምሮ ከ70 የሚበልጡ ሰዎች አብረውን ይሖዋን እያገለገሉ ነው።

ለጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘት ለ17 ዓመታት ጸልያለሁ። ይህ ከሆነ 39 ዓመታት ቢያልፉም አሁንም መጸለዬን አላቆምኩም፤ አሁን የምጸልየው ግን “ውድ የሰማዩ አባቴ፣ የልጅነት ጸሎቴን ስለመለስክልኝ አመሰግንሃለሁ” ብዬ ነው።