በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በዓለም ዙሪያ ምን ያህል የይሖዋ ምሥክሮች አሉ?

በዓለም ዙሪያ ምን ያህል የይሖዋ ምሥክሮች አሉ?

2023 ሪፖርት

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ብዛት

8,816,562

ጉባኤዎች

118,177

የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩባቸው አገሮች

239

አጠቃላይ ድምር 2023

የአገር ወይም የግዛት ሪፖርት 2023

የይሖዋ ምሥክሮችን የምትቆጥሩት እንዴት ነው?

 አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር ተብሎ የሚቆጠረው በየወሩ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሚሰብክ ከሆነ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ይህም ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሰዎችን እንዲሁም ባይጠመቁም እንኳ በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ብቃቱን ያሟሉ ሰዎችን ያካትታል።

አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ገንዘብ ማዋጣት አለበት?

 በፍጹም። አንድ ሰው ገንዘብ ስላዋጣ ብቻ የይሖዋ ምሥክር ተደርጎ ሊቆጠር አሊያም በድርጅታችን ውስጥ አንድ ዓይነት ተልእኮ ወይም ኃላፊነት ሊሰጠው አይችልም። (የሐዋርያት ሥራ 8:18-20) እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ መዋጮ ያደረገው ማን እንደሆነ እንኳ አይታወቅም። እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር አቅሙ በፈቀደውና ልቡ ባነሳሳው መጠን ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን በመስጠት በዓለም ዙሪያ የሚከናወነውን ሥራ ይደግፋል።—2 ቆሮንቶስ 9:7

እየሰበኩ ያሉት ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑ የምታውቁት እንዴት ነው?

 የይሖዋ ምሥክሮች በየወሩ፣ ለሚሰበሰቡበት ጉባኤ የስብከት እንቅስቃሴያቸውን ሪፖርት ያደርጋሉ። ይህን ሪፖርት የሚያደርጉት በፈቃደኝነት ነው።

 የጉባኤዎች ሪፖርት በሚገባ ከተጠናቀረ በኋላ ድምሩ በዚያ አካባቢ ያለውን ሥራ ወደሚከታተለው ቅርንጫፍ ቢሮ ይላካል። ቅርንጫፍ ቢሮው ደግሞ የእያንዳንዱን አገር ወይም ክልል ድምር ወደ ዋናው ቢሯችን ይልካል።

 በእያንዳንዱ የአገልግሎት ዓመት a መጨረሻ ላይ፣ እያንዳንዱ አገር በዚያ ዓመት ያስመዘገበው ከፍተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ይወሰዳል። ከዚያም ይህን አኃዝ አንድ ላይ በመደመር በዓለም ዙሪያ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ስንት እንደሆነ ማወቅ ይቻላል። ከስብከቱ ሥራ የተገኙ ተሞክሮዎችን ጨምሮ የእያንዳንዱ አገር ዝርዝር ሪፖርት ድረ ገጻችን ላይ “በዓለም ዙሪያ” በሚለው ክፍል ሥር ይወጣል። ይህን የመሰሉ ሪፖርቶች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችን እንዳበረታቷቸው ሁሉ እኛንም ያበረታቱናል።—የሐዋርያት ሥራ 2:41፤ 4:4፤ 15:3

አብረዋችሁ የሚሰበሰቡ ሆኖም የማይሰብኩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክር ተብለው ይቆጠራሉ?

 እንዲህ ያሉ ሰዎችን የይሖዋ ምሥክር ብለን ባንቆጥራቸውም አብረውን ሲሰበሰቡ ደስ ይለናል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከተሰብሳቢዎች ቁጥር ላይ የይሖዋ ምሥክሮቹን ቁጥር በመቀነስ የእነዚህን ሰዎች ብዛት ከሞላ ጎደል ማወቅ ይቻላል። 2023 በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት ሰዎች ብዛት 20,461,767 ነበር።

 በስብሰባዎቻችን ላይ የማይገኙ በርካታ ሰዎችም እንኳ ከምንሰጠው ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይጠቀማሉ። 2023 በእያንዳንዱ ወር በአማካይ 7,281,212 የሚያክሉ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስተምረናል፤ በርከት ያሉ ሰዎችን አንድ ላይ የምናስተምርበት ጊዜም አለ።

መንግሥት የሚያወጣው የይሖዋ ምሥክሮች አኃዝ እናንተ ከምታወጡት አኃዝ የሚበልጠው ለምንድን ነው?

 የመንግሥት የሕዝብ ቆጠራ ቢሮዎች ይህን አኃዝ የሚወስኑት ሰዎችን የየትኛው ሃይማኖት አባል እንደሆኑ በመጠየቅ ነው። ለምሳሌ የዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ፣ የቆጠራው ውጤት የሚወሰነው ግለሰቦቹ የየትኛው ሃይማኖት ደጋፊ እንደሆኑ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ በሚሰጡት ምላሽ እንደሆነ ገልጿል። በመሆኑም ውጤቱ የሚያንጸባርቀው እውነታውን ሳይሆን የግለሰቦቹን አመለካከት እንደሆነ አመልክቷል። በተቃራኒው ግን እኛ አንድን ሰው የይሖዋ ምሥክር አድርገን የምንቆጥረው ራሱን የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ አድርጎ ስለቆጠረ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ለሌሎች የሚሰብክና ይህንንም ሪፖርት የሚያደርግ ከሆነ ብቻ ነው።

a የአገልግሎት ዓመት የሚባለው በአውሮፓውያን አቆጣጠር ከመስከረም 1 ጀምሮ በቀጣዩ የቀን መቁጠሪያ ዓመት እስከ ነሐሴ 31 ድረስ ያለው ጊዜ ነው። ለምሳሌ የ2015 የአገልግሎት ዓመት የሚባለው ከመስከረም 1, 2014 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 31, 2015 ድረስ ነው።