በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋ ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ ይሰጣሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋ ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ ይሰጣሉ?

 አዎ፣ የይሖዋ ምሥክሮች አብዛኛውን ጊዜ አደጋ ሲከሰት እርዳታ ይሰጣሉ። በገላትያ 6:10 ላይ ከሚገኘው መመሪያ ጋር በሚስማማ መልኩ ለይሖዋ ምሥክሮችም ሆነ የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ ሰዎች እርዳታ እንሰጣለን፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም ነገር እናድርግ።” በተጨማሪም ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ እንሰጣለን፤ ደግሞም የአደጋው ሰለባዎች በእነዚያ ወቅቶች በዋነኝነት የሚያስፈልጋቸውን እንዲህ ያለ እርዳታ ነው።​—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

አደረጃጀት

 በአንድ ቦታ አደጋ ሲደርስ በዚያ አካባቢ በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች አብረዋቸው የሚሰበሰቡ አባሎቻቸውን በሙሉ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህም ደኅንነታቸውን ለማረጋገጥና የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማወቅ ያስችላቸዋል። ከዚያም ሽማግሌዎቹ ያገኙትን ውጤትና የሰጡትን ፈጣን እርዳታ ለቅርንጫፍ ቢሮው ሪፖርት ያደርጋሉ።

 በአደጋ የተጎዱትን ለመርዳት የሚያስፈልጉትን ነገሮች በአካባቢው ያሉ ጉባኤዎች ማሟላት ካልቻሉ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት ዝግጅት ያደርጋል። ይህ ደግሞ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ረሃብ በተከሰተ ጊዜ አንዳቸው ሌላውን ለመርዳት ከተከተሉት መንገድ ጋር ተመሳሳይ ነው። (1 ቆሮንቶስ 16:1-4) አደጋ በደረሰበት አካባቢ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ የእርዳታ ሥራውን የሚያደራጁና የሚያስተባብሩ ኮሚቴዎችን ያቋቁማል። በሌላ አካባቢ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችም ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን መሥዋዕት በማድረግ በዚህ ሥራ በፈቃደኝነት ይተባበራሉ።​—ምሳሌ 17:17

የገንዘብ ድጋፍ

 ለይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች የሚላኩ መዋጮዎች የተለያዩ ነገሮችን ለማከናወን የሚውሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በአደጋ የተጎዱትን መርዳት ይገኝበታል። (የሐዋርያት ሥራ 11:27-30፤ 2 ቆሮንቶስ 8:13-15) በሥራው ላይ የሚካፈሉት የበጎ ፈቃድ ሠራተኖች ገንዘብ ስለማይከፈላቸው የሚዋጣው ገንዘቡ በሙሉ የሚውለው በአደጋው የተጠቁትን ሰዎች ለመርዳት ነው፤ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚወጣ ገንዘብ አይኖርም ማለት ነው። ሁሉንም የገንዘብ መዋጮዎችን የምንጠቀመው በጥንቃቄ ነው።​—2 ቆሮንቶስ 8:20