በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

“ጠላቶቻችሁን ውደዱ” ሲባል ምን ማለት ነው?

“ጠላቶቻችሁን ውደዱ” ሲባል ምን ማለት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ኢየሱስ ታዋቂ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ” ብሏል። (ማቴዎስ 5:44፤ ሉቃስ 6:27, 35) ይህም ሲባል የሚጠሉንን ወይም ግፍ የሚፈጽሙብንን ሰዎች በፍቅር መያዝ ይኖርብናል ማለት ነው።

 ኢየሱስ በደል ያደረሱበትን ሰዎች ይቅር በማለት ጠላቶቹን እንደሚወድ አሳይቷል። (ሉቃስ 23:33, 34) ጠላትን ስለመውደድ የሰጠው ምክር በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብለው በሚጠሩት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር ይስማማል።—ዘፀአት 23:4, 5፤ ምሳሌ 24:17፤ 25:21

 “ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ።”ማቴዎስ 5:43, 44

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 ጠላቶቻችንን መውደድ ያለብን ለምንድን ነው?

  •   አምላክ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። አምላክ “ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ደግ ነው።” (ሉቃስ 6:35) እሱ “በክፉዎች . . . ላይ ፀሐዩን ያወጣል።”—ማቴዎስ 5:45

  •   ፍቅር ማሳየታችን ጠላቶቻችን እንዲለወጡ ሊያነሳሳቸው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ጠላቶቻችንን በደግነት እንድንይዛቸው ይመክረናል፤ እንዲህ ካደረግን ‘በራሳቸው ላይ ፍም እንደምንከምር’ ይናገራል። (ምሳሌ 25:22) ይህ አገላለጽ ውድ የሆነ ማዕድንን በማቅለጥ ከቆሻሻው ለመለየት ከሚደረገው ሂደት ጋር የተያያዘ ነው። እኛም በተመሳሳይ ለሚጠሉን ሰዎች ደግነት የምናሳይ ከሆነ ቁጣቸው ቀልጦ እንዲወገድና መልካም ባሕርያቸው እንዲወጣ ማድረግ እንችል ይሆናል።

 ጠላቶቻችንን እንደምንወድ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

  •   “ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ።” (ሉቃስ 6:27) መጽሐፍ ቅዱስ “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው” ይላል። (ሮም 12:20) “ልክ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ እንደምትፈልጉት ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” የሚለውን ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ በማድረግ ለጠላቶቻችን ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸውን ሌሎች መንገዶችም ማግኘት እንችላለን።—ሉቃስ 6:31

  •   “የሚረግሟችሁን መርቁ።” (ሉቃስ 6:28) ጠላቶቻችን ክፉ ቃል ቢናገሩንም እነሱን በደግነትና በአሳቢነት በማነጋገር ‘የሚረግሙንን መመረቅ’ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ስድብን በስድብ አትመልሱ። ከዚህ ይልቅ ባርኩ” ይላል። (1 ጴጥሮስ 3:9) ይህ ምክር የጥላቻን ሰንሰለት ለመበጠስ ይረዳናል።

  •   “ለሚሰድቧችሁ ጸልዩ።” (ሉቃስ 6:28) አንድ ሰው ከሰደባችሁ “በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ።” (ሮም 12:17) ከዚህ ይልቅ አምላክ ግለሰቡን ይቅር እንዲለው ጸልዩ። (ሉቃስ 23:34፤ የሐዋርያት ሥራ 7:59, 60) ለመበቀል ከመሞከር ይልቅ አምላክ ፍጹም በሆነው የፍትሕ መሥፈርቱ መሠረት እንዲፈርድበት ጉዳዩን ለእሱ ተዉት።—ዘሌዋውያን 19:18፤ ሮም 12:19

 “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፤ እንዲሁም ለሚሰድቧችሁ ጸልዩ።” ሉቃስ 6:27, 28

  •   “ታጋሽና ደግ” ሁኑ። (1 ቆሮንቶስ 13:4) ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ፍቅር በሰጠው ታዋቂ ማብራሪያ ላይ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል (አጋፔ) በማቴዎስ 5:44 እና በሉቃስ 6:27, 35 ላይ ከሚገኙት ቃላት ጋር ተዛማጅነት አለው። ቅናተኛ፣ ትዕቢተኛና አክብሮት የለሽ ከመሆን ይልቅ ታጋሽና ደግ በመሆን ለጠላቶቻችንም ጭምር እንዲህ ያለ ክርስቲያናዊ ፍቅር እናሳያለን።

 “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም። ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም፣ ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም፣ በቀላሉ አይበሳጭም። ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም። ፍቅር በዓመፅ አይደሰትም፤ ከዚህ ይልቅ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል። ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል። ፍቅር ለዘላለም ይኖራል።”1 ቆሮንቶስ 13:4-8

 ከጠላቶቻችን ጋር መዋጋት ይኖርብናል?

 አይኖርብንም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ተከታዮቹ ከጠላቶቻቸው ጋር መዋጋት እንደሌለባቸው ተናግሯል። ለምሳሌ ኢየሩሳሌም ጥቃት እንደሚሰነዘርባት በነገራቸው ወቅት እዚያው ቆይተው እንዲዋጉ ሳይሆን እንዲሸሹ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 21:20, 21) በተጨማሪም ኢየሱስ ሐዋርያው ጴጥሮስን “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ብሎታል። (ማቴዎስ 26:52) መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ታሪክ እንደሚያሳዩት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ተከታዮች ከጠላቶቻቸው ጋር አይዋጉም ነበር። a2 ጢሞቴዎስ 2:24

 ሰዎች ጠላትን ስለመውደድ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ የአምላክ ሕግ፣ እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን እንዲጠሉ ያዝዝ ነበር።

 እውነታው፦ በሕጉ ውስጥ እንዲህ ያለ ትእዛዝ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ሕጉ እስራኤላውያን ባልንጀራቸውን እንዲወዱ ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 19:18) “ባልንጀራ” የሚለው ቃል ሁሉንም ሰው የሚያመለክት ቢሆንም አንዳንድ አይሁዳውያን “ባልንጀራ” የሚባሉት ሌሎች አይሁዳውያን ብቻ እንደሆኑ ያስቡ ነበር፤ እንዲሁም አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎችን እንደ ጠላት ይቆጥሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 5:43, 44) ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚገልጸውን ምሳሌ በመናገር የተሳሳተ አመለካከታቸውን አርሟል።—ሉቃስ 10:29-37

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ጠላቶቻችንን መውደድ ማለት የተሳሳተ ምግባራቸውን መደገፍ ማለት ነው።

 እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ሰው የሚፈጽመውን የተሳሳተ ምግባር ባንደግፍም ግለሰቡን መውደድ እንደምንችል ይጠቁማል። ለምሳሌ ኢየሱስ ዓመፅን ቢያወግዝም ለገደሉት ሰዎች ጸልዮላቸዋል። (ሉቃስ 23:34) በተጨማሪም ኃጢአትን ቢጠላም ለኃጢአተኞች ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል።—ዮሐንስ 3:16፤ ሮም 6:23

a በኧርነስት ዊሊያም ባርንስ የተዘጋጀው ዘ ራይዝ ኦቭ ክርስቲያኒቲ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “መረጃዎች ሁሉ በጥንቃቄ ሲመረመሩ እስከ ማርከስ ኦሪሊየስ ዘመነ መንግሥት ድረስ [ከ161 እስከ 180 ዓ.ም. የገዛው ሮማዊ ንጉሠ ነገሥት] ወታደር የሆነ ክርስቲያንና ክርስቲያን ከሆነ በኋላ በውትድርና አገልግሎት የቀጠለ ወታደር አልነበረም።”