በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የቃየን ሚስት ማን ነበረች?

የቃየን ሚስት ማን ነበረች?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ቃየን የሰው ዘር የመጀመሪያ ጥንዶች የሆኑት የአዳምና የሔዋን የበኩር ልጅ ሲሆን ከእህቶቹ መካከል አንዷን አሊያም የቅርብ ዘመዱ የሆነችን ሴት አግብቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቃየን እና ስለ ቤተሰቡ የሚናገረውን ዘገባ በመመርመር እንዲህ ያለ መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል።

ከቃየንና ከቤተሰቡ ጋር የተያያዙ እውነታዎች

  •   ሁሉም የሰው ልጆች የተገኙት በአዳምና በሔዋን በኩል ነው። አምላክ “በምድር ሁሉ ላይ [እንዲኖሩ] የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው [ከአዳም] ፈጠረ።” (የሐዋርያት ሥራ 17:26) የአዳም ሚስት ሔዋንም “የሕያዋን ሁሉ እናት” ሆነች። (ዘፍጥረት 3:20) በመሆኑም ቃየን ያገባው የአዳምና የሔዋን ዘር ከሆኑ ሴቶች መካከል አንዷን መሆን ይኖርበታል።

  •   ቃየንና ወንድሙ አቤል ሔዋን ከወለደቻቸው በርካታ ልጆች መካከል የመጀመሪያዎቹ ነበሩ። (ዘፍጥረት 4:1, 2) ቃየን ወንድሙን በመግደሉ ምክንያት ስደተኛ ሆኖ እንደሚኖር በተነገረው ጊዜ “ያገኘኝ ሁሉ ይገድለኛል” በማለት በምሬት ተናግሯል። (ዘፍጥረት 4:14) ቃየን የፈራው ማንን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አዳም “ወንዶችና ሴቶች ልጆችን” እንደወለደ ይናገራል። (ዘፍጥረት 5:4) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው የአዳምና የሔዋን ሌሎች ልጆች ለቃየን ሥጋት ሊሆኑበት ይችላሉ።

  •   በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ አካባቢ የቅርብ ዘመድን ማግባት የተለመደ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ታማኙ አብርሃም ያገባው የአባቱ ልጅ የሆነችውን እህቱን ነው። (ዘፍጥረት 20:12) ከቅርብ ዘመድ ጋር መጋባትን የሚከለክል ሕግ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው፣ ቃየን ከሞተ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ በተሰጠው የሙሴ ሕግ ላይ ነበር። (ዘሌዋውያን 18:9, 12, 13) በዚያን ጊዜ የቅርብ ዘመዳሞች ተጋብተው የሚወልዷቸው ልጆች በዛሬው ጊዜ እንደሚታየው ያለ በዘር የሚተላለፍ የጤና እክል ያጋጥማቸው የነበረ አይመስልም።

  •   መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ስለ ቤተሰባቸው የሚናገረው ታሪክ እውነተኛ ዘገባ ነው። ወደ አዳም የሚያደርሰው የዘር ሐረግ ዝርዝር የሚገኘው ሙሴ በጻፈው የዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ጸሐፊዎቹ ዕዝራና ሉቃስ በጻፏቸው መጻሕፍት ላይም ጭምር ነው። (ዘፍጥረት 5:3-5፤ 1 ዜና መዋዕል 1:1-4፤ ሉቃስ 3:38) ስለ ቃየን የሰፈረው ዘገባ እውነተኛ ስለሆነ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም ታሪኩን ጠቅሰው ጽፈዋል።—ዕብራውያን 11:4፤ 1 ዮሐንስ 3:12፤ ይሁዳ 11