በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የምንሞትበት ቀን አስቀድሞ ተወስኗል?

የምንሞትበት ቀን አስቀድሞ ተወስኗል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የምንሞትበት ቀን አስቀድሞ አልተወሰነም። መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎች ዕድል አስቀድሞ እንደተወሰነ የሚገልጸውን እምነት አይደግፍም፤ ከዚህ ይልቅ የምንሞተው አብዛኛውን ጊዜ ‘ባልተጠበቁ ክስተቶች’ የተነሳ እንደሆነ ይናገራል።—መክብብ 9:11 NW

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ “ለመሞትም ጊዜ አለው” በማለት ይናገር የለም?

 ልክ ነው፣ መክብብ 3:2 “ለመወለድ ጊዜ አለው፤ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፤ ለመንቀልም ጊዜ አለው” በማለት ይናገራል። ይሁን እንጂ በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደምንችለው ጥቅሱ እየተናገረ ያለው በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ስለሚያጋጥሙን የተለመዱ ነገሮች ነው። (መክብብ 3:1-8) አምላክ አንድ ገበሬ የሚዘራበትን ጊዜ እንደማይወስንለት ሁሉ የምንሞትበትን ቀንም አይወስንም። ከዚህ ይልቅ ጥቅሱ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት፣ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ከመጠመዳችን የተነሳ ፈጣሪያችንን ቸል ማለት እንደሌለብን ነው።—መክብብ 3:11፤ 12:1, 13

ዕድሜን ማራዘም ይቻላል

 ሕይወት አስተማማኝ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ ያም ሆኖ የጥበብ ውሳኔዎችን በማድረግ አብዛኛውን ጊዜ ዕድሜያችንን ማራዘም እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “የጠቢብ ትምህርት የሕይወት ምንጭ ናት፤ ሰውን በሞት ወጥመድ እንዳይያዝ ታደርገዋለች” ይላል። (ምሳሌ 13:14) በተመሳሳይም ሙሴ፣ እስራኤላውያን የአምላክን ትእዛዛት የሚጠብቁ ከሆነ ‘ዕድሜያቸው እንደሚረዝም’ ነግሯቸዋል። (ዘዳግም 6:2) በአንጻሩ ደግሞ መጥፎ ተግባር ወይም የሞኝነት ድርጊት የምንፈጽም ከሆነ በግዴለሽነት ዕድሜያችንን ልናሳጥር እንችላለን።—መክብብ 7:17

 ምንም ያህል ጥበበኛ ወይም ጠንቃቃ ብንሆንም እንኳ ከሞት እንደማናመልጥ የታወቀ ነው። (ሮም 5:12) ይሁንና ይህ ሁኔታ ይቀየራል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም” በማለት ቃል ገብቷል።—ራእይ 21:4