በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ በላይ ማግባትን ይደግፋል?

መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ በላይ ማግባትን ይደግፋል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አምላክ፣ ሰዎች ከአንድ በላይ እንዲያገቡ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ፈቅዶ ነበር። (ዘፍጥረት 4:19፤ 16:1-4፤ 29:18-29) ይሁንና ከአንድ በላይ የማግባትን ልማድ ያስጀመረው አምላክ አይደለም። ለአዳም የሰጠው አንዲት ሚስት ብቻ ነው።

 አምላክ፣ አንድ ወንድ አንዲትን ሴት ብቻ እንዲያገባ የነበረውን ዓላማ ኢየሱስ ክርስቶስ በድጋሚ ለሰዎች እንዲገልጽ አድርጓል። (ዮሐንስ 8:28) ኢየሱስ ስለ ትዳር ጥያቄ ሲቀርብለት እንዲህ የሚል መልስ ሰጥቷል፦ “ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁም? ‘በዚህ ምክንያት ሰው ከአባትና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።’”—ማቴዎስ 19:4, 5

 ከጊዜ በኋላም ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ወንድ የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዷም ሴት የራሷ ባል ይኑራት።” (1 ቆሮንቶስ 7:2) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ያገባ ወንድ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የተለየ ኃላፊነት እንዲሰጠው “የአንዲት ሚስት ባል” መሆን እንዳለበት ይናገራል።—1 ጢሞቴዎስ 3:2, 12