በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አምላክ የተለያዩ ፍጥረታትን ወደ ሕልውና ለማምጣት በዝግመተ ለውጥ ተጠቅሟል?

አምላክ የተለያዩ ፍጥረታትን ወደ ሕልውና ለማምጣት በዝግመተ ለውጥ ተጠቅሟል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አልተጠቀመም። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሰዎችን እንደሠራ እንዲሁም እንስሳትንና ዕፀዋትን “እንደየወገናቸው” እንደፈጠረ በግልጽ ይናገራል። a (ዘፍጥረት 1:12, 21, 25, 27፤ ራእይ 4:11) እንዲሁም መላው የሰው ዘር የተገኘው ከአዳምና ከሔዋን እንደሆነ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 3:20፤ 4:1) አምላክ የተለያዩ ፍጥረታትን ወደ ሕልውና ለማምጣት በዝግመተ ለውጥ እንደተጠቀመ የሚገልጸውን ጽንሰ ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ አይደግፈውም። እርግጥ ነው፣ ሳይንስ በአንድ የፍጥረት ወገን ሥር በሚመደቡ ፍጥረታት መካከል የተወሰነ ልዩነት ሊኖር እንደሚችል ይናገራል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሐሳብ አይቃወምም።

 አምላክ በዝግመተ ለውጥ ተጠቅሟል?

 አምላክ የተለያዩ ነገሮችን ለመፍጠር በዝግመተ ለውጥ እንደተጠቀመ የሚያምኑ ሰዎች ይህን ያደረገው በተለያየ መንገድ ሊሆን እንደሚችል ሲናገሩ ይሰማል። አንዳንድ ሰዎች ‘አምላክ ተፈጥሮን አቅጣጫ ለማስያዝ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ ተፈጥሯዊ ምርጦሽ እንደሆነ’ ያምናሉ።

 አምላክ በዝግመተ ለውጥ ተጠቅሞ እንደፈጠረ የሚገልጸው ጽንሰ ሐሳብ የሚከተሉትን ነጥቦችም ሊያካትት ይችላል፦

  •   ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ጥንት ከነበሩ ጥቂት ፍጥረታት ተሻሽለው የመጡ ናቸው።

  •   አንድ ዓይነት ፍጥረት ከእሱ ጨርሶ ወደተለየ ሌላ ዓይነት ፍጥረት ሊለወጥ ይችላል።

  •   ይህን ሂደት የሚከታተለው አምላክ ነው።

 ዝግመተ ለውጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል?

 አምላክ በዝግመተ ለውጥ ተጠቅሞ እንደፈጠረ የሚገልጸው ጽንሰ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የዘፍጥረት ዘገባ አንዳንድ ስህተቶች እንዳሉት በተዘዋዋሪ መንገድ የሚገልጽ ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የዘፍጥረት ዘገባ ትክክለኛ ታሪክ መሆኑን ተናግሯል። (ዘፍጥረት 1:26, 27፤ 2:18-24፤ ማቴዎስ 19:4-6) መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ከአምላክ ጋር ይኖር እንደነበረና አምላክ ‘ሁሉንም ነገሮች’ ሲፈጥር አብሮት እንደነበረ ይገልጻል። (ዮሐንስ 1:3) ከዚህ አንጻር አምላክ የተለያዩ ፍጥረታትን ወደ ሕልውና ለማምጣት በዝግመተ ለውጥ እንደተጠቀመ የሚገልጸው ጽንሰ ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ትምህርት ጋር አይስማማም።

 ዕፀዋትና እንስሳት ከአካባቢያቸው ጋር ለመላመድ ሲሉ ስለሚያደርጉት ለውጥ ምን ማለት ይቻላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ የፍጥረት ወገን ሥር በሚመደቡ ፍጥረታት መካከል ምን ያህል ልዩነት ሊኖር እንደሚችል አይገልጽም። በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ የፈጠራቸው የተለያዩ ዕፀዋትና እንስሳት ለመራባት ወይም ከአካባቢያቸው ጋር ለመላመድ ሲሉ ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚገልጸውን ሐሳብ አይቃወምም። አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ያለውን ለውጥ እንደ ዝግመተ ለውጥ ቢመለከቱትም ይህ ለውጥ ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ ፍጥረት እንደማያስገኝ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው።

a መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀምበት ‘ወገን’ የሚለው ቃል ሳይንቲስቶች ከሚጠቀሙበት “ዝርያ” ከሚለው ቃል ይበልጥ ሰፋ ያለ ትርጉም አለው። ሳይንቲስቶች አዲስ ዝርያ በዝግመተ ለውጥ እንደተገኘ ይናገሩ ይሆናል፤ ብዙውን ጊዜ ግን የተገኘው አዲስ ዓይነት ፍጥረት ሳይሆን በዚያው ‘ወገን’ ሥር ያለ መጠነኛ ልዩነት ያለው ፍጥረት ሊሆን ይችላል።