በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መስጠትን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መስጠትን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ በፈቃደኝነትና በትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ተነሳስተን እንድንሰጥ ያበረታታናል። እንዲህ ባለ ዝንባሌ ተነሳስቶ መስጠት ተቀባዩን ብቻ ሳይሆን ሰጪውንም እንደሚጠቅም ይናገራል። (ምሳሌ 11:25፤ ሉቃስ 6:38) ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ሲል ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

 መስጠት ጠቃሚ የሚሆነው መቼ ነው?

 መስጠት ጠቃሚ የሚሆነው በፈቃደኝነት ተነሳስተን ስናደርገው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ያለፍላጎቱ ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ” ይላል።—2 ቆሮንቶስ 9:7 የግርጌ ማስታወሻ

 ከልብ ተነሳስቶ መስጠት፣ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው “ሃይማኖት” አንዱ ገጽታ ነው። (ያዕቆብ 1:27 የግርጌ ማስታወሻ) እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በልግስና ስንሰጥ ከአምላክ ጋር አብረን እየሠራን ነው፤ አምላክ ደግሞ እንዲህ ያለውን ደግነት ለእሱ እንዳበደርነው ብድር አድርጎ ይቆጥረዋል። (ምሳሌ 19:17) አምላክ በደግነት ለሚሰጡ ሰዎች ብድራታቸውን እንደሚመልስ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ሉቃስ 14:12-14

 መስጠት ተገቢ የማይሆነው መቼ ነው?

 በራስ ወዳድነት ፍላጎት ተነሳስተን የምንሰጥ ከሆነ። ለምሳሌ፦

 የምንሰጠው ነገር አምላክ የሚያወግዘውን ድርጊት አሊያም አስተሳሰብ ለመደገፍ የሚውል ከሆነ። ለምሳሌ ገንዘብ የሰጠነው ሰው ገንዘቡን ቁማር ለመጫወት፣ አደንዛዥ ዕፅ ለመውሰድ ወይም የአልኮል መጠጥ አላግባብ ለመጠጣት የሚጠቀምበት ከሆነ እንዲህ ላለው ሰው መስጠታችን ተገቢ አይሆንም። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1) በተጨማሪም ሠርቶ ማግኘት እየቻለ ለመሥራት ፈቃደኛ ላልሆነ ሰው መስጠታችን ትክክል አይደለም።—2 ተሰሎንቄ 3:10

 የቤተሰባችንን ፍላጎት ችላ ብለን ለሌሎች የምንሰጥ ከሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብ ራሶች ለቤተሰባቸው አባላት የሚያስፈልገውን ነገር ማቅረብ እንዳለባቸው ያስተምራል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) አንድ የቤተሰብ ራስ ለሌሎች ብዙ ከመስጠቱ የተነሳ የገዛ ቤተሰቡ ችግር ላይ የሚወድቅ ከሆነ ተገቢ ያልሆነ ነገር እያደረገ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ንብረታቸው ሁሉ “ለአምላክ የተወሰነ ስጦታ” እንደሆነ በመናገር በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን የማይጦሩ ሰዎችን አውግዟል።—ማርቆስ 7:9-13