በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

1 ጴጥሮስ 5:6, 7—“ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ . . . የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት”

1 ጴጥሮስ 5:6, 7—“ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ . . . የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት”

 “ስለዚህ በተገቢው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥሮስ 5:6, 7 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።”—1 ጴጥሮስ 5:6, 7 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የ1 ጴጥሮስ 5:6, 7 ትርጉም

 ሐዋርያው ጴጥሮስ እነዚህን ቃላት የተናገረው ክርስቲያኖች አምላክ እንደሚሰማቸው ተማምነው ስለ ችግሮቻቸውና ስለሚያሳስቧቸው ነገሮች ለእሱ መንገር እንደሚችሉ ዋስትና ለመስጠት ነው። አምላክ ትሑት ሰዎችን ከፍ አድርጎ ይመለከታል፤ አትረፍርፎም ይባርካቸዋል።

 “ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ።” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የአምላክ እጅ” የሚለው አባባል ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው አገልጋዮቹን የማዳንና የመጠበቅ ኃይሉን ነው። (ዘፀአት 3:19፤ ዘዳግም 26:8፤ ዕዝራ 8:22) ክርስቲያኖች ከአምላክ እጅ በታች ራሳቸውን ዝቅ አድርገዋል ሊባል የሚችለው በእሱ ሙሉ በሙሉ ሲተማመኑ ነው። አቅማቸው ውስን እንደሆነ አምነው ይቀበላሉ፤ ያለእሱ እርዳታ ፈተናዎችን መወጣት እንደማይችሉም ያውቃሉ። (ምሳሌ 3:5, 6፤ ፊልጵስዩስ 4:13) አምላክ በተገቢው ጊዜና ከሁሉ በተሻለው መንገድ ለእነሱ ሲል እርምጃ የመውሰድ ኃይል እንዳለው አይጠራጠሩም።—ኢሳይያስ 41:10

 “በተገቢው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ።” በፈተና ሲያልፉ በትዕግሥት የሚጸኑ ሰዎች የኋላ ኋላ አምላክ ከፍ እንደሚያደርጋቸው ወይም እንደሚባርካቸው መተማመን ይችላሉ። አምላክ፣ አገልጋዮቹ ለዘላለም እየተፈተኑ እንዲኖሩ ወይም ከአቅማቸው በላይ የሆነ ፈተና እንዲደርስባቸው አይፈቅድም። (1 ቆሮንቶስ 10:13) እንዲያውም መልካም ሥራ መሥራታቸውን ከቀጠሉ “ጊዜው ሲደርስ” ወሮታቸውን እንደሚከፍላቸው ምንም ጥርጥር የለውም።—ገላትያ 6:9

 “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።” ክርስቲያኖች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ አምላክ በመጸለይ የሚያስጨንቃቸውን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ መጣል ይችላሉ። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዲህ የሚል ማብራሪያ ሰጥቷል፦ “መጣል የሚለው ግስ የሚያመለክተው አንድን ነገር አሽቀንጥሮ ለመወርወር የሚደረግን ጥረት ነው። ሆን ተብሎ የሚወሰድ እርምጃን ያመለክታል።” አንድ ክርስቲያን የሚያስጨንቁትን ነገሮች በአምላክ ላይ ሲጥል ጭንቀቱ ቀለል ይልለታል፤ መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክ ሰላም” ብሎ የሚጠራውን የመረጋጋት ስሜትም ያገኛል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) አምላክ እሱን መርዳት እንደሚፈልግ እርግጠኛ ነው፤ ምክንያቱም እንደሚያስብለትና እሱን ለመደገፍ የሚያስችል ታላቅ ኃይል እንዳለው ያውቃል።—መዝሙር 37:5፤ 55:22

የ1 ጴጥሮስ 5:6, 7 አውድ

 ምዕራፍ 5 ሐዋርያው ጴጥሮስ ለክርስቲያኖች የጻፈው የመጀመሪያው ደብዳቤ የመጨረሻ ምዕራፍ ነው። (1 ጴጥሮስ 1:1) በዚያን ጊዜ የነበሩ የክርስቶስ ተከታዮች ልክ በአሁኑ ጊዜ እንዳለው የተለያዩ የእምነት ፈተናዎች ያጋጥሟቸው ነበር፤ እነዚህ ነገሮች ቢያስጨንቋቸውም አይገርምም። (1 ጴጥሮስ 1:6, 7) ያለባቸውን መከራ አሳምሮ የሚያውቀው ጴጥሮስ፣ ከ62-64 ዓ.ም. ገደማ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚያጽናና እና የሚያበረታታ ደብዳቤ ጻፈላቸው።—1 ጴጥሮስ 5:12

 ጴጥሮስ ደብዳቤውን የደመደመው በእምነታቸው ምክንያት እየተፈተኑ ያሉ ክርስቲያኖችን የሚያበረታታ ሐሳብ በመናገር ነው። ምንጊዜም ትሑት ከሆኑና በአምላክ መታመናቸውን ከቀጠሉ አምላክ ጸንተው እንዲቆሙ እንደሚረዳቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። (1 ጴጥሮስ 5:5-10) ጴጥሮስ የተናገረው ነገር በዛሬው ጊዜ በእምነታቸው ምክንያት እየተሰደዱ ያሉ ክርስቲያኖችንም ያበረታታል።

 የ1 ጴጥሮስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።