በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ሚክያስ 6:8—“በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ”

ሚክያስ 6:8—“በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ”

 “ሰው ሆይ፣ መልካም የሆነውን ነግሮሃል። ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን እንድታደርግ፣ ታማኝነትን እንድትወድና ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር እንድትሄድ ብቻ ነው!”—ሚክያስ 6:8 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?”—ሚክያስ 6:8 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የሚክያስ 6:8 ትርጉም

 ነቢዩ ሚክያስ፣ ይሖዋ a አምላክን ማስደሰት ለሰዎች በጣም ከባድ እንዳልሆነ ገልጿል። (1 ዮሐንስ 5:3) በዚህ ጥቅስ ላይ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ነገር በሦስት ሐረጎች ቁልጭ ተደርጎ ተቀምጧል። ሁለቱ ከሰዎች ጋር ካለን ግንኙነት፣ ሦስተኛው ደግሞ ከአምላክ ጋር ካለን ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነው።

 “ፍትሕን እንድታደርግ።” አምላክ አገልጋዮቹ ፍትሐዊ ወይም ትክክለኛ የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ይፈልጋል። ይህም ሲባል አምላክ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ካወጣው መሥፈርት ጋር የሚስማማ አስተሳሰብና ምግባር ሊኖረን ይገባል ማለት ነው። (ዘዳግም 32:4) ለምሳሌ በአምላክ መሥፈርቶች የሚመሩ ሰዎች ዘር፣ ባሕልና የኑሮ ደረጃ ሳይለዩ ሁሉንም ሰዎች በሐቀኝነትና ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ ለመያዝ ጥረት ያደርጋሉ።—ዘሌዋውያን 19:15፤ ኢሳይያስ 1:17፤ ዕብራውያን 13:18

 “ታማኝነትን እንድትወድ።” ይህ ሐረግ “ታማኝ ፍቅርን እንድትወድ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። (ሚክያስ 6:8 የግርጌ ማስታወሻ) ይህ ጥቅስ መጀመሪያ በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ “ታማኝነት” የሚለው ቃል አንድን ሰው አለመክዳትን ብቻ ሳይሆን ከሚጠበቅብን አልፈን ለእሱ ደግነትና ምሕረት ማሳየትንም ይጨምራል። አምላክ እሱን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች ደግነትና ምሕረት እንዲያሳዩ ብቻ ሳይሆን እነዚህን ባሕርያት እንዲወዱም ይጠብቅባቸዋል። ይህም ሲባል አገልጋዮቹ ሌሎችን፣ በተለይም የተቸገሩትን መርዳት ሊያስደስታቸው ይገባል ማለት ነው። ደግሞም መስጠት ደስታ ያስገኛል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

 “ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር እንድትሄድ።” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘መሄድ’ የሚለው ቃል “አንድን ዓይነት አካሄድ መከተል” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። አንድ ሰው ከአምላክ ጋር መሄድ የሚችለው እሱን የሚያስደስት የአኗኗር ዘይቤ በመከተል ነው። ኖኅ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ኖኅ “ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር” የተባለው በአምላክ ዓይን ጻድቅ ስለነበር እንዲሁም “በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል እሱ እንከን የሌለበት ሰው” ስለነበር ነው። (ዘፍጥረት 6:9) በዛሬው ጊዜም የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ትምህርቶች መሠረት ሕይወታችንን በመምራት ‘ከአምላክ ጋር መሄድ’ እንችላለን። ይህን ለማድረግ ልካችንን ማወቅ ማለትም የአቅም ገደብ እንዳለብን እንዲሁም በሁሉም ነገር የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገን አምነን መቀበል ይኖርብናል።—ዮሐንስ 17:3፤ የሐዋርያት ሥራ 17:28፤ ራእይ 4:11

የሚክያስ 6:8 አውድ

 ሚክያስ በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በጥንቷ እስራኤል ይኖር የነበረ ነቢይ ነው። በወቅቱ የእስራኤል ምድር በጣዖት አምልኮ፣ በማጭበርበርና በጭቆና ተሞልታ ነበር። (ሚክያስ 1:7፤ 3:1-3, 9-11፤ 6:10-12) አብዛኞቹ እስራኤላውያን አምላክ ለሙሴ በሰጠው ሕግ ውስጥ የነበሩትን መመሪያዎች ችላ ይሉ ነበር። ብዙዎች ሃይማኖታዊ ሥርዓት በመፈጸምና መሥዋዕት በማቅረብ ብቻ የአምላክን ሞገስ እንደሚያገኙ ያስቡ ነበር፤ ሆኖም ምንኛ ተሳስተዋል!—ምሳሌ 21:3፤ ሆሴዕ 6:6፤ ሚክያስ 6:6, 7

 ሚክያስ ከሞተ ከበርካታ መቶ ዘመናት በኋላ ኢየሱስ፣ አባቱ ፍቅር፣ ፍትሕና ምሕረት በሚያሳዩ ሰዎች እንደሚደሰት፣ ለታይታ ብለው የአምልኮ ሥርዓት በሚፈጽሙ ሰዎች ግን እንደሚያዝን ገልጿል። (ማቴዎስ 9:13፤ 22:37-39፤ 23:23) ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ አምላክ በዛሬው ጊዜ ካሉ አገልጋዮቹም ምን እንደሚጠብቅ ያስተምረናል።

 የሚክያስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a የአምላክ ስም በዕብራይስጥ יהוה (የሐወሐ) በሚሉት አራት ፊደላት የሚወከል ሲሆን በአማርኛ “ይሖዋ” ተብሎ ይጠራል። አዲሱ መደበኛ ትርጉም በዚህ ጥቅስ ላይ ይህን ስም “እግዚአብሔር” በሚለው ስም ተክቶታል። ይሖዋ ስለሚለው ስም እንዲሁም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ስም የማይጠቀሙት ለምን እንደሆነ ለማወቅ “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።