በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

የሐዋርያት ሥራ 1:8—“ኃይል ትቀበላላችሁ”

የሐዋርያት ሥራ 1:8—“ኃይል ትቀበላላችሁ”

 “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 1:8 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 1:8 የ1954 ትርጉም

የሐዋርያት ሥራ 1:8 ትርጉም

 ኢየሱስ ለተከታዮቹ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ በመታገዝ አገልግሎታቸውን በጣም ርቀው በሚገኙ የዓለም ክፍሎች ጭምር ማከናወን እንደሚችሉ ቃል ገብቶላቸዋል።

 “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ።” ኢየሱስ እሱ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ a እንደሚረዳቸው ለደቀ መዛሙርቱ የገባላቸውን ቃል በድጋሚ አረጋግጦላቸዋል። (ዮሐንስ 14:16, 26) ኢየሱስ በ33 ዓ.ም. ወደ ሰማይ ከሄደ ከአሥር ቀን በኋላ ተከታዮቹ ቃል የተገባላቸውን መንፈስ ቅዱስ አገኙ። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲናገሩና ተአምራትን እንዲፈጽሙ ብቻ ሳይሆን በኢየሱስ ላይ ስላላቸው እምነት በድፍረት እንዲናገሩም ረድቷቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 3:1-8፤ 4:33፤ 6:8-10፤ 14:3, 8-10

 “ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” “ምሥክር” የሚለው ቃል ካየው ወይም ራሱ ካጋጠመው ነገር በመነሳት የአንድን ነገር እውነተኝነት የሚያረጋግጥን ሰው ያመለክታል። ሐዋርያቱ የኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት የዓይን እማኞች እንደመሆናቸው መጠን ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲፈጽም ስለተከናወኑት ነገሮች እንዲሁም ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው መመሥከር ይችላሉ። (የሐዋርያት ሥራ 2:32፤ 3:15፤ 5:32፤ 10:39) እነሱ የሰጡት አስተማማኝ ምሥክርነት ብዙዎች ኢየሱስ፣ ክርስቶስ ማለትም ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን እርግጠኛ እንዲሆኑ አድርጓል። (የሐዋርያት ሥራ 2:32-36, 41) ሐዋርያቱ በተናገሩት ነገር ያመኑ ሰዎች የኢየሱስ ምሥክሮች በመሆን እነሱም በተራቸው የኢየሱስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ ስላለው ትርጉም ለሌሎች አውጀዋል።—የሐዋርያት ሥራ 17:2, 3፤ 18:5

 “እስከ ምድር ዳር ድረስ።” ይህ አገላለጽ “እስከ ምድር ጫፍ ድረስ” ወይም “በሌሎች አገሮች” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ተከታዮቹ ስለ እሱ የሚሰጡትን ምሥክርነት ስፋት ይጠቁማሉ። በይሁዳና በሰማርያ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በጣም ርቀው ባሉ ቦታዎችም ጭምር ስለሚያምኑበት ነገር ያውጃሉ። እንዲያውም የሚሰብኩበት ክልልም ሆነ ምሥራቹን የሚሰብኩላቸው ሰዎች ቁጥር ከኢየሱስ የበለጠ ይሆናል። (ማቴዎስ 28:19፤ ዮሐንስ 14:12) ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ከተናገረ 30 ዓመት እንኳ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ስለ ኢየሱስ የሚገልጸው ምሥራች “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ ተሰብኳል” ብሎ ሊጽፍ ችሏል፤ ምሥራቹ እንደ ሮም፣ ጳርቴና (ከካስፒያን ባሕር በስተ ደቡብ ምሥራቅ) እና ሰሜን አፍሪካ ባሉ ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች እንኳ ተሰብኳል።—ቆላስይስ 1:23፤ የሐዋርያት ሥራ 2:5, 9-11

የሐዋርያት ሥራ 1:8 አውድ

 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሚቀጥለው የሉቃስ ወንጌል ካቆመበት ነው። (ሉቃስ 24:44-49፤ የሐዋርያት ሥራ 1:4, 5) የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ የሆነው ደቀ መዝሙሩ ሉቃስ ዘገባውን የሚጀምረው ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ እንዴት እንደተገለጠላቸው በመግለጽ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 1:1-3) ከዚያም የክርስቲያን ጉባኤ የተቋቋመውና ከ33 ዓ.ም. እስከ 61 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እድገት ያደረገው እንዴት እንደሆነ ዘግቧል።—የሐዋርያት ሥራ 11:26

 የሐዋርያት ሥራ 1:8 አውድ እንደሚያሳየው የኢየሱስ ተከታዮች፣ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት የሚጀምረው በእነሱ የሕይወት ዘመን መሆን አለመሆኑን ማወቅ ፈልገው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:6) ኢየሱስም በምላሹ መንግሥቱ ስለሚቋቋምበት ጊዜ ከልክ በላይ እንዳይጨነቁ ነገራቸው። (የሐዋርያት ሥራ 1:7) ከዚህ ይልቅ ተከታዮቹ ትኩረት ማድረግ ያለባቸው “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ስለ ኢየሱስ ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ ላይ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ይህንኑ ምክር ተግባራዊ በማድረግ ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች በቅንዓት እየሰበኩ ነው።—ማቴዎስ 24:14

 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a የአምላክ ቅዱስ መንፈስ፣ አምላክ የተለያዩ ነገሮችን ለማከናወን የሚጠቀምበት ኃይል ነው። (ዘፍጥረት 1:2) ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።