በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ኤፌሶን 3:20—“ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ [የሚቻለው]” አምላክ

ኤፌሶን 3:20—“ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ [የሚቻለው]” አምላክ

 “እንግዲህ በእኛ ውስጥ ከሚሠራው ኃይሉ ጋር በሚስማማ ሁኔታ፣ ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚችለው ለእሱ . . . ክብር ይሁን።”—ኤፌሶን 3:20, 21 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው እንደ ኀይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፣ . . . ለእርሱ ክብር ይሁን።”—ኤፌሶን 3:20, 21 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የኤፌሶን 3:20 ትርጉም

 ሐዋርያው ጳውሎስ በአምላክ ላይ ያለውን የመተማመን ስሜት እየገለጸ ነው፤ አምላክ፣ አገልጋዮቹ ጨርሶ ይሆናል ብለው ባልጠበቁት መንገድ ጸሎታቸውን እንደሚመልስና የልባቸውን መሻት እንደሚፈጽም ተናግሯል። እንዲያውም አምላክ የሚሰጠው ምላሽ ከጠበቁት ወይም ተስፋ ካደረጉት የላቀ ሊሆን ይችላል።

 “እንግዲህ በእኛ ውስጥ ከሚሠራው ኃይሉ ጋር በሚስማማ ሁኔታ . . . ለሚችለው።” እዚህ ላይ ‘የሚችለው’ የተባለው ይሖዋ አምላክ a እንደሆነ ከቁጥር 21 እንረዳለን። ጳውሎስ ቁጥር 21 ላይ “ለእሱ በጉባኤው አማካኝነትና በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት . . . ለዘላለም ክብር ይሁን” ብሏል። አምላክ የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስፈልገንን ኃይል ወይም ብርታት ሊሰጠን ይችላል።—ፊልጵስዩስ 4:13

 ሐዋርያው ጳውሎስ ቁጥር 20 ላይ ይሖዋ አገልጋዮቹን ለመርዳት ስላለው አቅም ትኩረት የሚስብ ነጥብ ጠቅሷል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው “ለሚችለው” ተብሎ የተተረጎመው ቃል አምላክ የፈለገውን ነገር የማድረግ አቅም እንዳለው ያጎላል። ከልብ የሚወደን አንድ ወዳጃችን እኛን መርዳት ቢፈልግም ሰው ነውና አቅም ሊያንሰው ይችላል፤ ይሖዋ ግን ምንጊዜም አገልጋዮቹን ለመንከባከብና ጸሎታቸውን ለመመለስ አቅሙ አለው። ገደብ የለሽ ኃይልና ሥልጣን ያለው እሱ ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 40:26

 “ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚችለው።” ይሖዋ አምላክ ለአገልጋዮቹ አትረፍርፎ እንዲያውም “እጅግ አብልጦ” መስጠት ይችልበታል። እነሱ በቂ ወይም ከበቂ በላይ ነው ብለው ከሚያስቡት በላይም እንኳ ሊያደርግላቸው ይችላል።

 “ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ” የሚለው አገላለጽም ነጥቡን በሌላ አቅጣጫ የሚያጎላ ነው። ጳውሎስ እዚህ ላይ እኛ የሚለውን ተውላጠ ስም የተጠቀመው ሁሉም ክርስቲያኖች አምላክ ከጠበቁት በላይ ሊረዳቸው እንደሚችል እንዲገነዘቡ ነው። አንድ እንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ቁጥር 20⁠ን “ከምንጠይቀውና ከምናስበው ሁሉ በላይ ያለገደብ ማድረግ ለሚችለው” ሲል አስቀምጦታል። ክርስቲያኖች አንዳንድ ጊዜ ችግሮቻቸው ከአቅማቸው በላይ በጣም ከባድ ወይም ውስብስብ እንደሆኑ ሊሰማቸው ይችላል። ምን ብለው እንደሚጸልዩ እንኳ ግራ የሚገባቸው ጊዜ አለ። ሆኖም ከይሖዋ የመረዳት ችሎታ በላይ የሆነ አንድም ችግር የለም፤ እነሱን ለመርዳት ያለው አቅምም ገደብ የለውም። እሱ ተገቢ ነው ባለው ጊዜ የትኛውንም ችግር ሊፈታው ይችላል፤ አንዳንድ ጊዜ ይህን የሚያደርገው አገልጋዮቹ ጨርሶ ባላሰቡት ወይም ባልጠበቁት መንገድ ነው። (ኢዮብ 42:2፤ ኤርምያስ 32:17) እስከዚያው ግን ለመጽናት እንዲያውም በደስታ ለመጽናት የሚያስችላቸውን ጥንካሬ ይሰጣቸዋል።—ያዕቆብ 1:2, 3

የኤፌሶን 3:20 አውድ

 የኤፌሶን መጽሐፍ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ከተማ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ ነው፤ ኤፌሶን በትንሿ እስያ (በአሁኗ ቱርክ) የምትገኝ ከተማ ናት። ጳውሎስ በደብዳቤው ላይ ለእነዚህ ክርስቲያኖች ምን ብሎ እንደሚጸልይላቸው ገልጿል። (ኤፌሶን 3:14-21) ፍቅር የሚንጸባረቅበትን የኢየሱስ አስተሳሰብና ድርጊት በመምሰል የክርስቶስን ፍቅር ይበልጥ እንዲያውቁ ጸልዮላቸዋል፤ ይህ ሐሳብ ለሁሉም ክርስቲያኖች ይሠራል። ጳውሎስ ጸሎቱን የደመደመው በኤፌሶን 3:20, 21 ላይ እንደሚገኘው አምላክን በማወደስ ነው።

 የኤፌሶን መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።