በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።”—ያዕቆብ 4:8

አምላክ ጸሎታችንን ይሰማል?

አምላክ ጸሎታችንን ይሰማል?

አምላክ ጸሎትህን የሚሰማ መሆኑን ተጠራጥረህ ታውቃለህ? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ብዙዎች አምላክ እንዲረዳቸው ቢጸልዩም ችግሮቻቸው አልተወገዱላቸውም። ታዲያ ይህ አምላክ ጸሎታችንን እንደማይሰማ የሚያሳይ ነው? በፍጹም! መጽሐፍ ቅዱስ በትክክለኛው መንገድ እስከጸለይን ድረስ አምላክ ጸሎታችንን እንደሚሰማ ማረጋገጫ ይሰጠናል። እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንመልከት።

አምላክ ጸሎትህን ይሰማል።

“ጸሎት ሰሚ የሆንከው አምላክ ሆይ፣ ሁሉም ዓይነት ሰው ወደ አንተ ይመጣል።”—መዝሙር 65:2

አንዳንድ ሰዎች ጸሎታቸውን የሚሰማ አካል እንዳለ ባያምኑም ይጸልያሉ፤ እንዲህ የሚያደርጉት ጸሎት ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ስለሚያደርግ ነው። ሆኖም የምንጸልየው፣ ጸሎት ጭንቀታችን ቀለል እንዲልልንና ችግሮቻችንን በተሻለ መንገድ እንድንወጣ ስለሚረዳን ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል፦ “ይሖዋ * ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። . . . እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትንም ጩኸት ይሰማል።”—መዝሙር 145:18, 19

በመሆኑም ይሖዋ አምላክ የአገልጋዮቹን ጸሎት እንደሚሰማ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። “ትጠሩኛላችሁ፤ ወደ እኔም ቀርባችሁ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ” በማለት ፍቅራዊ ግብዣ አቅርቦልናል።—ኤርምያስ 29:12

አምላክ ወደ እሱ እንድትጸልይ ይፈልጋል።

“ሳትታክቱ ጸልዩ።”—ሮም 12:12

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሳናሰልስ እንድንጸልይ’ እና ‘በማንኛውም ጊዜ መጸለያችንን እንድንቀጥል’ ያበረታታናል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደምንችለው ይሖዋ አምላክ ወደ እሱ እንድንጸልይ ይፈልጋል።—ማቴዎስ 26:41፤ ኤፌሶን 6:18

አምላክ ወደ እሱ እንድንጸልይ የሚፈልገው ለምንድን ነው? እስቲ አስበው፦ አንድ አባት ትንሽ ልጁ “አባዬ፣ እባክህ እርዳኝ?” ብሎ ሲጠይቀው ደስ አይለውም? እርግጥ ነው፣ አባትየው የልጁን ፍላጎት ወይም ስሜት ቀድሞውንም ያውቅ ይሆናል፤ ከልጁ አንደበት እነዚያን ቃላት መስማቱ ግን ልጁ እንደሚተማመንበትና እንደሚቀርበው እንዲሰማው ያደርጋል። እኛም በተመሳሳይ ወደ ይሖዋ አምላክ ስንጸልይ እንደምንተማመንበትና ልንቀርበው እንደምንፈልግ እናሳያለን።—ምሳሌ 15:8፤ ያዕቆብ 4:8

አምላክ ያስብልሃል።

“የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥሮስ 5:7

አምላክ ወደ እሱ እንድንጸልይ የሚፈልገው ስለሚወደንና ስለሚያስብልን ነው። የሚያሳስቡንንና የሚያስጨንቁንን ነገሮች ጠንቅቆ የሚያውቅ ከመሆኑም ሌላ ሊረዳን ይፈልጋል።

ንጉሥ ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እርዳታ ለመጠየቅ ወደ ይሖዋ ይጸልይ ነበር፤ እንዲሁም ሐሳቡንና ስሜቱን ለአምላክ ይገልጽ ነበር። (መዝሙር 23:1-6) ታዲያ አምላክ ለዳዊት ምን ስሜት ነበረው? አምላክ ዳዊትን ይወደው የነበረ ሲሆን ወደ እሱ የሚያቀርባቸውን ጸሎቶች ይሰማ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 13:22) አምላክ ለእኛም ስለሚያስብልን ወደ እሱ የምናቀርበውን ጸሎት ይሰማል።

‘ይሖዋ ድምፄን ስለሚሰማ እወደዋለሁ’

እነዚህን ቃላት የተናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መዝሙሮች ከጻፉት ሰዎች መካከል አንዱ ነው። ይህ መዝሙራዊ፣ አምላክ ጸሎቱን እንደሰማለት እርግጠኛ ነበር፤ ይህን ማወቁም በእጅጉ ረድቶታል። ወደ አምላክ ይበልጥ እንደቀረበ የተሰማው ከመሆኑም ሌላ በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠመውን ጭንቀትና ሐዘን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት አግኝቷል።—መዝሙር 116:1-9

አምላክ ጸሎታችንን እንደሚሰማ እርግጠኛ ከሆንን ሳንታክት ወደ እሱ እንጸልያለን። በሰሜናዊ ስፔን የሚኖረውን የፔድሮን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ፔድሮ የ19 ዓመት ልጁን በመኪና አደጋ አጣ። በዚህ ጊዜ፣ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ለአምላክ የተናገረ ሲሆን ማጽናኛና ድጋፍ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጸለየ። ውጤቱ ምን ሆነ? ፔድሮ “ይሖዋ ሌሎች ክርስቲያኖች እኔንና ባለቤቴን እንዲያጽናኑንና እንዲደግፉን በማድረግ ለጸሎቴ መልስ ሰጥቶኛል” ብሏል።

አብዛኛውን ጊዜ አምላክ አሳቢ የሆኑ ወዳጆቻችን እንዲያጽናኑንና እንዲደግፉን በማድረግ ለጸሎታችን መልስ ይሰጣል

ፔድሮ ወደ አምላክ መጸለዩ ልጁን መልሶ እንዲያገኝ ባያስችለውም እሱንና ቤተሰቡን በብዙ መንገዶች ጠቅሟቸዋል። ባለቤቱ ማሪያ ካርመን እንዲህ ብላለች፦ “ጸሎት ሐዘኔን እንድቋቋም ረድቶኛል። ይሖዋ አምላክ ስሜቴን እንደተረዳልኝ እርግጠኛ ነበርኩ፤ ምክንያቱም ስጸልይ ውስጤ ይረጋጋ ነበር።”

መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ሐሳብና ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ያጋጠማቸው ነገር አምላክ የምናቀርበውን ጸሎት እንደሚሰማ በግልጽ ያሳያሉ። ሆኖም አምላክ ምላሽ የሚሰጠው ለሁሉም ጸሎቶች አይደለም። አምላክ ለአንዳንዶቹ ጸሎቶች መልስ ሲሰጥ ለአንዳንዶቹ ግን መልስ የማይሰጠው ለምንድን ነው?

^ አን.5 ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18