በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ፊልጵስዩስ 4:13—“ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ”

ፊልጵስዩስ 4:13—“ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ”

 “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።”—ፊልጵስዩስ 4:13 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ።”—ፊልጵስዩስ 4:13 የ1954 ትርጉም

የፊልጵስዩስ 4:13 ትርጉም

 ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈው ይህ ሐሳብ የአምላክ አገልጋዮች የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን ኃይል እንደሚያገኙ ዋስትና ይሰጣል።

 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ለጳውሎስ ኃይል የሰጠው ክርስቶስ እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁንና ጥንታዊ በሆኑ የግሪክኛ ቅጂዎች ውስጥ እዚህ ጥቅስ ላይ “ክርስቶስ” የሚለው ቃል አይገኝም። በመሆኑም በርካታ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት” (አዲስ ዓለም ትርጉም) ወይም “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ” (አዲሱ መደበኛ ትርጉም) እንደሚሉት ያሉ አገላለጾችን ተጠቅመዋል። ታዲያ ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ስለ ማን ነው?

 ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ስለ አምላክ እንደሆነ የጥቅሱ አውድ ይጠቁማል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 10) ጳውሎስ በዚሁ ደብዳቤ ላይ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች “ለተግባር የሚያነሳሳ . . . ኃይል እንድታገኙ በማድረግ . . . ብርታት የሚሰጣችሁ አምላክ ነው” ብሏቸው ነበር። (ፊልጵስዩስ 2:13) በ2 ቆሮንቶስ 4:7 ላይ ደግሞ አገልግሎቱን ለማከናወን የሚያስችል ኃይል የሰጠው አምላክ እንደሆነ ጽፏል። (ከ2 ጢሞቴዎስ 1:8 ጋር አወዳድር።) እንግዲያው ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ” ሲል ስለ አምላክ እየተናገረ እንደነበረ የሚያረጋግጥ አሳማኝ ምክንያት አለ።

 ጳውሎስ “ለሁሉም ነገር የሚሆን” ኃይል እንደሚያገኝ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? ጳውሎስ ይህን ሲል የአምላክን ፈቃድ በሚያደርግበት ወቅት ያጋጠሙትን የተለያዩ ሁኔታዎች መጥቀሱ ሳይሆን አይቀርም። በቁሳዊ ረገድ ቢያገኝም ሆነ ቢያጣ አምላክ እንደሚንከባከበው ይተማመን ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ባለው ነገር ረክቶ መኖርን ተምሯል።—2 ቆሮንቶስ 11:23-27፤ ፊልጵስዩስ 4:11

 ጳውሎስ የጻፈው ሐሳብ በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችንም ያበረታታል። አምላክ አገልጋዮቹ ፈተናዎችን ለመቋቋምና ፈቃዱን ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን ኃይል ይሰጣቸዋል። አምላክ በመንፈስ ቅዱስ ማለትም በሥራ ላይ ባለው ኃይሉ እንዲሁም በእምነት ባልንጀሮቻቸውና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ብርታት ይሰጣቸዋል።—ሉቃስ 11:13፤ የሐዋርያት ሥራ 14:21, 22፤ ዕብራውያን 4:12

የፊልጵስዩስ 4:13 አውድ

 እነዚህ ቃላት የሚገኙት ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ መደምደሚያ ላይ ነው። ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ የጻፈው ከ60-61 ዓ.ም. ገደማ በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ ታስሮ በነበረበት ወቅት ነው። ለተወሰነ ጊዜ ያህል የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ለጳውሎስ ቁሳዊ ድጋፍ መስጠት አልቻሉም ነበር። አሁን ግን ጳውሎስን ለመርዳት ስጦታ እየላኩለት ነው።—ፊልጵስዩስ 4:10, 14

 ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን ስለ ልግስናቸው ከልቡ አመስግኗቸዋል፤ እንዲሁም የሚያስፈልገውን ነገር እንዳላጣ ነግሯቸዋል። (ፊልጵስዩስ 4:18) በተጨማሪም አጋጣሚውን ተጠቅሞ ክርስቲያናዊ ሕይወትን የሚመለከት አንድ ሚስጥር ነገራቸው፦ ሀብታምም ሆኑ ድሃ፣ ሁሉም ክርስቲያኖች በአምላክ እርዳታ ከተማመኑ ባላቸው ነገር ረክተው መኖር ይችላሉ።—ፊልጵስዩስ 4:12