በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጆችና ማኅበራዊ ሚዲያ—ክፍል 1፦ ልጄ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲጠቀም ልፍቀድለት?

ልጆችና ማኅበራዊ ሚዲያ—ክፍል 1፦ ልጄ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲጠቀም ልፍቀድለት?

 በአንድ የዳሰሳ ጥናት ላይ 97 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል። የእናንተስ ልጅ ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም እንድትፈቅዱለት ጥያቄ እያቀረበ ነው? እሺ ወይም እንቢ ከማለታችሁ በፊት ከታች የተጠቀሱትን ነጥቦች አስቡባቸው።

በዚህ ርዕስ ውስጥ፦

 የልጃችሁ የጊዜ አጠቃቀም

 ኸልፕ ጋይድ የተባለው ድረ ገጽ እንዲህ ብሏል፦ “ማኅበራዊ ሚዲያ የተዘጋጀው ሙሉ በሙሉ ትኩረታችሁን እንዲይዝ ታስቦ ነው። አቁሙ አቁሙ አይልም፤ ‘ምን መጥቶ ይሆን?’ እያላችሁ በተደጋጋሚ ስልካችሁን እንድትመለከቱ ይገፋፋችኋል።”

 “ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ነገሮችን ስመለከት ሳላስበው ሰዓታት ያልፋሉ። ከስልኬ መላቀቅና ቁም ነገር ያለው ሌላ ሥራ ማከናወን በጣም ይፈትነኛል።”—ሊን፣ 20

 ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ልጄ በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሙ ላይ ያወጣሁለትን ገደቦች ለማክበር ቆራጥነቱ አለው? የራሱን ገደቦች ማውጣትና ማክበር የሚችልበት የብስለት ደረጃ ላይ ደርሷል?

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የምትመላለሱት . . . እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ . . . ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።”—ኤፌሶን 5:15, 16

ለልጃችሁ ተገቢውን ገደብ ሳታወጡ ማኅበራዊ ሚዲያ እንድትጠቀም መፍቀድ፣ ተገቢውን ሥልጠና ሳታገኝ ፈረስ እንድትጋልብ ከመፍቀድ ተለይቶ አይታይም

ልጃችሁ ስለ ጓደኝነት ያለው አመለካከት

  “ማኅበራዊ ሚዲያ” የሚለው መጠሪያ በራሱ ተጠቃሚዎች ጓደኞች እንዲያገኙና ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር እንዲገናኙ የተዘጋጀ መድረክ እንደሆነ ይጠቁማል። ጓደኝነቱ ግን በአብዛኛው የይስሙላ ነው።

 “አንድ ያስተዋልኩት ነገር፣ ብዙ ወጣቶች ብዙ ‘ላይክ’ ወይም ‘ፎሎወር’ ሲያገኙ ብዙ የሚወዳቸው ሰው ያገኙ ይመስላቸዋል፤ የሚገርመው ግን አንዳንዶቹን ሰዎች ጨርሶ አያውቋቸውም።”—ፓትሪሺያ፣ 17

 ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ልጄ ላይክ እና ፎሎወር ማግኘት ትልቅ ነገር እንዳልሆነ የሚገነዘብበት የብስለት ደረጃ ላይ ደርሷል? በአካል ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት ይችላል?

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።”—ምሳሌ 17:17

የልጃችሁ ስሜታዊ ደኅንነት

 ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከልክ ያለፈ ጊዜ የሚያሳልፉ ሰዎች ለብቸኝነት፣ ለጭንቀት ይባስ ብሎም ለድባቴ እንደሚዳረጉ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።

  “ጓደኞችህ አንተ በሌለህበት ዘና ሲሉ የሚያሳዩ ፎቶዎችን እያየህ እንዴት ልትደሰት ትችላለህ?”—ሴሬና፣ 19

 ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ልጄ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር ማየቱ ስለ ራሱ ብቻ እንዲያስብ፣ የፉክክር ስሜት እንዲያድርበት ወይም ሌላ መጥፎ ስሜት እንዲሰማው ያደርገው ይሆን? ወይስ እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ለመቋቋም የሚያስችል ብስለት አለው?

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ።”—ገላትያ 5:26

የልጃችሁ የኢንተርኔት ጠባይ

 ማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎች ኢንተርኔት ላይ ጉልበተኞች እንዲሆኑ፣ የብልግና መልእክቶችን እንዲልኩና ፖርኖግራፊ እንዲያዩ መንገድ ይከፍታል። ልጃችሁ በራሱ ተነሳሽነት እነዚህን ነገሮች ባያደርግ እንኳ ለእነዚህ መጥፎ ተጽዕኖዎች ሊጋለጥ ይችላል።

 “ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስትሆን ሳታስበው መጥፎ ነገር ውስጥ ልትገባ ትችላለህ። ስድብና ተገቢ ያልሆነ ሙዚቃ እንደልብ የሚገኝበት ቦታ ነው።”—ሊንዳ፣ 23

  ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ልጄ ኢንተርኔትን በጨዋነት መጠቀም የሚችልበት የብስለት ደረጃ ላይ ነው? አጉል ነገር ቢያይ ወዲያውኑ ለማጥፋት ቆራጥነቱ አለው?

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የፆታ ብልግናና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ወይም ስግብግብነት በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ፤ አሳፋሪ ምግባር፣ የማይረባ ንግግርም ሆነ ጸያፍ ቀልድ የማይገቡ ነገሮች ናቸው።”—ኤፌሶን 5:3, 4

ማኅበራዊ ሚዲያ የግድ አስፈላጊ ነው?

 ማኅበራዊ ሚዲያ ለሕይወት የግድ አስፈላጊ አይደለም፤ ሌላው ቀርቶ ለደስታችን እንኳ የሚጨምረው የተለየ ነገር የለም። ብዙ ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያ ባይጠቀሙም ደስተኛ መሆን ችለዋል፤ ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀማቸውን ለማቆም የወሰኑትም እንዲሁ።

 “ማኅበራዊ ሚዲያ እህቴን ምን ያህል እንደጎዳት ስመለከት እኔም መጠቀሜን ለማቆም ወሰንኩ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ደስታዬ ጨምሯል፤ ሕይወትን ይበልጥ እያጣጣምኩ እንደሆነም ይሰማኛል።”—ናታን፣ 17

 ዋናው ነጥብ፦ ልጃችሁ ማኅበራዊ ሚዲያ ሲጠቀም የተቀመጠለትን የጊዜ ገደብ ለማክበር፣ ጥሩ ጓደኝነት ለመመሥረት እንዲሁም አጉል ነገሮችን እንቢ ለማለት ብስለቱ አለው? ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲጠቀም ከመፍቀዳችሁ በፊት ይህን በደንብ አስቡበት።

  የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብልህ . . . አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።”—ምሳሌ 14:15