በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በእምነታቸው ምሰሏቸው | መግደላዊቷ ማርያም

“ጌታን አየሁት!”

“ጌታን አየሁት!”

 መግደላዊቷ ማርያም እንባዋን እየጠራረገች ወደ ሰማይ ተመለከተች። የምትወደው ጌታዋ በእንጨት ላይ ተሰቅሏል። ወቅቱ ጸደይ፣ ሰዓቱ ደግሞ እኩለ ቀን ገደማ ቢሆንም “ምድሪቱ በሙሉ . . . በጨለማ ተሸፈነች”! (ሉቃስ 23:44, 45) ማርያም በትከሻዋ ላይ ያለውን መደረቢያ ሳብ አድርጋ አብረዋት ወዳሉት ሴቶች ጠጋ አለች። መቼም ምድሪቱ ሦስት ሰዓት ሙሉ በጨለማ የተዋጠችው በፀሐይ ግርዶሽ የተነሳ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም የፀሐይ ግርዶሽ የሚቆየው ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነው። ምናልባትም ማርያምና በኢየሱስ አቅራቢያ የነበሩት ሌሎች ሰዎች በምሽት ብቻ የሚወጡ እንስሳትን ድምፅ ሰምተው ሊሆን ይችላል። ሁኔታውን ይመለከቱ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች “እጅግ ፈርተው ‘ይህ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነበር’ አሉ።” (ማቴዎስ 27:54) የኢየሱስ ተከታዮችና ሌሎች ሰዎች ይህ ሁኔታ ይሖዋ በልጁ ላይ በተፈጸመው ግፍ የተነሳ የተሰማውን ሐዘንና ቁጣ የሚያሳይ እንደሆነ አስበው ሊሆን ይችላል።

 መግደላዊቷ ማርያም እየተከናወነ ያለውን ነገር ማየት በጣም ከባድ ቢሆንባትም ትታ መሄድ አልቻለችም። (ዮሐንስ 19:25, 26) ኢየሱስ በእጅጉ እየተሠቃየ እንደሆነ ግልጽ ነው። እናቱም ብትሆን ማጽናኛና ድጋፍ ያስፈልጋታል።

 ኢየሱስ ለመግደላዊቷ ማርያም ብዙ ነገር ስላደረገላት እሷም ውለታውን ለመክፈል የምትችለውን ሁሉ ለማድረግ ፈልጋ ነበር። ማርያም የተደቆሰችና በሰዎች የተናቀች ሰው ነበረች፤ ኢየሱስ ግን ከዚያ ነፃ አውጥቷታል። ሰብዓዊ ክብሯን መልሳ እንድታገኝና ሕይወቷ ዓላማ ያለው እንዲሆን አስችሏታል። አሁን ታላቅ እምነት ያላት ሴት መሆን ችላለች። እንዴት? እኛስ ከእሷ እምነት ምን ትምህርት እናገኛለን?

“በንብረታቸው ያገለግሏቸው ነበር”

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ስለ መግደላዊቷ ማርያም የሚጠቅሰው የመጀመሪያው ዘገባ ኢየሱስ ያደረገላትን አስደናቂ ነገር የሚገልጽ ነው። ኢየሱስ ማርያምን ከነበረችበት አስከፊ የባርነት ሕይወት ነፃ አውጥቷታል። በዘመኑ አጋንንት ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድሩ ነበር፤ በሰዎች ላይ ጥቃት ይሰነዝሩ አልፎ ተርፎም ሰዎች ውስጥ በመግባት ይቆጣጠሯቸው ነበር። አጋንንቱ ምስኪኗን ማርያምን ምን አድርገዋት እንደነበር አናውቅም፤ ሆኖም ሰባት አጋንንት አድረውባት እንደነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይናገራል። ኢየሱስ ግን ሁሉንም አጋንንት አስወጣላት!—ሉቃስ 8:2

 ማርያም ከአጋንንት ባርነት ነፃ በመውጣቷ ምን ያህል ተደስታ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፤ አሁን አዲስ ሕይወት መምራት ትችላለች። ታዲያ አመስጋኝነቷን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ማርያም የኢየሱስ ታማኝ ተከታይ ሆናለች። ከዚህም በተጨማሪ የበኩሏን ተግባራዊ እርዳታ ለማበርከት ጥረት አድርጋለች። ኢየሱስና ሐዋርያቱ ምግብ፣ ልብስ እንዲሁም ማደሪያ ያስፈልጋቸው ነበር። ሆኖም ሀብት የላቸውም፤ እንዲሁም በወቅቱ ሰብዓዊ ሥራ አይሠሩም ነበር። በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ላይ ማተኮር እንዲችሉ ቁሳዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸው ነበር።

 ማርያምና ሌሎች በርካታ ሴቶች ይህን ክፍተት ለመድፈን ጥረት አድርገዋል። እነዚህ ሴቶች ኢየሱስንና ሐዋርያቱን “በንብረታቸው ያገለግሏቸው ነበር።” (ሉቃስ 8:1, 3) አንዳንዶቹ ሴቶች ሀብት ይኖራቸው ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሴቶች ምን ያደርጉ እንደነበር በግልጽ ባይናገርም ምግብ በማብሰል፣ ልብስ በማጠብ አሊያም ኢየሱስና ሐዋርያቱ ወደተለያየ መንደር ሲሄዱ ማደሪያ በማመቻቸት አገልግለዋቸው ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፣ እነዚህ ሴቶች 20 ገደማ የሚሆኑትን ተጓዦች ለመደገፍ በፈቃደኝነት ይሠሩ እንደነበር ግልጽ ነው። የእነሱ ድጋፍ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ሙሉ ትኩረታቸውን በስብከቱ ሥራ ላይ እንዲያደርጉ ረድቷቸው መሆን አለበት። እርግጥ ነው፣ ማርያም ኢየሱስ ላደረገላት ነገር ውለታውን መክፈል እንደማትችል ታውቃለች፤ ሆኖም አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ ማድረጓ ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶላት ነበር።

 በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች፣ ሌሎችን ለማገልገል ሲሉ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ሰዎችን ይንቃሉ። አምላክ ግን እንደዚያ አይሰማውም። ማርያም ኢየሱስንና ሐዋርያቱን ለመደገፍ አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ በትጋት ስታደርግ ይሖዋ ምን ያህል ተደስቶ ሊሆን እንደሚችል አስበው! በዛሬው ጊዜም በርካታ ታማኝ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሌሎችን ያገለግላሉ። አሳቢነት የሚንጸባረቅበት ተግባር መፈጸም ወይም መልካም ቃል መናገር እንኳ ግሩም ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። ይሖዋ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎችን ከፍ አድርጎ ይመለከታል።—ምሳሌ 19:17፤ ዕብራውያን 13:16

“ኢየሱስ በተሰቀለበት የመከራ እንጨት አጠገብ”

 መግደላዊቷ ማርያም በ33 ዓ.ም. የፋሲካን በዓል ለማክበር ከኢየሱስ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ከተጓዙት በርካታ ሴቶች መካከል አንዷ ነበረች። (ማቴዎስ 27:55, 56) ኢየሱስ በዚያ ምሽት እንደታሰረና ሸንጎ ፊት እንደቀረበ ስታውቅ ማርያም በጣም ደንግጣ መሆን አለበት። ከዚህ የከፋው ደግሞ አገረ ገዢው ጳንጥዮስ ጲላጦስ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎችና ሕዝቡ ባሳደሩበት ተጽዕኖ ተሸንፎ ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ዘግናኝ በሆነ መንገድ እንዲገደል እንደፈረደበት ሰማች። ማርያም ጌታዋ ደም በደም ሆኖና ተጎሳቁሎ፣ የሚሰቀልበትን ረጅም እንጨት እየጎተተ በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ሲጓዝ ተመልክታው ሊሆን ይችላል።—ዮሐንስ 19:6, 12, 15-17

 ቀጥሎም ኢየሱስ ተሰቀለ፤ እኩለ ቀን ገደማ ምድሪቱ በጨለማ በተዋጠችበት ጊዜ መግደላዊቷ ማርያምና ሌሎች ሴቶች “ኢየሱስ በተሰቀለበት የመከራ እንጨት አጠገብ” ቆመው ነበር። (ዮሐንስ 19:25) ማርያም እስከ መጨረሻው በዚያ ቦታ የቆየች ሲሆን ኢየሱስ እናቱን እንዲንከባከብለት ለሐዋርያው ዮሐንስ አደራ ሲሰጠው ተመልክታ ነበር። ኢየሱስ በሥቃይ ወደ አባቱ ሲጮኽም አዳምጣለች። ልክ ከመሞቱ በፊት ደግሞ በድል አድራጊነት “ተፈጸመ” ሲል ሰምታለች። ማርያም በሐዘን ተደቁሳ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ከሞተ በኋላም ከቦታው የተንቀሳቀሰች አይመስልም። በኋላም የአርማትያሱ ዮሴፍ የተባለ ሀብታም ሰው የኢየሱስን አስከሬን በአዲስ መቃብር ውስጥ ሲያኖረው ማርያም በቦታው ነበረች።—ዮሐንስ 19:30፤ ማቴዎስ 27:45, 46, 57-61

 የማርያም ምሳሌ የእምነት አጋሮቻችን ከባድ መከራ ሲያጋጥማቸው ምን ማድረግ እንደምንችል ያስተምረናል። መከራ እንዳይደርስባቸው ማድረግ ወይም የደረሰባቸውን ችግር ማስወገድ አንችል ይሆናል። ሆኖም ርኅራኄና ድፍረት ማሳየት እንችላለን። አንድ ሰው ከባድ ችግር ሲያጋጥመው ታማኝ ወዳጁ አብሮት መሆኑ በራሱ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ችግር ካጋጠመው ወዳጃችን ጎን መቆማችን በእጅጉ የሚያጽናናው ከመሆኑም ሌላ ጠንካራ እምነት እንዳለን ያሳያል።—ምሳሌ 17:17

የኢየሱስ እናት ማርያም፣ መግደላዊቷ ማርያም አብራት በመኖሯ እንደተጽናናች ጥያቄ የለውም

“እኔም እወስደዋለሁ”

 የኢየሱስ አስከሬን መቃብር ውስጥ ከተቀመጠ በኋላ፣ አስከሬኑን ሊቀቡ ተጨማሪ ቅመሞች ከገዙት ሴቶች መካከል አንዷ ማርያም ነበረች። (ማርቆስ 16:1, 2፤ ሉቃስ 23:54-56) ሰንበት ካለፈ በኋላ መግደላዊቷ ማርያም በጠዋት ከእንቅልፏ ተነሳች። ማርያምና ሌሎቹ ሴቶች ገና ጎህ ሳይቀድ ወደ ኢየሱስ መቃብር ሲጓዙ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። መንገድ ላይ እያሉ፣ በመቃብሩ ደጃፍ ላይ ያለውን ትልቅ ድንጋይ እንዴት ማንከባለል እንደሚችሉ አሳስቧቸው ነበር። (ማቴዎስ 28:1፤ ማርቆስ 16:1-3) ሆኖም ወደ ኋላ አልተመለሱም። በይሖዋ ላይ እምነት ስለነበራቸው፣ የሚችሉትን ካደረጉ በኋላ የቀረውን ለይሖዋ ለመተው ወስነው እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል።

 ማርያም ከሌሎቹ ሴቶች ቀድማ መቃብሩ ጋ የደረሰች ይመስላል። በቦታው ከደረሰች በኋላ በድንጋጤ ቆመች። ድንጋዩ ተንከባሎ የነበረ ሲሆን መቃብሩም ባዶ ነበር! እርምጃ ለመውሰድ ፈጣን የሆነችው ማርያም እየሮጠች ወደ ጴጥሮስና ወደ ዮሐንስ ሄዳ ያየችውን ነገር ነገረቻቸው። ትንፋሿ እየተቆራረጠ “ጌታን ከመቃብሩ ውስጥ ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” ስትላቸው ይታይህ። ጴጥሮስና ዮሐንስ በፍጥነት ወደ መቃብሩ አመሩ፤ ከዚያም መቃብሩ ባዶ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ወደየቤታቸው ተመልሰው ሄዱ። aዮሐንስ 20:1-10

 ማርያም ወደ መቃብሩ ተመልሳ ከሄደች በኋላ ብቻዋን እዚያው ቆየች። ጭር ባለው በዚያ ማለዳ ባዶውን መቃብር ስታይ እንባዋን መቆጣጠር አልቻለችም። ጌታዋ አለመኖሩን ማመን አቅቷት ወደ መቃብሩ ውስጥ ለማየት ጎንበስ ስትል አስደንጋጭ ነገር አጋጠማት። ነጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት እዚያ ተቀምጠዋል! እነሱም “ለምን ታለቅሻለሽ?” በማለት ጠየቋት። እሷም ለሐዋርያቱ የነገረቻቸውን ነገር ለመላእክቱ ደገመችላቸው፤ “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳደረጉትም አላውቅም” አለቻቸው።—ዮሐንስ 20:11-13

 ዞር ስትል ከኋላዋ አንድ ሰው ቆሞ አየች። ሰውየው ማን መሆኑን ስላላወቀች የስፍራው አትክልተኛ ሊሆን እንደሚችል ገመተች። ሰውየው ደግነት በሚንጸባረቅበት ድምፅ “አንቺ ሴት፣ ለምን ታለቅሻለሽ? የምትፈልጊው ማንን ነው?” አላት። ማርያምም “ጌታዬ፣ አንተ ከዚህ ወስደኸው ከሆነ የት እንዳደረግከው ንገረኝ፤ እኔም እወስደዋለሁ” አለችው። (ዮሐንስ 20:14, 15) እስቲ አስበው። ጠንካራና ፈርጣማ ሰው የነበረውን የኢየሱስ ክርስቶስን አስከሬን አንዲት ሴት ብቻዋን ተሸክማ ልትወስድ የምትችለው እንዴት ነው? ማርያም ግን ይህ ሁሉ አላሳሰባትም። ማርያም ያሰበችው፣ የምትችለውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንዳለባት ብቻ ነው።

“እኔም እወስደዋለሁ”

 ያጋጠመን ችግር ወይም እንቅፋት ከአቅማችን በላይ እንደሆነ በሚሰማን ወቅት የመግደላዊቷን ማርያም ምሳሌ መከተል እንችል ይሆን? የምናተኩረው በድክመታችንና በአቅም ገደባችን ላይ ብቻ ከሆነ በፍርሃት ልንሽመደመድ እንችላለን። አቅማችን የፈቀደውን ነገር ሁሉ ለማድረግና የቀረውን ለአምላክ ለመተው ከቆረጥን ግን ከጠበቅነው በላይ ሊሳካልን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 12:10፤ ፊልጵስዩስ 4:13) ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋን እናስደስታለን። ማርያምም ይሖዋን እንዳስደሰተችው እርግጠኛ መሆን እንችላለን፤ ደግሞም አስገራሚ በሆነ መንገድ ወሮታ ከፍሏታል።

“ጌታን አየሁት!”

 ከማርያም ፊት ቆሞ የነበረው ሰው አትክልተኛው አልነበረም። ከፊቷ የቆመው በአንድ ወቅት አናጺ የነበረው፣ በኋላም መምህር የሆነው የምትወደው ጌታዋ ነበር። ማርያም ግን አላወቀችውም፤ ስለዚህ ትታው መሄድ ጀመረች። ማርያም ኢየሱስ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ ከሞት እንደተነሳ ልትገምት አትችልም። ኢየሱስ ለማርያም የታያት የሰው አካል ለብሶ ነው፤ ሆኖም የለበሰው መሥዋዕት ያደረገውን አካሉን አልነበረም። ከሞት ከተነሳ በኋላ በነበሩት አስደናቂ ቀናት ለተለያዩ ሰዎች በተገለጠበት ወቅት ከመሞቱ በፊት በደንብ ያውቁት የነበሩ ሰዎችም እንኳ ማንነቱን አላወቁም ነበር።—ሉቃስ 24:13-16፤ ዮሐንስ 21:4

 ታዲያ ኢየሱስ ለማርያም ማንነቱን ያሳወቃት እንዴት ነበር? “ማርያም!” ብሎ ጠራት፤ ስሟን የጠራበት መንገድ ማንነቱን አሳወቃት። እሷም በፍጥነት ፊቷን አዙራ “ራቦኒ!” አለችው፤ ማርያም ኢየሱስን ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ጊዜያት በዚህ የዕብራይስጥ ስም ጠርታው እንደምታውቅ ጥያቄ የለውም። ለካስ ከፊቷ የቆመው የምትወደው መምህሯ ነበር! ማርያም ልቧ በሐሴት ተሞላ። ኢየሱስን ጥብቅ አድርጋ ያዘችው፤ ልትለቀውም አልፈለገችም።—ዮሐንስ 20:16

 ኢየሱስ የማርያም ሐሳብ ገብቶት ነበር። “ጥብቅ አድርገሽ አትያዥኝ” አላት። ኢየሱስ ይህን ያላት ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ምናልባትም በፈገግታ እንደሚሆን መገመት እንችላለን፤ ቀስ ብሎ እጇን እያስለቀቀ “ገና ወደ አባቴ አላረግኩም” በማለት ሲያረጋጋት ይታይህ። ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚያርግበት ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር። በምድር ላይ የቀረው ሥራ ነበር፤ ማርያምም በሥራው እንድትካፈል ፈልጓል። ማርያም ኢየሱስ የሚላትን ለመስማት ጓጉታ እንደነበር ጥያቄ የለውም። “ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ላርግ ነው’ ብለሽ ንገሪያቸው” አላት።—ዮሐንስ 20:17

 ማርያም ጌታዋ ይህን ኃላፊነት ሲሰጣት ምንኛ ተደስታ ይሆን! ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ እሱን የማየት መብት ካገኙት የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዷ ማርያም ነች፤ አሁን ደግሞ ይህን ምሥራች ለሌሎችም የመናገር ልዩ ኃላፊነት ተሰጥቷታል። ማርያም ይህን ምሥራች ለደቀ መዛሙርቱ ለማብሰር ስትሄድ የነበራትን ደስታና ጉጉት መገመት ትችላለህ። ትንፋሿ እየተቆራረጠ “ጌታን አየሁት!” ብላ ስትነግራቸው ይታይህ፤ እነዚህ ቃላት በእሷም ሆነ በደቀ መዛሙርቱ አእምሮ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲያቃጭሉ እንደኖሩ ጥያቄ የለውም። ማርያም በደስታ ተሞልታ ኢየሱስ ያላትን ነገር በሙሉ ነገረቻቸው። (ዮሐንስ 20:18) የኢየሱስ መቃብር ጋ ሄደው የነበሩት ሌሎች ሴቶችም ለደቀ መዛሙርቱ ተመሳሳይ ነገር ነግረዋቸው ነበር።—ሉቃስ 24:1-3, 10

“ጌታን አየሁት!”

“ሴቶቹ የሚናገሩትን አላመኗቸውም”

 ታዲያ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን ምላሽ ሰጡ? መጀመሪያ ላይ የሰጡት ምላሽ ጥሩ አልነበረም። ጥቅሱ “እንዲሁ የሚቀባጥሩ ስለመሰላቸው ሴቶቹ የሚናገሩትን አላመኗቸውም” ይላል። (ሉቃስ 24:11) ደቀ መዛሙርቱ በራሳቸው ጥሩ ሰዎች ቢሆኑም ያደጉበት ማኅበረሰብ ሴቶችን ያለማመን ዝንባሌ ነበረው፤ እንዲያውም በረቢዎች ወግ መሠረት አንዲት ሴት ሸንጎ ፊት ቀርባ ምሥክርነት መስጠት አትችልም ነበር። ሐዋርያቱም ባሕላቸው ሳያስቡት ተጽዕኖ አሳድሮባቸው የነበረ ይመስላል። ኢየሱስና አባቱ ግን እንዲህ ዓይነት አድልዎ የሚንጸባረቅበት አመለካከት የላቸውም። ለዚያች ሴት ልዩ መብት ሰጥተዋታል!

 ማርያም በደቀ መዛሙርቱ ምላሽ ስሜቷ አልተጎዳም። ጌታዋ እንደሚያምናት ታውቃለች፤ ለእሷ ይህ በቂ ነበር። በተመሳሳይም ሁሉም የኢየሱስ ተከታዮች ለሌሎች የሚያደርሱት መልእክት ተሰጥቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መልእክት ‘የአምላክ መንግሥት ምሥራች’ በማለት ይጠራዋል። (ሉቃስ 8:1) ኢየሱስ ሁሉም ሰው መልእክታችንን እንደሚቀበል ወይም ሥራችንን እንደሚያደንቅ ቃል አልገባልንም። እንዲያውም ሁኔታው የዚህ ተቃራኒ ነው። (ዮሐንስ 15:20, 21) ስለዚህ ክርስቲያኖች መግደላዊቷ ማርያም የተወችውን ምሳሌ ማስታወሳቸው ጠቃሚ ነው። መንፈሳዊ ወንድሞቿ ባያምኗትም እንኳ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ የሚገልጸውን ምሥራች በደስታ ከመናገር ወደኋላ አላለችም!

 ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ለሐዋርያቱና ለሌሎች በርካታ ተከታዮቹ ተገልጧል። እንዲያውም በአንድ ወቅት ከ500 ለሚበልጡ ተከታዮቹ ታይቶ ነበር! (1 ቆሮንቶስ 15:3-8) ማርያም ኢየሱስን ባየችው ቁጥር ወይም መገለጡን በሰማች ቁጥር እምነቷ እያደገ እንደሄደ ጥርጥር የለውም። ምናልባትም በጴንጤቆስጤ ዕለት የኢየሱስ ተከታዮች በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ሳለ መንፈስ ቅዱስ በፈሰሰባቸው ወቅት በቦታው እንደነበሩ ከተጠቀሱት ሴቶች መካከል መግደላዊቷ ማርያም ሳትኖርበት አትቀርም።—የሐዋርያት ሥራ 1:14, 15፤ 2:1-4

 ያም ሆነ ይህ፣ መግደላዊቷ ማርያም እስከ መጨረሻው ጠንካራ እምነት ይዛ እንደቀጠለች ለማመን የሚያበቃ በቂ ምክንያት አለን። እኛም እንዲህ ዓይነት እምነት ለማዳበር ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ! ኢየሱስ ላደረገልን ነገር በሙሉ አመስጋኝ በመሆን እንዲሁም በአምላክ እርዳታ ታምነን ወንድሞቻችንን በትሕትና በማገልገል መግደላዊቷ ማርያምን በእምነቷ መምሰል እንችላለን።

a መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶቹ አንድ መልአክ እንዳገኙና መልአኩም የኢየሱስን መነሳት እንደነገራቸው ይገልጻል፤ ሆኖም በወቅቱ ማርያም ከቦታው ሄዳ የነበረ ይመስላል። ማርያም መልአኩን አግኝታው የነበረ ቢሆን ኖሮ ወደ ጴጥሮስና ወደ ዮሐንስ በሄደችበት ወቅት አንድ መልአክ እንዳገኘችና መልአኩ የኢየሱስ አስከሬን በቦታው ያልተገኘው ለምን እንደሆነ እንዳብራራላት ትነግራቸው እንደነበር ጥያቄ የለውም።—ማቴዎስ 28:2-4፤ ማርቆስ 16:1-8