በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በእምነታቸው ምሰሏቸው | ዮናታን

‘ይሖዋ ከማዳን የሚያግደው ነገር የለም’

‘ይሖዋ ከማዳን የሚያግደው ነገር የለም’

 ደረቅና ዓለታማ በሆነ አካባቢ የሚገኝ አንድ የጦር ሰፈር በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። በዚያ የጦር ሰፈር የሚገኙት ፍልስጤማውያን ወታደሮች በርቀት ትኩረት የሚስብ ነገር ተመለከቱ፦ ከሸለቆው ማዶ በግልጽ በሚታይ ቦታ ላይ ሁለት እስራኤላውያን ቆመዋል። ወታደሮቹ ሁለቱን ሰዎች ሲያዩ ቢገረሙም ስጋት አላደረባቸውም። ፍልስጤማውያን እስራኤላውያንን ለረጅም ጊዜ ሲገዟቸው ቆይተዋል፤ እንዲያውም እስራኤላውያን የግብርና መሣሪያዎቻቸውን ለማሳል እንኳ ወደ ፍልስጤማውያን መሄድ ነበረባቸው። በዚህም ምክንያት እስራኤላውያን ወታደሮች ጥሩ የጦር ትጥቅ አልነበራቸውም። በዚያ ላይ ደግሞ ከማዶ የሚታዩት ሰዎች ሁለት ብቻ ናቸው! ሁለቱ ሰዎች የታጠቁ ጦረኞች ቢሆኑ እንኳ ምን ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ? ፍልስጤማውያኑ በንቀት እያዩአቸው “ኑ፣ ወደ እኛ ውጡ፤ እናሳያችኋለን!” አሏቸው።—1 ሳሙኤል 13:19-23፤ 14:11, 12

 በእርግጥም ይህ አጋጣሚ ትልቅ ትምህርት የሚገኝበት ነው፤ ሆኖም ከዚህ ክንውን ትምህርት ያገኙት እስራኤላውያን ሳይሆኑ ፍልስጤማውያኑ ራሳቸው ናቸው። ሁለቱ እስራኤላውያን እየተንደረደሩ ወርደው ሸለቆውን ከተሻገሩ በኋላ ሽቅብ መውጣት ጀመሩ። ዳገቱ ቀጥ ያለ ስለነበር በእጅና በእግራቸው እየቧጠጡ መውጣት ነበረባቸው፤ ያም ቢሆን እየወደቁ እየተነሱ አቀበቱን በመውጣት በቀጥታ ወደ ጦር ሰፈሩ አመሩ! (1 ሳሙኤል 14:13) በዚህ ጊዜ ፍልስጤማውያኑ፣ ከፊት እየመራ ያለው እስራኤላዊ የታጠቀ መሆኑንና ከኋላውም ጋሻ ጃግሬው እንዳለ ተመለከቱ። ሆኖም ይህ እስራኤላዊ ጋሻ ጃግሬውን አስከትሎ የመጣው መላውን የጦር ሰፈር ማጥቃት እንደሚችል አስቦ ነው? ሰውየው አብዷል እንዴ?

 ሰውየው አላበደም፤ እንዲያውም ታላቅ እምነት ያለው ሰው ነው። ይህ ሰው ዮናታን ሲሆን ታሪኩም በዛሬው ጊዜ ላሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶችን ይዟል። በዛሬው ጊዜ ቃል በቃል በጦርነት ባንካፈልም እንኳ እውነተኛ እምነት ለመገንባት የሚያስፈልጉንን ባሕርያት ይኸውም ድፍረትንና ታማኝነትን እንዲሁም ራስ ወዳድ አለመሆንን በተመለከተ ከዮናታን ብዙ መማር እንችላለን።—ኢሳይያስ 2:4፤ ማቴዎስ 26:51, 52

ለአባቱ ታማኝ የሆነ ጀግና ወታደር

 ዮናታን በዚያ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት የሰነዘረው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ይህ ሰው ስላሳለፈው ሕይወት ማወቅ ያስፈልገናል። ዮናታን፣ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ የሆነው የሳኦል የበኩር ልጅ ነው። ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሲቀባ ዮናታን 20 ዓመቱ ወይም ከዚያ በላይ መሆን አለበት። ዮናታን ከአባቱ ጋር በጣም ይቀራረብ የነበረ ይመስላል፤ አባቱም ብዙ ጊዜ ሚስጥሩን ያካፍለው ነበር። በእነዚያ ዓመታት ዮናታን፣ አባቱ ቁመናው ዘለግ ያለና መልከ ቀና የሆነ ደፋር ተዋጊ ከመሆኑም ባሻገር አስፈላጊ የሆኑት ባሕርያት ይኸውም እምነትና ትሕትና ያለው ሰው መሆኑን ማስተዋል ይችል ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ሳኦልን ንጉሥ አድርጎ መምረጡ ዮናታንን አላስገረመውም። ነቢዩ ሳሙኤልም እንኳ ከሕዝቡ መካከል እንደ ሳኦል ያለ ሰው እንደሌለ ተናግሯል!—1 ሳሙኤል 9:1, 2, 21፤ 10:20-24፤ 20:2

 ዮናታን በአባቱ ሥር ሆኖ ከይሖዋ ሕዝብ ጠላቶች ጋር መዋጋትን እንደ ክብር ቆጥሮት መሆን አለበት። እነዚያ ጦርነቶች በዛሬው ጊዜ እንዳሉት ብሔራዊ ስሜት የሚንጸባረቅባቸው ውጊያዎች አልነበሩም። በዚያ ወቅት ይሖዋ እሱን እንዲወክል የእስራኤልን ብሔር መርጦ ነበር፤ የሐሰት አማልክት የሚያመልኩ ሌሎች ብሔራት ደግሞ በእስራኤላውያን ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ይሰነዝሩ ነበር። እንደ ዳጎን ያሉትን የሐሰት አማልክት የሚያመልኩት ፍልስጤማውያን የይሖዋን ምርጥ ሕዝብ ለመጨቆን ይባስ ብሎም ለማጥፋት ብዙ ጊዜ ይጥሩ ነበር።

 በመሆኑም በዚያ ዘመን የነበሩ እንደ ዮናታን ያሉ ሰዎች፣ ከጠላቶቻቸው ጋር የሚያደርጉት ውጊያ ለይሖዋ አምላክ ታማኝነታቸውን የሚያሳዩበት መንገድ ነበር። ደግሞም ይሖዋ የዮናታንን ጥረት ባርኮለታል። ሳኦል ንጉሥ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ልጁን በ1,000 ወታደሮች ላይ የጦር አዛዥ አድርጎ ሾመው፤ ዮናታንም ሠራዊቱን ይዞ በጌባ በነበረው የፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ሰነዘረ። ዮናታን ያዘመታቸው ሰዎች በቂ የጦር ትጥቅ ባይኖራቸውም በይሖዋ እርዳታ በውጊያው ማሸነፍ ችለዋል። ፍልስጤማውያኑ ይህንን ሲያዩ እጅግ ብዙ የሆነ ሠራዊት ይዘው ለውጊያ ተሰበሰቡ። በዚህ ጊዜ ብዙዎቹ የሳኦል ወታደሮች በፍርሃት ተርበደበዱ። አንዳንዶቹ ሸሽተው ተደበቁ፤ ጥቂቶች ደግሞ ጭራሽ ከፍልስጤማውያን ሠራዊት ጋር ወገኑ! ያም ቢሆን ዮናታን ወኔው አልከዳውም።—1 ሳሙኤል 13:2-7፤ 14:21

 በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰውን ታሪክ መለስ ብለን እንመልከት፤ በዚያ ዕለት ዮናታን ማንም ሳያውቅ ወደ ፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ጋሻ ጃግሬውን ብቻ አስከትሎ ለመሄድ ወሰነ። በሚክማሽ ወዳለው የፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ሲቃረቡ ዮናታን ለጋሻ ጃግሬው ዕቅዱን ነገረው። ዮናታን፣ እሱና ጋሻ ጃግሬው በማዶ ላሉት የፍልስጤማውያን ወታደሮች በግልጽ በሚታዩበት ቦታ ላይ እንዲቆሙ አስቦ ነበር። ፍልስጤማውያኑ ሁለቱን ሰዎች መጥተው ውጊያ እንዲገጥሟቸው ከጠሯቸው ይህ ይሖዋ አገልጋዮቹን እንደሚረዳቸው ምልክት ይሆናል። ጋሻ ጃግሬውም በዮናታን ዕቅድ ያላንዳች ማንገራገር ተስማማ፤ ይህን ያደረገው ዮናታን ቀጥሎ የተናገረው ሐሳብ ስላደፋፈረው ሊሆን ይችላል፤ ዮናታን “ይሖዋ በብዙም ሆነ በጥቂት ሰዎች ተጠቅሞ ከማዳን የሚያግደው ነገር [የለም]” ብሎ ነበር። (1 ሳሙኤል 14:6-10) ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር?

 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ዮናታን አምላኩን በደንብ የሚያውቅ ሰው ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት እስራኤላውያን በቁጥር በጣም የሚበልጧቸውን ጠላቶቻቸውን ድል እንዲያደርጉ ይሖዋ እንደረዳቸው ዮናታን ያውቅ ነበር። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ በአንድ ግለሰብ ብቻ ተጠቅሞ ሕዝቡን ድል እንዲጎናጸፉ ረድቷቸዋል። (መሳፍንት 3:31፤ 4:1-23፤ 16:23-30) በመሆኑም ዮናታን፣ የአምላክ አገልጋዮች በውጊያ እንዲያሸንፉ የሚረዳቸው የሠራዊታቸው ብዛት፣ ጥንካሬያቸው አሊያም የጦር መሣሪያቸው ሳይሆን እምነታቸው መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ስለዚህ ዮናታን፣ እሱና ጋሻ ጃግሬው በፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት መሰንዘር እንዳለባቸው ለመወሰን የሚያስችለው ምልክት ይሖዋ እንዲያሳየው በእምነት ጠየቀ። ዮናታን ይሖዋ እንደሚደግፈው ማረጋገጫ ሲያገኝ ያላንዳች ፍርሃት ወደፊት ገሰገሰ።

 የዮናታን እምነት የታየባቸውን ሁለት መንገዶች እስቲ እንመልከት። አንደኛ፣ ዮናታን ለአምላኩ ለይሖዋ ጥልቅ አክብሮታዊ ፍርሃት ነበረው። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ዓላማውን ለማስፈጸም የሰዎች ድጋፍ ባያስፈልገውም እሱን የሚያገለግሉትን ታማኝ ሰዎች መባረክ እንደሚያስደስተው ዮናታን ያውቅ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 16:9) ሁለተኛ፣ ዮናታን እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ዕቅዱ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው የሚያረጋግጥለት ማስረጃ ለማግኘት ጥሯል። በዛሬው ጊዜ የምንኖር ክርስቲያኖች፣ አምላክ የምንወስደው እርምጃ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ለየት ያለ ምልክት እንዲያሳየን አንጠብቅም። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ሙሉው የአምላክ ቃል በእጃችን ስላለ የአምላክን ፈቃድ ለማስተዋል የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ አለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ታዲያ በጣም አስፈላጊ ውሳኔዎችን ከማድረጋችን በፊት መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ እንመረምራለን? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ልክ እንደ ዮናታን ከራሳችን ፍላጎት ይበልጥ የሚያሳስበን የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ እናሳያለን።

 ከላይ እንዳየነው ሁለቱ ሰዎች ማለትም ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው ወደ ጠላት የጦር ሰፈር የሚወስደውን ቀጥ ያለ አቀበት በፍጥነት ወጡ። በዚህ ጊዜ ፍልስጤማውያን ጥቃት እየተሰነዘረባቸው እንደሆነ ስለተገነዘቡ ሁለቱን ወራሪዎች እንዲመክቱ ሰዎች ላኩ። ፍልስጤማውያኑ እስራኤላውያኑን በቁጥር በጣም የሚበልጧቸው ከመሆኑም ሌላ ከመሬቱ አቀማመጥ አንጻር ከፍ ያለ ቦታ ላይ ስለነበሩ ሁለቱን ወራሪዎች በቀላሉ መግደል ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ ዮናታን ወታደሮቹን አንድ በአንድ እየመታ ረፈረፋቸው። ጋሻ ጃግሬውም ከኋላው እየተከተለ ገደላቸው። ሁለቱ ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ 20 የጠላት ወታደሮችን ገደሉ! ይሖዋም እነሱን ለመርዳት ተጨማሪ ነገር አደረገ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ከዚያም በእርሻው ውስጥ በሰፈረው ሠራዊትና በጦር ሰፈሩ ውስጥ በነበረው ሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ተነዛ፤ ሌላው ቀርቶ ወራሪ ቡድኖቹ እንኳ ተሸበሩ። ምድሪቱም መንቀጥቀጥ ጀመረች፤ ከአምላክ የመጣ ሽብርም ወረደባቸው።”—1 ሳሙኤል 14:15

ዮናታን ከጋሻ ጃግሬው ጋር በመሆን በሚገባ የታጠቁ የጠላት ወታደሮች ባሉበት የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ሰንዝሯል

 ሳኦልና ከእሱ ጋር ያሉት ሰዎች ከርቀት ሆነው በፍልስጤማውያን ሰፈር ሽብርና ሁከት እንደተፈጠረ ተመለከቱ፤ እንዲያውም ፍልስጤማውያኑ እርስ በርሳቸው መጨፋጨፍ ጀመረው ነበር! (1 ሳሙኤል 14:16, 20) በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ለማጥቃት ተደፋፈሩ፤ ምናልባትም ጥቃት የሰነዘሩት፣ ከሞቱት ፍልስጤማውያን ላይ በወሰዱት የጦር መሣሪያ ሊሆን ይችላል። በዚያ ቀን ይሖዋ ሕዝቡን ታላቅ ድል አጎናጸፈ። ይሖዋ አሁንም አልተለወጠም። ዮናታንና ስሙ ያልተገለጸው ጋሻ ጃግሬው እንዳደረጉት ሁሉ እኛም በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ላይ እምነት ከጣልን ባደረግነው ምርጫ ፈጽሞ አንቆጭም።—ሚልክያስ 3:6፤ ሮም 10:11

“ይህን ያደረገው ከአምላክ ጋር ሆኖ ነው”

 ይህ ድል ለሳኦል የዮናታንን ያህል መልካም ውጤት አላስገኘለትም። ሳኦል ከባድ ጥፋቶች ሠርቷል። ሳኦል፣ ይሖዋ የሾመው ነቢይና ሌዋዊ የሆነው ሳሙኤል ሊያቀርብ የሚገባውን መሥዋዕት በማቅረብ የነቢዩን ትእዛዝ ጥሷል። ሳኦል ባለመታዘዙ ምክንያት መንግሥቱ እንደማይዘልቅ ሳሙኤል ሲመጣ ነግሮታል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ሳኦል ሰዎቹን ወደ ጦርነት በሚልክበት ጊዜ “ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት እስከ ማታ ድረስ እህል የሚቀምስ ሰው የተረገመ ይሁን!” በማለት ሕዝቡን ጥበብ የጎደለው መሐላ አስማላቸው።—1 ሳሙኤል 13:10-14፤ 14:24

 ሳኦል የተናገራቸው ቃላት ባሕርይው እየተበላሸ መሆኑን የሚጠቁሙ ነበሩ። ትሑትና መንፈሳዊ አመለካከት የነበረው ሳኦል ታላቅ የመሆን ምኞት የተጠናወተው ራስ ወዳድ ሰው ሊሆን ነው እንዴ? ይሖዋ ከሳኦል ጋር በነበሩት ጀግናና ታታሪ ወታደሮች ላይ እንደዚህ ያለ ምክንያተ ቢስ እገዳ እንዲጣል ፈጽሞ አላዘዘም። ደግሞስ ሳኦል “ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት” በማለት መናገሩ ምን ያሳያል? ይህ ጦርነት ለእሱ ክብር ለማምጣት ተብሎ የሚደረግ እንደሆነ ማሰቡን የሚጠቁም ይሆን? ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ዋናው ነገር የይሖዋ ፍትሕ መፈጸሙ እንጂ ሳኦል የበቀል፣ የክብር ወይም ድል የማግኘት ጥማቱን ማርካቱ እንዳልሆነ ዘንግቶት ይሆን?

 ዮናታን፣ አባቱ ሕዝቡን ስላስማለው ጥበብ የጎደለው መሐላ ምንም ያወቀው ነገር አልነበረም። የተፋፋመው ጦርነት አድክሞት ስለነበር በእጁ የያዘውን በትር የማር እንጀራ ውስጥ አጥቅሶ ማሩን ቀመሰ፤ ወዲያውኑም ብርታቱ ሲመለስለት ተሰማው። ከዚያም ከሕዝቡ መካከል አንዱ፣ አባቱ ማንም ሰው ምግብ እንዳይቀምስ መከልከሉን ነገረው። በዚህ ጊዜ ዮናታን እንዲህ አለ፦ “አባቴ በምድሪቱ ላይ ከባድ ችግር አምጥቷል። እኔ ይህችን ማር በመቅመሴ ዓይኖቼ እንዴት እንደበሩ እስቲ ተመልከቱ። ሕዝቡ ከጠላቶቻቸው ከወሰዱት ምርኮ ዛሬ በነፃነት በልተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር! የተገደሉት ፍልስጤማውያንም ቁጥር ከዚህ እጅግ በበለጠ ነበር።” (1 ሳሙኤል 14:25-30) ዮናታን የተናገረው ነገር ትክክል ነው። ዮናታን ለአባቱ ታማኝ ልጅ ቢሆንም ጭፍን ታማኝነት አላሳየም። አባቱ የሚያደርገውን ወይም የሚናገረውን ሁሉ ምንም ሳያንገራግር የሚቀበል ሰው አልነበረም፤ እንዲህ ያለ ሚዛናዊ አመለካከት ያለው ሰው መሆኑ ደግሞ የሌሎችን አክብሮት አትርፎለታል።

 በኋላ ላይ ሳኦል፣ ዮናታን መሐላውን እንደጣሰ አወቀ፤ በዚህ ጊዜም ቢሆን፣ እሱ የሰጠው ትእዛዝ የተሳሳተ እንደሆነ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። እንዲያውም የራሱን ልጅ ለመግደል ተነሳ! ዮናታንም ከአባቱ ጋር አልተከራከረም ወይም ምሕረት እንዲደረግለት አልለመነም። የሰጠው ምላሽ አስደናቂ ነው። ለሕይወቱ ምንም ሳይሳሳ “እንግዲህ ይኸው ለመሞት ዝግጁ ነኝ!” አለ። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን እንዲህ አሉ፦ “ለእስራኤል ይህን ታላቅ ድል ያስገኘው ዮናታን መሞት ይገባዋል? ይሄማ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው! ሕያው በሆነው በይሖዋ እንምላለን፣ ከራስ ፀጉሩ አንዷ እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም፤ ምክንያቱም በዚህ ዕለት ይህን ያደረገው ከአምላክ ጋር ሆኖ ነው።” ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ሳኦል ሰዎቹ በተናገሩት አሳማኝ ሐሳብ ተሸነፈ። ዘገባው “በዚህ መንገድ ሕዝቡ ዮናታንን ታደገው፤ እሱም ከሞት ዳነ” ይላል።—1 ሳሙኤል 14:43-45

“እንግዲህ ይኸው ለመሞት ዝግጁ ነኝ!”

 ዮናታን ደፋር፣ ታታሪና ለራሱ የማይሳሳ ሰው በመሆኑ በሌሎች ዘንድ መልካም ስም አትርፏል። ያተረፈው መልካም ስም፣ ሕይወቱ አደጋ ላይ በወደቀበት ወቅት ጠቅሞታል። እኛም በየዕለቱ ምን ዓይነት ስም እያተረፍን እንደሆነ በጥሞና ማሰባችን የተገባ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ስም እጅግ ውድ ነገር እንደሆነ ይነግረናል። (መክብብ 7:1) እኛም እንደ ዮናታን በይሖዋ ዘንድ መልካም ስም ለማትረፍ የምንጥር ከሆነ መልካም ስማችን እንደ ውድ ሀብት ይሆንልናል።

ችግሩ እየተባባሰ ሄደ

 ሳኦል ስህተቶችን ቢሠራም ዮናታን በታማኝነት ከአባቱ ጎን ሆኖ ተዋግቷል። አባቱ ያለመታዘዝና የኩራት መንፈስ እያዳበረ መሆኑን ሲያይ ዮናታን ምን ያህል ሊያዝን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። የአባቱ ችግር እየተባባሰ ሲሆን ዮናታን ደግሞ ይህን ለማስቆም ምንም ማድረግ አይችልም።

 ችግሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ሳኦል አማሌቃውያንን እንዲወጋ ይሖዋ ባዘዘው ጊዜ ነው፤ አማሌቃውያን ክፋታቸው በጣም ከመብዛቱ የተነሳ ይሖዋ መላው ብሔር እንደሚጠፋ በሙሴ ዘመን ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ዘፀአት 17:14) ሳኦል እንስሶቻቸውን በሙሉ እንዲያጠፋና ንጉሣቸውን አጋግን እንዲገድለው ተነግሮት ነበር። ሳኦል በጦርነቱ አሸነፈ፤ ዮናታንም እንደተለመደው በአባቱ ሥር ሆኖ በጀግንነት እንደተዋጋ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ሳኦል የይሖዋን ትእዛዝ ሆን ብሎ በመጣስ አጋግን ከነሕይወቱ ማረከው፤ እንስሳቱንም አላጠፋም። በመሆኑም ነቢዩ ሳሙኤል “አንተ የይሖዋን ቃል ስላልተቀበልክ እሱም የአንተን ንግሥና አልተቀበለውም” በማለት ይሖዋ በሳኦል ላይ ያሳለፈውን የመጨረሻ ፍርድ ነገረው።—1 ሳሙኤል 15:2, 3, 9, 10, 23

 ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሳኦል የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ራቀው። ሳኦል አፍቃሪ የሆነው አምላክ ጥበቃ ስለተለየው ባሕርይው በጣም ይለዋወጥና ግልፍተኝነት ይታይበት ጀመር፤ በተጨማሪም ኃይለኛ ፍርሃት አደረበት። ሳኦል ቀድሞ በነበረው ጥሩ መንፈስ ፋንታ ከአምላክ ዘንድ መጥፎ መንፈስ የመጣበት ያህል ነበር። (1 ሳሙኤል 16:14፤ 18:10-12) ዮናታን፣ በአንድ ወቅት የተከበረ ሰው የነበረው አባቱ እንዲህ ተለውጦ መጥፎ ሰው እንደሆነ ማየቱ ምንኛ አሳዝኖት ይሆን! ያም ቢሆን ዮናታን ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሉን አልተወም። ዮናታን በተቻለው መጠን አባቱን ለመደገፍ ጥረት ያደረገ ሲሆን እንዲያውም አባቱ እየተሳሳተ መሆኑን በግልጽ ነግሮታል፤ ሆኖም ይበልጥ ትኩረት ያደረገው በሰማይ ባለው የማይለዋወጥ አባቱ ይኸውም በይሖዋ አምላክ ላይ ነበር።—1 ሳሙኤል 19:4, 5

 አንተስ የምትወደው ሰው ምናልባትም የቅርብ የቤተሰብህ አባል መጥፎ አካሄድ ለመከተል ሲመርጥ ተመልክተህ ታውቃለህ? እንዲህ ያለው ሁኔታ ጥልቅ ሐዘን ያስከትላል። የዮናታን ምሳሌ ከጊዜ በኋላ መዝሙራዊው የጻፈውን “የገዛ አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ ይሖዋ ራሱ ይቀበለኛል” የሚለውን ሐሳብ ያስታውሰናል። (መዝሙር 27:10) ይሖዋ ታማኝ ነው። ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች አንተን ሊያሳዝን ወይም ሊያስከፋ የሚችል ምንም ነገር ቢያደርጉ እንኳ ይሖዋ ይቀበልሃል፤ እንዲሁም ከማንም የላቀ አባት ይሆንልሃል።

 ዮናታን፣ ይሖዋ ንግሥናውን ከሳኦል ለመውሰድ እንዳሰበ ሳያውቅ አይቀርም። ታዲያ ዮናታን ምን ተሰማው? እሱ ቢነግሥ ምን ዓይነት ገዢ እንደሚሆን አስቦ ይሆን? አባቱን ተክቶ ቢነግሥ ሳኦል ከሠራቸው ስህተቶች አንዳንዶቹን እንደሚያስተካክል ብሎም ታማኝና ታዛዥ ንጉሥ በመሆን ጥሩ ምሳሌ እንደሚተው ተስፋ አድርጎ ይሆን? ዮናታን ምን ያስብ እንደነበረ አናውቅም፤ የምናውቀው ነገር ቢኖር እንደዚህ ዓይነት ተስፋዎች ቢኖሩት እንኳ አንዳቸውም እንዳልተፈጸሙ ነው። ይህ መሆኑ ታዲያ ይሖዋ ያንን ታማኝ ሰው እንደተወው የሚያሳይ ነው? በፍጹም! ይሖዋ፣ የዮናታን ታሪክ ታማኝ ወዳጅ በመሆን ረገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሰፈሩት ግሩም ምሳሌዎች አንዱ ሆኖ እንዲመዘገብ አድርጓል! ስለ ዮናታን ወደፊት በሚወጣ ርዕስ ላይ ስለዚህ ወዳጅነት ይብራራል።