በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ንድፍ አውጪ አለው?

ፓይለት ዌል የተባለው ዓሣ ነባሪ ቆዳውን የሚያጸዳበት መንገድ

ፓይለት ዌል የተባለው ዓሣ ነባሪ ቆዳውን የሚያጸዳበት መንገድ

 እንደ ባርናክሎች ያሉ በመርከብ አካል ላይ የሚጣበቁ የባሕር ፍጥረታት ከመርከብ ጋር የተያያዘ ሥራ ለሚሠሩ ድርጅቶች ከባድ ችግር ይፈጥራሉ። እነዚህ ፍጥረታት በመርከቦች ላይ መጣበቃቸው የመርከቦቹ ፍጥነት እንዲቀንስና የነዳጅ ፍጆታቸው እንዲጨምር ያደርጋል፤ በተጨማሪም መርከቦቹ በየሁለት ዓመት ገደማ መጽዳት ስላለባቸው ለተወሰነ ጊዜ ያህል አገልግሎት መስጠታቸውን ለማቆም ይገደዳሉ። በመሆኑም የሳይንስ ሊቃውንት መፍትሔ ለማግኘት በአንዳንድ ፍጥረታት ላይ ምርምር እያደረጉ ነው።

 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ባለ ረጅም ክንፉ ፓይለት ዌል (ግሎቢሲፋላ ሚላስ) ራሱን በራሱ ማጽዳት የሚችል ቆዳ እንዳለው በመስኩ የተደረጉ ጥናቶች አሳይተዋል። ቆዳው ናኖሪጅስ በተባሉ ጥቃቅን ሸንተረሮች የተሸፈነ ነው፤ እነዚህ ሸንተረሮች በጣም ትናንሽ ስለሆኑ የባርናክል እጮች ራሳቸውን ሊያጣብቁባቸው አይችሉም። በሸንተረሮቹ መካከል ያሉት ክፍተቶች ደግሞ አልጌ እና ባክቴሪያን በሚያጠቃ ዝልግልግ ነገር የተሞሉ ናቸው። ዓሣ ነባሪው ቆዳው ተገልፍፎ በወደቀ ቁጥር አዲስ ዝልግልግ ፈሳሽ ያመነጫል።

 የሳይንስ ሊቃውንት ይህ ዓሣ ነባሪ ራሱን ለማጽዳት የሚጠበቅምበትን ዘዴ በመርከቦች ላይ ለመጠቀም አስበዋል። ቀደም ሲል የባሕር ፍጥረታትን ለማራቅ ሲሉ የመርከቡን አካል እነዚህን ፍጥረታት የሚያባርር ኬሚካል ይቀቡት ነበር። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቀሙባቸው ኬሚካሎች ለባሕር ፍጥረታት መርዛማ ሆነው ስለተገኙ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ተከልክለዋል። ተመራማሪዎቹ ያገኙት መፍትሔ የመርከቦቹን አካል በባሕር ፍጥረታት ላይ ጉዳት የማያስከትል ኬሚካል በሚተፉ መደዳውን የተደረደሩ ብዙ ቀዳዳዎች ከሸፈኑት በኋላ ቀዳዳዎቹን ከብረት በተሠራ ወንፊት መሸፈን ነው። ኬሚካሉ ከባሕር ውኃ ጋር ሲገናኝ ወፍራም ዝልግልግ ሽፋን በመፍጠር ውኃ ውስጥ ያለውን የመርከቡን አካል በሙሉ ያለብሰዋል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ 0.7 ሚሊ ሜትር ውፍረት ያለው ይህ ሽፋን በላዩ ላይ የተጣበቁትን የባሕር ፍጥረታት ሁሉ ይዞ ተገልፍፎ ይወድቃል። ከዚያም የመርከቡን አካል የሚሸፍን ዝልግልግ ፈሳሽ እንደገና ይመነጫል።

ባርናክሎች የመርከቦችን ፍጥነት የሚቀንሱ ከመሆኑም ሌላ ለማስወገድ አስቸጋሪ ናቸው

 መርከቡ እንዲህ ያለ ችሎታ እንዲኖረው መደረጉ በመርከቡ ላይ የሚጣበቁትን የባሕር ፍጥረታት በመቶ እጥፍ ሊቀንሳቸው እንደሚችል የቤተ ሙከራ ምርምሮች አሳይተዋል። ይህ ደግሞ ለመርከብ ኩባንያዎች ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል፤ ምክንያቱም መርከቡን ከባሕር አውጥቶ ማጽዳት ብዙ ወጪ ይጠይቃል።

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? ፓይለት ዌል ያለው ራሱን በራሱ የማጽዳት ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?