በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ንድፍ አውጪ አለው?

የባርናክሎች ሙጫ

የባርናክሎች ሙጫ

 የሥነ እንስሳት ተመራማሪዎች፣ ባርናክሎች ከድንጋዮች፣ ከወደብ መድረኮችና ከመርከቦች ጋር ሙጭጭ ብለው እንደሚጣበቁ ካስተዋሉ ብዙ ዘመናት ተቆጥረዋል። የባርክሎች ሙጫ ከየትኛውም ሰው ሠራሽ ሙጫ የበለጠ ኃይል አለው። ባርናክሎች እርጥበት ካላቸው ነገሮች ጋር የሚጣበቁበት መንገድ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንቆቅልሽ ሆኖ ቆይቷል።

 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ መዋኘት የጀመረ የባርናክል እጭ፣ የሚጣበቅበትን ቦታ ከመምረጡ በፊት የተለያዩ ነገሮች ላይ ለመጣበቅ እንደሚሞክር ጥናቶች ያሳያሉ። እጩ ለመጣበቅ የሚያመች ቦታ ሲያገኝ ሁለት ኬሚካሎችን እንደሚያመነጭ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ። መጀመሪያ ላይ የሚያመነጨው፣ በሚጣበቅበት ቦታ ላይ ያለውን ውኃ የሚያስወግድ ቅባታማ የሆነ ፈሳሽ ነው። ይህ ቅባታማ ፈሳሽ፣ ፎስፎፕሮቲን ከሚባሉ ፕሮቲኖች የተሠራው ሁለተኛው ኬሚካል እንዲጣበቅ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

 ሁለቱ ኬሚካሎች በባክቴሪያዎች እንኳ ሊበላሽ የማይችል ጠንካራ ሙጫ ይፈጥራሉ። ባርናክሉ ዕድሜ ልኩን እዚያ ቦታ ላይ ተጣብቆ ስለሚኖር ሙጫው በጣም ጠንካራ መሆኑ አስፈላጊ ነው።

ባርናክሎች እና የባርናክሎች ሙጫ ጎላ ተደርጎ ሲታይ

 ባርናክሎች ሙጫ የሚሠሩበት መንገድ ቀደም ሲል ይታሰብ ከነበረው ይበልጥ እጅግ የተወሳሰበ ነው። ይህን ውስብስብ ሂደት ያገኘው ቡድን አባል የሆነ አንድ ተመራማሪ “እርጥበት ላለበት ቦታ የሚሆን ግሩም የሆነ ተፈጥሯዊ መፍትሔ ነው” ብሏል። ይህ ግኝት ውኃ ውስጥ ማጣበቅ የሚችሉ ሙጫዎች ለመሥራት እንዲሁም ለኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችና ለሕክምና ሊውል የሚችል ከተፈጥሯዊ ንጥረ ነገሮች የተቀመመ ሙጫ ለማዘጋጀት እንደሚያስችል ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? የባርናክሎች ሙጫ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?