በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

BluePlanetArchive/Whale Watch Azores

ንድፍ አውጪ አለው?

ረጅም ርቀት የሚጠልቁ ዓሣ ነባሪዎች

ረጅም ርቀት የሚጠልቁ ዓሣ ነባሪዎች

 ኩቪየርስ ቢክድ ዌል የተባለው ዓሣ ነባሪ 2,992 ሜትር ድረስ መጥለቅ ይችላል፤ በዚያ ያለው የውኃ ግፊት 30,300 ኪሎፓስካል ይደርሳል። በተጨማሪም ይህ ዓሣ ነባሪ ለረጅም ሰዓት ውኃ ውስጥ እንደጠለቀ መቆየት ይችላል። ለምሳሌ አንድ ዓሣ ነባሪ ለመተንፈስ ወደ ላይ ከመውጣቱ በፊት ለ3 ሰዓት ከ42 ደቂቃ ያህል ውኃ ውስጥ እንደቆየ ተመዝግቧል። አየር የሚተነፍሱ አጥቢ እንስሳት የሆኑት እነዚህ ዓሣ ነባሪዎች ከፍተኛ ግፊትና ትንሽ ኦክስጅን ባለበት ቦታ ይህን ያህል ረጅም ጊዜ መቆየት የሚችሉት እንዴት ነው?

 በውኃ ውስጥ እንደሚኖሩ ሌሎች አጥቢዎች ሁሉ የዓሣ ነባሪዎቹ የጎድን አጥንቶችም ወደ ውስጥ ይታጠፋሉ፤ እንዲሁም ሳንባዎቻቸው ይኮማተራሉ። በውኃ ውስጥ የሚኖሩ አጥቢዎች የልብ ምታቸው በከፍተኛ መጠን ሲቀንስና ደማቸው ጫፍ ጋ ወዳሉ የሰውነታቸው ክፍሎች ከመሄድ ይልቅ ወደ አንጎላቸው፣ ወደ ልባቸውና ወደ ጡንቻዎቻቸው ሲሄድ የሚጠቀሙት የኦክስጅን መጠን እንደሚቀንስ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።

 ከዚህም ሌላ፣ በውኃ ውስጥ የሚኖሩ አጥቢዎች ማዮግሎቢን በተባለ ፕሮቲን አማካኝነት በጡንቻዎቻቸው ውስጥ ኦክስጅን ያከማቻሉ። ውኃ ውስጥ ጠልቀው በሚገቡበት ጊዜ ይህ ፕሮቲን እንደ አስፈላጊነቱ ኦክስጅኑን ይለቃል። በእነዚህ ዓሣ ነባሪዎች ጡንቻ ውስጥ ያለው የማዮግሎቢን መጠን በሰዎችና በየብስ እንስሳት ጡንቻ ውስጥ ካለው መጠን በእጅጉ ይበልጣል።

 ያም ቢሆን አንድ ተመራማሪ ኩቪየርስ ቢክድ ዌል የተባሉትን ዓሣ ነባሪዎች በተመለከተ የሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፦ “የሚደርሱበት ጥልቀት ለማመን የሚከብድ ነው። እስካሁን ስለ እንስሳት አካል ካለን እውቀት አንጻር ከምንጠብቀውም ሆነ ልንረዳው ከምንችለው እጅግ የላቀ ችሎታ አላቸው።” ሳይንቲስቶች እነዚህ ዓሣ ነባሪዎች የሚጠልቁበትን መንገድ ይበልጥ መረዳት ይፈልጋሉ፤ ምክንያቱም ይህ እውቀት፣ ሐኪሞች የተኮማተረ ሳንባ ወይም ተመሳሳይ የጤና ችግር ያለባቸውን ሰዎች በተሻለ መንገድ እንዲያክሙ ሊረዳቸው ይችላል።

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? ኩቪየርስ ቢክድ ዌል ያለው ረጅም ርቀት የመጥለቅና በዚያ የመቆየት ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?