በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንዳማሩ ማርጀት ይቻላል?

እንዳማሩ ማርጀት ይቻላል?

ስለ እርጅና ስታስብ ምን ይሰማሃል? ስለ እርጅና ማሰብ ብዙዎችን በሐሳብ እንዲዋጡ፣ እንዲጨነቁና እንዲፈሩ ያደርጋቸዋል። እንዲህ የሚሰማቸው እርጅና አብዛኛውን ጊዜ ከቆዳ መሸብሸብ፣ አቅም ከማጣት፣ ነገሮችን ከመርሳትና ሥር ከሰደዱ በሽታዎች ጋር ስለሚያያዝ ነው።

ይሁን እንጂ ሰዎች በእርጅና ዘመናቸው የሚጋፈጧቸው ነገሮች በእጅጉ ይለያያሉ። አንዳንዶች ዕድሜያቸው ቢገፋም በአንጻራዊ ሁኔታ ጥሩ አካላዊና አእምሯዊ ጤንነት ይኖራቸዋል። ሌሎች ደግሞ በሕክምናው መስክ የተገኘው እድገት ካሉባቸው ሥር የሰደዱ በሽታዎች እንዲድኑ አሊያም በሽታቸውን እንዲቆጣጠሩ አስችሏቸዋል። በዚህም የተነሳ በአንዳንድ አገሮች የተሻለ ጤንነት ኖሯቸው ረጅም ዕድሜ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

ይሁን እንጂ ከእርጅና ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች አጋጠሟቸውም አላጋጠሟቸው፣ ብዙዎች እንዳማረባቸው ቢያረጁ ደስ ይላቸዋል። ታዲያ ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ለዚህ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አመለካከታችን እንዲሁም ከዚህ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ጋር ለመላመድ ያለን ፈቃደኝነትና ችሎታ ይገኙበታል። ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ቀላልና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች እንመልከት።

ልካችሁን የምታውቁ ሁኑ፦ “ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች።” (ምሳሌ 11:2) እዚህ ላይ ‘ልካቸውን የሚያውቁ’ የሚለው አገላለጽ እርጅና ያስከተለባቸውን የአቅም ውስንነት ለማስተባበል ወይም ችላ ለማለት ሳይሞክሩ ከዚህ ሁኔታ ጋር ተስማምተው የሚኖሩ በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ሊያመለክት ይችላል። በብራዚል የሚኖሩት የ93 ዓመቱ ቻርልስ እውነታውን በመቀበል “ረጅም ዕድሜ ከኖራችሁ ማርጀታችሁ አይቀርም። ጊዜን ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም” ብለዋል።

ይሁን እንጂ ልክን ማወቅ ሲባል “በቃ አርጅቻለሁ፤ ከእንግዲህ ምንም ማከናወን አልችልም” ብሎ እጅ መስጠት ማለት አይደለም። እንዲህ ያለው አመለካከት አንድን ሰው ወኔ ሊያሳጣው ይችላል። ምሳሌ 24:10 “በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል” ይላል። ከዚህ ይልቅ ልኩን የሚያውቅ ሰው አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ጥበብ እንዳለው ያሳያል።

በጣሊያን የሚኖሩት የ77 ዓመቱ ኮራዶ “ዳገት ላይ መኪና ስትነዳ ማርሽ ትቀይራለህ እንዲሁም ሞተሩ እንዳይጠፋብህ ትጠነቀቃለህ” በማለት የተናገሩት ነገር ጥበብ የሚንጸባረቅበት ነው። እውነት ነው፣ አንድ ሰው እያረጀ ሲሄድ ማስተካከያዎችን ማድረጉ አስፈላጊ ነው። ኮራዶና ባለቤታቸው የቤት ውስጥ ሥራዎቻቸውን ሲያከናውኑ ውለው በቀኑ መጨረሻ ላይ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የመዛል ስሜት ለማስወገድ በአንጻራዊ ሁኔታ ዘና ያለ ፕሮግራም በመከተል ሚዛናዊ አመለካከት አዳብረዋል። በብራዚል የሚኖሩት የ81 ዓመቷ ሜሪየንም ለእርጅና ምክንያታዊ የሆነ አመለካከት አላቸው። እንዲህ ብለዋል፦ “አቅሜን ማወቅ ተምሬአለሁ። ሥራዬን ስሠራ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በየመሃሉ አጫጭር እረፍት አደርጋለሁ። ተቀምጬ ወይም ጋደም ብዬ አነብባለሁ አሊያም ሙዚቃ አዳምጣለሁ። የአቅም ገደቤን መገንዘብ እንዲሁም እረፍት ሲያስፈልገኝ ማረፍን ተምሬአለሁ።”

ሚዛናዊ ሁኑ

ሚዛናዊ ሁኑ፦ “ሴቶች . . . በልከኝነትና በማስተዋል ተገቢ በሆነ ልብስ ራሳቸውን ያስውቡ።” (1 ጢሞቴዎስ 2:9) ‘ተገቢ የሆነ ልብስ’ የሚለው አገላለጽ ሚዛናዊነትንና ጥሩ ምርጫን ያመለክታል። በካናዳ የሚኖሩት የ74 ዓመቷ ባርባራ እንዲህ ብለዋል፦ “ንጹሕና ሥርዓታማ ሆኜ መታየት እፈልጋለሁ። ‘እኔ እንደሆነ አርጅቻለሁ፣ ምንም መስዬ ብታይ አያሳስበኝም’ የሚል አመለካከት በመያዝ ‘ዝርክርክ’ ማለት አልፈልግም።” በብራዚል የሚኖሩት የ91 ዓመቷ ፈርን ደግሞ “ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ ለማድረግ አልፎ አልፎ አዳዲስ ልብሶችን እገዛለሁ” ብለዋል። በዕድሜ ስለገፉ ወንዶችስ ምን ማለት ይቻላል? “ንጹሕ ልብስ በመልበስ ዝንጥ ብዬ ለመታየት የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ” በማለት በብራዚል የሚኖሩት የ73 ዓመቱ አንቶኒዮ ይናገራሉ። የግል ንጽሕናን በተመለከተም “ገላዬን የምታጠበውና ጺሜን የምላጨው በየቀኑ ነው” ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ስለ ቁመናችሁ ከልክ በላይ አትጨነቁ፤ ይህ “ማስተዋል” የጎደላችሁ ሰዎች እንደሆናችሁ ያሳያል። በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩት የ69 ዓመቷ ቦኪም ስለ ልብሶች ሚዛናዊ አመለካከት እንዳላቸው ሲናገሩ “በዚህ ዕድሜዬ በወጣትነቴ እለብሳቸው ከነበሩት ልብሶች መካከል አንዳንዶቹን ብለብስ ተገቢ እንደማይሆን አውቃለሁ” ብለዋል።

አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ

አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ፦ “ጎስቋላ ሰው ዘመኑ ሁሉ አስከፊ ነው፤ ደስተኛ ልብ ያለው ሰው ግን ሁልጊዜ ግብዣ ላይ ያለ ያህል ነው።” (ምሳሌ 15:15) እያረጃችሁ ስትሄዱ የወጣትነት ብርታታችሁንና ከዚህ ቀደም ታከናውኗቸው የነበሩትን ነገሮች በማሰብ በአሉታዊ ስሜቶች ትዋጡ ይሆናል። እንዲህ ቢሰማችሁ አያስገርምም። ይሁንና በእነዚህ አሉታዊ ስሜቶች ላለመሸነፍ ጥረት አድርጉ። ያለፈውን ዘመን እያሰባችሁ መቆዘም ቀሪ ሕይወታችሁን ሊያጨልመውና አሁን ማድረግ የምትችሏቸውን ነገሮች እንዳታደርጉ ተስፋ ሊያስቆርጣችሁ ይችላል። በካናዳ የሚኖሩት የ79 ዓመቱ ጆሴፍ አዎንታዊ አመለካከት አላቸው፤ “ማከናወን የምችላቸውን ነገሮች በማድረግ ለመደሰት እንዲሁም ከዚህ በፊት እሠራቸው የነበሩትንና አሁን ግን ልሠራቸው የማልችላቸውን ነገሮች እያሰብኩ ላለማዘን ጥረት አደርጋለሁ” ብለዋል።

ማንበብና እውቀት መቅሰምም የአእምሮ አድማስህን በማስፋት ይበልጥ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖርህ ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም ማንበብም ሆነ አዳዲስ ነገሮችን መማር የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች በተቻለ መጠን ተጠቀምባቸው። በፊሊፒንስ የሚኖሩት የ74 ዓመቱ ኤርኔስቶ ወደ ቤተ መጻሕፍት እየሄዱ ትኩረታቸውን የሚስቡ መጻሕፍትን ይፈልጋሉ። እንዲህ ብለዋል፦ “አሁንም ቢሆን ልብ የሚያንጠለጥሉ ታሪኮችን ማንበብ የሚፈጥረውን ስሜት እንዲሁም በጽሑፍ በሰፈሩ ቃላት አማካኝነት ከቤቴ ራቅ ወዳለ ቦታ በሐሳብ መጓዝ የሚያስገኘውን ደስታ እወደዋለሁ።” በስዊድን የሚኖሩት የ75 ዓመቱ ሌናርት ተፈታታኝ ቢሆንም አዲስ ቋንቋ ተምረዋል።

ለጋስ ሁኑ

ለጋስ ሁኑ፦ “ለሰዎች ስጡ፤ እነሱም ይሰጧችኋል።” (ሉቃስ 6:38) ጊዜያችሁንና ጥሪታችሁን ለሌሎች የማካፈል ልማድ ይኑራችሁ። ይህም ጠቃሚ ነገር በማከናወን የሚገኘውን ደስታ እንድታጣጥሙ ያስችላችኋል። በብራዚል የሚኖሩት የ85 ዓመቷ ኦዘ አካላዊ የአቅም ገደብ ቢኖርባቸውም ሌሎችን ለመርዳት ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ። እንዲህ ብለዋል፦ “ለታመሙ ወይም ተስፋ ለቆረጡ ወዳጆቼ ስልክ እደውልላቸዋለሁ እንዲሁም ደብዳቤ እጽፍላቸዋለሁ። አንዳንድ ጊዜ ትናንሽ ስጦታዎችን እልክላቸዋለሁ። በተጨማሪም ለታመሙ ወዳጆቼ ምግብ ማብሰል ወይም ጣፋጭ ነገር መሥራት ደስ ይለኛል።”

ለጋስ መሆን ሌሎች ለጋስ እንዲሆኑ ያነሳሳል። በስዊድን የሚኖሩት የ66 ዓመቱ ያን “ለሌሎች ፍቅር ስታሳዩ እነሱም ፍቅር ያሳዩአችኋል” ብለዋል። አዎ፣ ለጋስ የሆነ ሰው ሞቅ ያለ መንፈስ ያለው ሲሆን ሌሎችንም ያደንቃል፤ ይህም ሌሎችን የሚያስደስት ባሕርይ ነው።

የወዳጅነት መንፈስ አሳዩ፦ “ራሱን የሚያገል ሰው ሁሉ የራስ ወዳድነት ምኞቱን ያሳድዳል፤ ጥበብንም ሁሉ ይቃወማል።” (ምሳሌ 18:1) ብቻችሁን መሆን የምትፈልጉባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ራሳችሁን አታግልሉ፤ እንዲሁም ከሰው አትራቁ። በናይጄሪያ የሚኖሩት የ72 ዓመቱ ኢኖሰንት ከጓደኞቻቸው ጋር መሆን ያስደስታቸዋል። “በማንኛውም የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ሰዎች ጋር ስሆን ደስ ይለኛል” ብለዋል። በስዊድን የሚኖሩት የ85 ዓመቱ በርዬ እንዲህ ይላሉ፦ “ከወጣቶች ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ጥረት አደርጋለሁ። የእነሱን ብርታት ስመለከት ቢያንስ በውስጤ እንደገና ወጣት እንደሆንኩ ይሰማኛል።” አልፎ አልፎ ጓደኞችህን ጋብዛቸው። በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩት የ72 ዓመቱ ሀንሲክ “እኔና ባለቤቴ በሁሉም የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ወዳጆቻችን ጋር አብረን ጊዜ ማሳለፍ ወይም እነሱን ራት መጋበዝ ደስ ይለናል” ብለዋል።

የወዳጅነት መንፈስ አሳዩ

የወዳጅነት መንፈስ የሚያሳዩ ሰዎች ተጫዋች ናቸው። ይሁን እንጂ ተጫዋች መሆን ሲባል ተናጋሪ መሆን ብቻ ሳይሆን ጥሩ አድማጭ መሆንንም ይጨምራል። ለሌሎች አሳቢነት አሳዩ። በሞዛምቢክ የሚኖሩት የ71 ዓመቷ ኢሊነ እንዲህ ብለዋል፦ “የወዳጅነት መንፈስ የማሳይ ከመሆኔም ሌላ ሌሎችን አከብራለሁ። ምን እንደሚያስቡና ምን እንደሚወዱ ለማወቅ ሲናገሩ አዳምጣለሁ።” በብራዚል የሚኖሩት የ73 ዓመቱ ዡዜ እንዲህ ይላሉ፦ “ሰዎች ከሚያዳምጧቸው ሰዎች ጋር ማለትም የሰውን ችግር እንደራሳቸው አድርገው ከሚመለከቱና አሳቢነት ከሚያሳዩ እንዲሁም አመስጋኝና ተጫዋች ከሆኑ ሰዎች ጋር መሆን ያስደስታቸዋል።”

ሐሳባችሁን በምትገልጹበት ጊዜ “ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው የተቀመመ” እንዲሆን ጥንቃቄ አድርጉ። (ቆላስይስ 4:6) አሳቢና የምታበረታቱ ሁኑ።

አመስጋኝ ሁኑ፦ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ።” (ቆላስይስ 3:15) ሌሎች ለሚሰጧችሁ እርዳታ አድናቆት አሳዩ። አመስጋኝ መሆን ጥሩ ግንኙነት ለመመሥረት ይረዳል። “እኔና ባለቤቴ በቅርቡ ቤት ቀይረን ነበር። ብዙ ወዳጆቻችን ሊረዱን መጥተው ነበር። ምስጋናችንን በቃላት መግለጽ አልቻልንም። እያንዳንዳቸውን ለማመስገን ካርዶች ላክንላቸው እንዲሁም እስካሁን ድረስ አንዳንዶቹን እንጋብዛቸዋለን” በማለት በካናዳ የሚኖሩት የ74 ዓመቷ ማሪፖል ተናግረዋል። በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩት የ76 ዓመቷ ጄወን በመኪና ወደ መንግሥት አዳራሽ ይዘዋቸው ስለሚሄዱ እጅግ አመስጋኝ ናቸው። እንዲህ ይላሉ፦ “ለተደረገልኝ እርዳታ በጣም አመስጋኝ ከመሆኔ የተነሳ ለነዳጅ የሚሆን ጥቂት ገንዘብ ለመስጠት ጥረት አደርጋለሁ። አንዳንድ ጊዜም ከምስጋና መግለጫ ካርድ ጋር አነስተኛ ስጦታዎችን እሰጣለሁ።”

ከሁሉ በላይ በሕይወት በመኖራችሁ አመስጋኝ ሁኑ። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “በሕይወት ያለ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላል” በማለት ተናግሯል። (መክብብ 9:4) አዎ፣ ትክክለኛ አመለካከት ካዳበራችሁና ካላችሁበት ሁኔታ ጋር ራሳችሁን ለማስማማት ፈቃደኛ ከሆናችሁ እንዳማረባችሁ ማርጀት ትችላላችሁ።

አመስጋኝ ሁኑ