በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምንወደው ሰው ሲታመም

የምንወደው ሰው ሲታመም

“አባዬ ከሆስፒታል ሲወጣ ሐኪሙን ስለ አባዬ የደም ምርመራ ውጤት እንዲነግረን ጠየቅነው። ሐኪሙም የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ነገረን፤ ከዚያም የምርመራውን ውጤት በድጋሚ ተመለከተው። የሚገርመው ከምርመራው ውጤቶች መካከል ሁለቱ ችግር እንዳለ የሚጠቁሙ መሆናቸውን ተገነዘበ! ይቅርታ ከጠየቀን በኋላ አንድ ስፔሻሊስት ጠርቶ እንዲያየው አደረገ። አሁን አባዬ ተሽሎታል። ያን ቀን ስለ አባዬ የምርመራ ውጤት መጠየቃችን አስደስቶናል።”—መሪቤል

ሐኪም ጋ ከመሄዳችሁ በፊት የሕመም ምልክቶቹንና የሚወስደውን መድኃኒት ጻፍ

የሕክምና ቀጠሮዎችና ሆስፒታል ውስጥ የምናሳልፈው ጊዜ ውጥረት ሊፈጥሩብን ይችላሉ። የመሪቤል ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከጓደኛ ወይም ከዘመድ እንዲህ ያለ እርዳታ ማግኘት በጣም ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ ሕይወት አድን ሊሆን ይችላል። ታዲያ አንድ የምንወደው ሰው ሲታመም መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

ሐኪም ጋ ከመሄዳችሁ በፊት። ሕመምተኛው የሚታዩበትን የሕመም ምልክቶችና የሚወስዳቸው መድኃኒቶች ወይም ቪታሚኖች ካሉ በጽሑፍ እንዲያሰፍር እርዳው። በተጨማሪም ሐኪሙን ሊጠይቃቸው የሚፈልጋቸውን ጥያቄዎች በዝርዝር ጻፉ። ጓደኛህ የሚሰማውን ማንኛውንም ነገር ወይም በቤተሰቡ ውስጥ ተመሳሳይ ችግር የነበረበት ሰው ካለ እንዲያስታውስ እርዳው። ሐኪሙ እነዚህን ዝርዝር ጉዳዮች ያውቃቸዋል ወይም ይህን በተመለከተ ጥያቄ ያቀርብልናል ብለህ በማሰብ አትዘናጋ።

በትኩረት አዳምጥ፣ አክብሮት በተሞላበት መንገድ ጥያቄ ጠይቅ እንዲሁም ማስታወሻ ያዝ

ሐኪሙን በምታነጋግሩበት ወቅት። ሐኪሙ የሚናገረው ነገር በደንብ እንደገባችሁ እርግጠኛ ሁኑ። ጥያቄዎች ጠይቅ፤ ይሁን እንጂ ሐኪሙን በጥያቄ አታፋጥጠው። ሕመምተኛው የሚፈልጋቸውን ጥያቄዎች እንዲጠይቅና የሚሰማውን እንዲናገር ዕድል ስጠው። በትኩረት አዳምጥ፤ እንዲሁም ማስታወሻ ያዝ። ምን ዓይነት የሕክምና አማራጮች እንዳሉ ጠይቅ። አንዳንድ ጊዜ ሕመምተኛው ሌላ ሐኪም እንዲያማክር ሐሳብ ማቅረብህ ጥሩ ሊሆን ይችላል።

ሐኪሙ ስለሰጠው መመሪያና ስላዘዘው መድኃኒት ተወያዩ

ከሐኪሙ ዘንድ ስትወጡ። ስለ ቀጠሮው ቀን ከሕመምተኛው ጋር ተነጋገር። የታዘዘለትን መድኃኒት በትክክል ማግኘቱን አረጋግጥ። መድኃኒቱን በታዘዘለት መሠረት እንዲወስድና የጎንዮሽ ጉዳት ካስከተለበት ወዲያውኑ ለሐኪሙ እንዲናገር አበረታታው። ሕመምተኛው አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረው እንዲሁም ሕክምናውን በየጊዜው እየሄደ መከታተልን ጨምሮ የሚሰጡትን ሌሎች መመሪያዎች በሥራ ላይ እንዲያውል ምክር ስጠው። ስለ በሽታው ይበልጥ እንዲያውቅ እርዳው።

ሆስፒታል ውስጥ

ሁሉም ቅጾች በትክክል መሞላታቸውን አረጋግጥ

ተረጋጋ እንዲሁም ንቁ ሁን። አንድ ሰው ሆስፒታል ሲገባ ሊጨነቅና ምንም ማድረግ እንደማይችል ሊሰማው ይችላል። የአንተ መረጋጋትና ንቁ መሆን ሌሎች ዘና እንዲሉ ሊያደርግ አልፎ ተርፎም ስህተት ከመሥራት እንድትቆጠብ ሊያደርግህ ይችላል። አንድ ሰው ሆስፒታል ሲገባ የሚሞሉ ቅጾች በትክክል መሞላታቸውን አረጋግጥ። ሕመምተኛው ባገኘው መረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳለው መገንዘብ ይኖርብሃል። በጣም ከመታመሙ የተነሳ ውሳኔ ማድረግ ካልቻለ ቀደም ሲል በጽሑፍ ያሰፈረውን የግል ፍላጎቱን ማክበር አለብህ፤ በተጨማሪም የቅርብ ዘመዱ ወይም የሕክምና ወኪሉ የሚያደርጉትን ውሳኔ መቀበል ይኖርብሃል። *

ከሕመምተኛው ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለሕክምና ባለሙያው በአክብሮት ንገረው

ቅድሚያውን ውሰድ። የሕክምና ባለሙያዎችን ለማናገር አትፍራ። ጥሩ አለባበስ ያለህ መሆኑና መልካም ምግባር ማሳየትህ የሕክምና ባለሙያዎቹ ለሕመምተኛው ትኩረት እንዲሰጡትና ይበልጥ እንዲንከባከቡት ሊያደርግ ይችላል። በአብዛኞቹ ሆስፒታሎች ውስጥ አንድን ሕመምተኛ የተለያዩ ሐኪሞች ያዩታል። አዲስ ለሚመጣው የሕክምና ባለሙያ፣ ሌሎቹ የሕክምና ባለሙያዎች የተናገሩትን ነገር በመንገር ልትረዳው ትችላለህ። ሕመምተኛውን በደንብ ስለምታውቀው በሰውነቱ ወይም በአእምሮው ጤንነት ላይ የሆነ ለውጥ እንዳለ ካስተዋልክ ንገራቸው።

በሥራቸው ጣልቃ ሳትገባ ሕመምተኛውን ለመርዳት የምትችለውን ሁሉ አድርግ

አክብሮት አሳይ፤ እንዲሁም አመስጋኝ ሁን። የሆስፒታል ሠራተኞች ብዙውን ጊዜ የሥራ ጫና አለባቸው። እነሱ እንዲያደርጉልህ የምትፈልገውን ነገር አንተም አድርግላቸው። (ማቴዎስ 7:12) ሥልጠናና ልምድ እንዳላቸው አምነህ ተቀበል፤ እንዲሁም በችሎታቸው እንደምትተማመን አሳይ፤ ለሚያደርጉት ጥረትም አመስግናቸው። ይህም የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል።

ሁሉም ሰው ሊታመም ይችላል። ይሁንና አስቀድመህ ዕቅድ በማውጣትና ተግባራዊ እርዳታ በመስጠት ጓደኛህ ወይም ዘመድህ ያጋጠመውን አስቸጋሪ ሁኔታ በጥሩ መንገድ እንዲወጣ ልትረዳው ትችላለህ።—ምሳሌ 17:17

^ አን.8 የአንድን ሕመምተኛ መብትና ግዴታ አስመልክቶ የሚወጡ ሕጎች ከቦታ ቦታ ይለያያል። ሕመምተኛው ያሉት የሕክምና ሰነዶች የተሟሉና ወቅታዊ መሆናቸውን አረጋግጥ።