በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሕይወትህን መቆጣጠር ትችላለህ?

ተፈታታኙ ነገር፦ አሉታዊ ስሜቶች

ተፈታታኙ ነገር፦ አሉታዊ ስሜቶች

እንደ ሐዘን፣ ቁጣ ወይም ምሬት ያሉ ከባድ ስሜቶችን መቋቋም አዳጋች ሆኖብሃል? እነዚህ ስሜቶች ልታከናውናቸው የሚገቡ ነገሮችን ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ ወይም አቅም እንድታጣ አድርገውህ ይሆናል። ታዲያ ምን ልታደርግ ትችላለህ? *

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ፦ ዳዊት

ንጉሥ ዳዊት ጭንቀትንና ሐዘንን ጨምሮ የተለያዩ ስሜቶች ተፈራርቀውበታል። ታዲያ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲቀጥል የረዳው ምንድን ነው? ዳዊት ያስጨነቁትን ነገሮች ለአምላክ ይተው ነበር። (1 ሳሙኤል 24:12, 15) በተጨማሪም ስሜቶቹን በጽሑፍ ያሰፍር እንዲሁም የእምነት ሰው እንደመሆኑ መጠን አዘውትሮ ይጸልይ ነበር። *

ግሪጎሪ ያደረገው ነገር

በመክፈቻው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው ግሪጎሪ በመንፈስ ጭንቀት ይሠቃያል። “ነገሮችን በጣም አጋንኜ በመመልከት ከልክ በላይ እጨነቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ይህ ስሜት ከቁጥጥሬ ውጭ ሆኖ ነበር” ብሏል። ታዲያ ግሪጎሪ ሚዛኑን መጠበቅ የቻለው እንዴት ነው? “ባለቤቴና ጓደኞቼ በደግነት ያደረጉልኝን እርዳታ መቀበሌ ሚዛኔን ለመጠበቅ ረድቶኛል። በተጨማሪም የባለሙያ እርዳታ ያገኘሁ ሲሆን ስላለሁበት ሁኔታ ይበልጥ ለማወቅ ጥረት አደረግኩ። በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቼ ላይ አንዳንድ ለውጦች ሳደርግ ነገሮችን በቁጥጥሬ ሥር ማድረግ እንደቻልኩ ይሰማኝ ጀመር፤ አሁን ስሜቴ እኔን አይቆጣጠረኝም። እርግጥ አልፎ አልፎ የጭንቀት ስሜት ያድርብኛል፤ ያም ቢሆን ጭንቀት እንዲሰማኝ የሚያደርጉትን ሁኔታዎችና ይህን ስሜት መቋቋም የምችልበትን መንገድ በተመለከተ ከበፊቱ የተሻለ ግንዛቤ አለኝ።”

“ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኃኒት ነው።”—ምሳሌ 17:22

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ያደረብህን አሉታዊ ስሜት መቆጣጠር እንዳቃተህ ከተሰማህ የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ ሞክር፦

  • የሚሰሙህን ስሜቶች በማስታወሻህ ላይ አስፍር።

  • ስሜትህን ለቅርብ ዘመድህ ወይም ጓደኛህ በግልጽ ተናገር።

  • የሚሰሙህ ስሜቶች ትክክል ናቸው ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘እንዲህ ያለ አሉታዊ ስሜት እንዲያድርብኝ የሚያደርግ አሳማኝ ምክንያት አለኝ?’

  • እንደ ጭንቀት፣ ንዴት ወይም ቂም ያሉ አሉታዊ ስሜቶች እስክትዝል ድረስ እንዲቆጣጠሩህ አትፍቀድ። ከዚህ ይልቅ ኃይልህን ትርጉም ያለው ነገር ለማከናወን ተጠቀምበት። *

ዋናው ነጥብ፦ ብዙውን ጊዜ አሉታዊ ስሜት እንዲያድርብን የሚያደርገው ያጋጠመን ሁኔታ ሳይሆን ለተፈጠረው ሁኔታ ያለን አመለካከት ነው።

^ አን.3 አንዳንድ አሉታዊ ስሜቶች የባለሙያ እርዳታ በሚሹ የጤና ችግሮች ሳቢያ የሚከሰቱ ሊሆኑ ይችላሉ። ንቁ! አንድን የሕክምና ዓይነት ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም። እያንዳንዱ ግለሰብ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት፣ ያሉትን አማራጮች በጥንቃቄ መመዘን ይኖርበታል።

^ አን.5 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ መዝሙሮች ዳዊት በጽሑፍ ያሰፈራቸው የራሱ ጸሎቶች ናቸው።

^ አን.13 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሐምሌ 1, 2015 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ጭንቀትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ተከታታይ ርዕስ ተመልከት።