በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

የሸረሪት የማጣበቅ ችሎታ ሚስጥር

የሸረሪት የማጣበቅ ችሎታ ሚስጥር

በአሜሪካ በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ የምትኖረው ሸረሪት (ፓራስቲአቶዳ ቴፒዳሪዮረም) ግድግዳ ላይ ሲሆን በኃይል የሚጣበቅ፣ መሬት ላይ ሲሆን ደግሞ በቀላሉ ተላቅቆ ስፕሪንግ እንዳለው ወጥመድ በላዩ ላይ የሚሄዱትን ነፍሳት የሚይዝ ድር ታደራለች። ሸረሪቷ የምታመነጨው ያው ሙጫ በኃይል የሚያጣብቅ እና በቀላሉ የሚላቀቅ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

ስካፎልዲንግ ዲስክ

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ሸረሪቷ ስካፎልዲንግ ዲስክስ ተብለው የሚጠሩ በጣም የሚያጣብቁ ክሮች በመጎንጎን ድሩን በግድግዳ፣ በኮርኒስ ወይም እንዲህ ባለ ቦታ ላይ ታደራለች፤ ይህ ድር ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ እየበረሩ የሚመጡ ነፍሳት የሚፈጥሩትን ንዝረት መቋቋም ይችላል። በሌላ በኩል ግን ጋምፉት ዲስክስ በመባል የሚታወቁት መሬት ላይ የሚጣበቁ ክሮች ንድፋቸው ወይም አሠራራቸው ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ በአክሮን፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ከስካፎልዲንግ ዲስክስ አንጻር ሲታይ ሸረሪቷ ጋምፉት ዲስክስ የሚባሉትን ክሮች ከመሬት ጋር የምታያይዘው ጥቂት ቦታዎች ላይ ብቻ በመሆኑ ድሩ በቀላሉ ከመሬት ተላቅቆ በላዩ ላይ የሚሄዱትን ነፍሳት በድንገት ይይዛል።

ጋምፉት ዲስክ

የአክሮን ዩኒቨርሲቲ ያወጣው የዜና ዘገባ እንደገለጸው ይህን አስገራሚ የተፈጥሮ ሥራ የደረሱበት ተመራማሪዎች “ሸረሪቷ የምትጠቀምበትን አስደናቂ ንድፍ በመኮረጅ ሰው ሠራሽ ማጣበቂያ ለማምረት ጥረት ማድረግ ጀምረዋል።” የሳይንስ ሊቃውንት ፋሻ ለመሥራትም ሆነ የአጥንት መሰንጠቅን ለማከም የሚያገለግል ማጣበቂያ መፈልሰፍ እንደሚችሉ ተስፋ ያደርጋሉ።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ሸረሪቷ በኃይል የሚያጣብቅ እና በቀላሉ የሚላቀቅ ሙጫ የማመንጨት ችሎታዋ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?