በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሥነ ፍጥረት

ሥነ ፍጥረት

አንዳንድ የፍጥረት አማኞች እንደሚሉት አምላክ ምድርን የፈጠረው እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝማኔ ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ ነው?

“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።”—ዘፍጥረት 1:1

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ ምድርን ጨምሮ አጽናፈ ዓለምን የፈጠረው በውል ከማይታወቁ ዘመናት በፊት ይኸውም ዘፍጥረት 1:1 እንደሚለው “በመጀመሪያ” ነው። ዘመናዊው ሳይንስ አጽናፈ ዓለም መጀመሪያ አለው በሚለው ሐሳብ ይስማማል። የሳይንስ ሊቃውንት በቅርቡ እንደገመቱት አጽናፈ ዓለም ከተፈጠረ 14 ቢሊዮን ዓመት ገደማ ሆኖታል።

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ሥራ የተከናወነባቸው ስድስት ‘ቀናት’ እንደነበሩ ይገልጻል። ይሁንና እነዚህ ቀናት የ24 ሰዓት ርዝማኔ ያላቸው እንደሆኑ አይናገርም። (ዘፍጥረት 1:31) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ቀን” የሚለውን ቃል የተለያየ ርዝማኔ ያላቸውን ጊዜያት ለማመልከት ተጠቅሞበታል። ለምሳሌ ያህል፣ የፍጥረት ሥራ የተከናወነበትን ጊዜ በጠቅላላ ሲገልጽ “እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን ባደረገ ቀን” ይላል። (ዘፍጥረት 2:4 የ1954 ትርጉም) እነዚህ የፍጥረት ‘ቀናት’ ለብዙ ሺህ ዓመታት የዘለቁ ሊሆኑ ይችላሉ።—መዝሙር 90:4

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

አንዳንድ የፍጥረት አማኞች ያላቸው የተሳሳተ አስተሳሰብ መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ ገሸሽ እንድታደርግ ሊገፋፋህ ይችላል። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የያዘው ዘገባ እምነት የሚጣልበት ከሆነ በውስጡ ከሚገኘው “መልካም ጥበብ” ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት ትችላለህ።—ምሳሌ 3:21 የ1954 ትርጉም

አምላክ በምድር ላይ ሕያዋን ነገሮችን የፈጠረው በዝግመተ ለውጥ ተጠቅሞ ነው?

“እግዚአብሔር፣ ‘ምድር ሕያዋን ፍጡራንን እንደየወገናቸው . . . ታስገኝ’ አለ።”—ዘፍጥረት 1:24

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ በመጀመሪያ አንዲት ትንሽ ሕያው ነገር ፈጥሮ በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት በጣም ውስብስብ የሆኑ ሕያዋን ነገሮች እንዲገኙ አላደረገም። ከዚህ ይልቅ የተሟሉ የአካል ክፍሎች ያሏቸው እንስሳትንና ዕፅዋትን “እንደየወገናቸው” ከፈጠረ በኋላ በየወገናቸው እንዲባዙ አድርጓል። (ዘፍጥረት 1:11, 21, 24) ይህ ሂደት እስከ ዛሬ ድረስ የቀጠለ በመሆኑ ምድር አምላክ በመጀመሪያ በፈጠራቸው በእነዚያው ‘ወገኖች’ ተሞልታለች።—መዝሙር 89:11

መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአንድ ወገን ውስጥ ያሉ እንስሳት ሲዳቀሉ ወይም ከሚኖሩበት አካባቢ ጋር ለመላመድ ጥረት ሲያደርጉ በአፈጣጠራቸው ላይ ምን ያህል ለውጥ ሊከሰት እንደሚችል አይገልጽም። አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ እንደ ዝግመተ ለውጥ አድርገው የሚቆጥሩት ቢሆንም ይህ ሂደት ከወገኑ የተለየ አዲስ ፍጥረት አያስገኝም። በዘመናችን የተካሄዱ ምርምሮች መሠረታዊ የሆኑት የዕፅዋትና የእንስሳት ወገኖች ባለፉት በርካታ ዘመናት እምብዛም ለውጥ እንዳልታየባቸው መሥክረዋል።

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ስለሆኑት የፍጥረታት ‘ወገኖች’ የሚናገረው ሐሳብ ከሳይንስ አንጻር ትክክል መሆኑ ታሪክንና ትንቢትን ጨምሮ በሌሎች መስኮችም የሚታመን መረጃ እንደያዘ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።

አጽናፈ ዓለም የተሠራበት ንጥረ ነገር ከየት ተገኘ?

“እጆቼ ሰማያትን ዘርግተዋል።”—ኢሳይያስ 45:12

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ የማይነጥፍ ኃይል ወይም ጉልበት አለው። (ኢዮብ 37:23) የሳይንስ ሊቃውንት ኃይል ወደ ቁስ አካል ሊለወጥ እንደሚችል ስለተገነዘቡ ይህ ሐሳብ ትልቅ ትርጉም ያዘለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ከኀይሉ ታላቅነት” የተነሳ አጽናፈ ዓለምን እንዳስገኘ ይናገራል። (ኢሳይያስ 40:26) አምላክ የፈጠራቸውን ነገሮች ጠብቆ ለማቆየት ኃይሉን እንደሚጠቀም ቃል ገብቷል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን አስመልክቶ ሲናገር “[አምላክ] ከዘላለም እስከ ዘላለም አጸናቸው” ይላል።—መዝሙር 148:3-6

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

አለን ሰንዴጅ የተባሉ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለዋል፦ “ሳይንስ ከባድ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ የለውም። አንድ ነገር ከየት ሊመጣ ቻለ የሚል ጥያቄ ስታነሱ ጉዳዩ ከሳይንስ አቅም በላይ ይሆናል።” መጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረትን አመጣጥ በተመለከተ ከሳይንስ ጋር የሚጣጣም ማብራሪያ የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ ከሳይንስ አቅም በላይ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፤ ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ‘አምላክ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?’ የሚለው ይገኝበታል። *

^ አን.16 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት። ይህ መጽሐፍ www.pr418.com/am በተባለው ድረ ገጽ ላይም ይገኛል።