በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ፦ የመግዛት አባዜ ተጠናውቶናል?

ወጪህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?

ወጪህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?

በ2012 ይፋ በሆነ አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት ላይ፣ ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች መካከል ግማሽ የሚሆኑት የማያስፈልጋቸውን ዕቃ እንደሚገዙ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ደግሞ፣ ሰዎች የመግዛት አባዜ እንደተጠናወታቸው ይሰማቸዋል። በእርግጥም ጉዳዩ አሳሳቢ ነው። ብዙ ሸማቾች ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ በሚሄድ የዕዳ ማጥ ውስጥ ተዘፍቀዋል። ብዙ ነገሮችን መግዛት እርካታ ከማስገኘት ይልቅ የባሰ ጭንቀትና ብስጭት እንደሚያስከትል ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ታዲያ የመግዛት አባዜ የተጠናወተን ለምንድን ነው?

ሸማቾች ለአፍታ እንኳ ጋብ የማይል የማስታወቂያ ውርጅብኝ ይዥጎደጎድባቸዋል። የንግድ አስተዋዋቂዎች ዓላማ ምንድን ነው? ለማግኘት የምንመኛቸው ነገሮች፣ የግድ እንደሚያስፈልጉን ሆኖ እንዲሰማን ማድረግ ነው። የንግድ አስተዋዋቂዎች ሸማቾች በአብዛኛው በስሜት እንደሚነዱ ያውቃሉ። በመሆኑም የማስታወቂያዎቹ አቀራረብና ሸቀጦች የሚቀርቡበት መንገድ ሸማቾች ዕቃዎቹን ለመግዛት እንዲጓጉ የሚያደርግ ነው።

ሰዎች የማያስፈልጋቸውን ነገር የሚገዙት ለምንድን ነው? (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “በአብዛኛው ሸማቾች አንድ አዲስ ነገር ለመግዛት በሚነሱበት ጊዜ ሸቀጡን ሲፈልጉ፣ ሲያገኙና የራሳቸው ሲያደርጉ በዓይነ ሕሊናቸው ይታያቸዋል።” ሸማቾች ገበያ ሲወጡ በውስጣቸው ያለው የአድሬናሊን መጠን በጣም እንደሚጨምር አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የሽያጭ ባለሙያ የሆኑት ጂም ፑለር እንዲህ ብለዋል፦ “ሻጩ፣ ሸማቹ እንዲህ ያለ ስሜት እንዳለው ካስተዋለ የደንበኛውን ቀልብ ለመሳብ ጥረት ያደርጋል፤ ከዚያም የሸማቹ መጓጓትና ብዙም የማያቅማማ መሆኑ የፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ዕቃውን ገዝቶ እንዲሄድ ያግባባዋል።”

ታዲያ የብልሃተኛ አሻሻጮች ሰለባ ከመሆን ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? ስሜታዊ ሳትሆን ሰከን ባለ መንፈስ የንግድ አስተዋዋቂዎች የሚሰጡትን ተስፋ ከእውነታው ጋር አወዳድር።

 የሚሰጡህ ተስፋ፦ “ሕይወትህ ይሻሻላል”

የተሻለ ሕይወት መኖር የማይፈልግ ሰው የለም። የንግድ አስተዋዋቂዎች ትክክለኛውን ዕቃ ከገዛን ምኞታችን በሙሉ ማለትም ጥሩ ጤንነት፣ ከስጋትና ከጭንቀት ነፃ የሆነ ኑሮና ከሰዎች ጋር የተሻለ ግንኙነት እንደሚኖረን የሚገልጹ መልእክቶች ያዥጎደጉዱብናል።

እውነታው፦

ቁሳዊ ንብረታችን እየጨመረ መምጣቱ ሕይወታችንን ከማሻሻል ይልቅ ደስታችን እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርጋል። ተጨማሪ ቁሳዊ ነገር በገዛን ቁጥር ለእነዚህ ነገሮች አስፈላጊውን እንክብካቤ ለማድረግ ተጨማሪ ጊዜና ገንዘብ ያስፈልገናል። እንዲሁም ከዕዳ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ጭንቀት እየጨመረ ሊሄድ ብሎም ከቤተሰባችንና ከወዳጆቻችን ጋር የምናሳልፈው ጊዜ እየቀነሰ ሊመጣ ይችላል።

ቁሳዊ ንብረታችን እየጨመረ መምጣቱ ሕይወታችንን ከማሻሻል ይልቅ ደስታችን እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርጋል

ጠቃሚ መመሪያ፦ ‘አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ አይደለም።’ሉቃስ 12:15

የሚሰጡህ ተስፋ፦ “በሌሎች ዘንድ ያለህ ግምትና ክብር ይጨምራል”

አብዛኞቹ ሰዎች ዕቃ የሚገዙት የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ እንደሆነ አምነው መቀበል ይከብዳቸዋል። ይሁን እንጂ ጂም ፑለር እንዲህ ብለዋል፦ “ሰዎች ዕቃ ለመግዛት ከሚነሳሱባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ከወዳጆቻቸው፣ ከጎረቤቶቻቸው፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸውና ከዘመዶቻቸው ጋር ለመፎካከር ነው። አብዛኛዎቹ ማስታወቂያዎች የናጠጡ ሀብታሞች አንድን ምርት እየተጠቀሙበት ሲደሰቱ የሚያሳዩት ለዚህ ነው። እንዲህ ያሉ ማስታወቂያዎች ለሸማቾች የሚያስተላልፉት መልእክት “ይህ ሰው አንተ ልትሆን ትችላለህ!” የሚል ነው።

እውነታው፦

ማንነታችንን የምንለካው ራሳችንን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ከሆነ ዕድሜ ልካችንን እርካታ እንዳጣን እንኖራለን። ስንመኘው የነበረን አንድ ነገር በእጃችን ስናስገባው ሌላ ነገር መመኘት እንጀምራለን።

ጠቃሚ መመሪያ፦ “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም።”መክብብ 5:10

የሚሰጡህ ተስፋ፦ “ማንነትህን ማሳየት አለብህ”

አብረቅራቂ ዕቃዎች (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ “ማንነታችንን (ወይም መሆን የምንፈልገውን) ለሌሎች ከምናሳውቅባቸው የተለመዱ መንገዶች አንዱ ንብረት ማሳየት ነው።” የንግድ አስተዋዋቂዎች ይህን ስለሚያውቁ የንግድ አርማዎችን፣ በተለይ ውድ የሆኑ ዕቃዎችን የኑሮ ደረጃቸው ከፍ ካሉ ሰዎች ሕይወት ወይም ትልቅ ቦታ ከሚሰጠው አንድ ነገር ጋር ለማዛመድ ይጥራሉ።

አንተ ራስህን የምታየው እንዴት ነው? ሌሎችስ እንዴት እንዲያዩህ ትፈልጋለህ? ዘናጭ እንደሆንክ ወይም ጥሩ ቁመና እንዳለህ? መሆን የምትፈልገው ምንም ይሁን ምን የንግድ አስተዋዋቂዎች አንድ ጥሩ ስም ያለው ዕቃ ከገዛህ የምትፈልገው ዓይነት ሰው መሆን እንደምትችል ተስፋ ይሰጡሃል።

እውነታው፦

የምንገዛው ዕቃ ምንም ይሁን ምን እውነተኛ ማንነታችንን ሊለውጠው አይችልም፤ ወይም እንደ ሐቀኝነትና ታማኝነት ያሉ ድንቅ ባሕርያት ባለቤት ሊያደርገን አይችልም።

ጠቃሚ መመሪያ፦ “ውበታችሁ . . . የወርቅ ጌጣ ጌጦች በማድረግ ወይም በልብስ አይሁን፤ ከዚህ ይልቅ . . . የተሰወረ የልብ ሰው ይሁን።”1 ጴጥሮስ 3:3, 4