በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ንድፍ አውጪ አለው?

የሃምፕባክ ዓሣ ነባሪ መቅዘፊያ

የሃምፕባክ ዓሣ ነባሪ መቅዘፊያ

ለአካለ መጠን የደረሰ ሃምፕባክ ዓሣ ነባሪ መጠኑም ሆነ ክብደቱ ከአንድ የከተማ አውቶቡስ ይበልጣል። ያም ሆኖ ይህ ግዙፍ አጥቢ እንስሳ በባሕር ውስጥ ሲንቀሳቀስ በጣም ቀልጣፋ ነው። ለመሆኑ ሃምፕባክ ዓሣ ነባሪ እንደ ልብ መተጣጠፍ የቻለው እንዴት ነው? ሚስጥሩ በከፊል ያለው የመቅዘፊያው ጠርዝ ወጣ ገባ መሆኑ ላይ ነው።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አብዛኞቹ ዓሣ ነባሪዎችና ሌሎች የባሕር አጥቢ እንስሳት የመቅዘፊያቸው ፊተኛ ጠርዝ ልሙጥ ነው። የሃምፕባክ ዓሣ ነባሪ መቅዘፊያ ግን ይለያል። የመቅዘፊያው ፊተኛ ጠርዝ ወጣ ገባ ነው። ዓሣ ነባሪው በሚዋኝበት ጊዜ መቅዘፊያው ውኃውን ሰንጥቆ ሲያልፍ በርካታ አዙሪቶች ይፈጠራሉ። እንዲህ ያለው ነውጥ እንዲከሰት የሚያደርገው ውኃው በወጣ ገባዎቹ በኩል ማለፉ ነው። ይህ ሁኔታ ዓሣ ነባሪውን ወደ ላይ በመግፋት እንዲንሳፈፍ የሚያደርገው ግፊት እንዲጨምር ያደርጋል፤ ይህም ዓሣ ነባሪው ፍጥነቱን ሳይቀንስ መቅዘፊያውን ወደ ላይ ከፍ ለማድረግ ያስችለዋል። በተጨማሪም እነዚህ ወጣ ገባዎች ዓሣ ነባሪው መቅዘፊያውን ወደ ላይ በሚያነሳበት ጊዜ ወደ ኋላ የሚጎትተው ግፊት እንዲቀንስ ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ በጣም ረጅም የሆነውን መቅዘፊያ እንደልቡ ለማንቀሳቀስ ያስችለዋል፤ ምክንያቱም የዓሣ ነባሪው አንዱ መቅዘፊያ የቁመቱን አንድ ሦስተኛ ያክላል።

ተመራማሪዎች ይህን ንድፍ በመጠቀም ይበልጥ ውጤታማ የሆኑ የጀልባ መቅዘፊያዎች፣ በውኃና በንፋስ የሚሠሩ ኃይል ማመንጫ ሞተሮች እንዲሁም የሄሊኮፕተር መቅዘፊያዎች እየሠሩ ነው።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የሃምፕባክ ዓሣ ነባሪ መቅዘፊያ በዝግመተ ለውጥ የመጣ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?