በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወጣቶች ጥያቄ

ከትዳር ምን መጠበቅ እችላለሁ?​—ክፍል 1

ከትዳር ምን መጠበቅ እችላለሁ?​—ክፍል 1

“ከእሱ ጋር ስሆን በአየር ላይ የምሄድ ይመስለኛል! እስክንጋባ በጣም ቸኩያለሁ!”

“አንድም የሚያመሳስለን ነገር የለም። ባልና ሚስት ሳይሆን ደባሎች ነን ማለት ይቀላል! ብቻዬን የምኖር ያህል ይሰማኛል!”

የመጀመሪያውን ሐሳብ የተናገረችው ያላገባች ወጣት፣ ሁለተኛውን ሐሳብ የተናገረችው ደግሞ ያገባች ሴት እንደሆነች ሳትገምት አልቀረህም። ሁለቱንም ሐሳቦች የተናገረችው አንዲት ሴት እንደሆነች ስታውቅ ግን በጣም ትገረም ይሆናል።

ይህች ሴት ምን አጋጥሟት ይሆን? አንተስ አንድ ቀን ለማግባት የምታስብ ከሆነ ስታልመው በነበረው የፍቅር ሕይወት ፋንታ አስቸጋሪ ትዳር እንዳይገጥምህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

የሕይወት እውነታ፦ በትዳር ሕይወት ደስተኛ መሆንህ በአብዛኛው የተመካው ከትዳር በምትጠብቀው ነገር ላይ ነው።

ይህ ርዕስ እና በሚቀጥለው ወር ንቁ! ላይ የሚወጣው “የወጣቶች ጥያቄ” ከትዳር በምትጠብቀው ነገር ምክንያታዊ እንድትሆን ይረዱሃል።

ምክንያታዊ ሆነህ ከትዳር ልትጠብቃቸው የምትችላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል፦

  1. ጥቅም ታገኛለህ

  2. ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥምሃል

  3. ያልጠበቅኸው ነገር ያጋጥምሃል

እስቲ እነዚህን ነጥቦች ተራ በተራ እንመልከታቸው።

ጥቅም ታገኛለህ

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ትዳር ጥሩ ነገር እንደሆነ ይናገራል። (ምሳሌ 18:22) ከትዳር ልትጠብቃቸው የምትችላቸው አንዳንድ ጥቅሞች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።

ጓደኛ፦ አዳም ከተፈጠረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አምላክ “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለም” ብሎ እንደተናገረና ጓደኛ እንድትሆነው ሔዋንን እንደፈጠረለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 2:18) አምላክ ሁለቱንም የፈጠራቸው የተለያዩ ባሕርያት እንዲኖሯቸው ሆኖም እርስ በርስ መጣጣም እንዲችሉ አድርጎ ነው። በመሆኑም ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው የቅርብ ጓደኛ መሆን ይችላሉ።—ምሳሌ 5:18

አጋር፦ መጽሐፍ ቅዱስ “ለሥራቸው መልካም ውጤት ስለሚያገኙ፣ ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል” በማለት ይናገራል። (መክብብ 4:9) ይህ ጥቅስ ከትዳር ጋር በተያያዘም እንደሚሠራ ጥርጥር የለውም። ብሬንዳ * የምትባል በቅርቡ ያገባች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ትዳር፣ ተደጋግፎ የመሥራትና አንዳንዴም ትሑት ሆኖ የራስን ምርጫ የመተው ጉዳይ ነው።”

የፆታ ግንኙነት፦ መጽሐፍ ቅዱስ “ባል የሚስቱን የፆታ ፍላጎት ማሟላት ይገባዋል፤ ሚስትም ለባሏ እንደዚሁ ማድረግ አለባት” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 7:3 ኮመን ኢንግሊሽ ባይብል) ከጋብቻ በፊት የሚፈጸም የፆታ ግንኙነት ብዙውን ጊዜ ጭንቀትና ጸጸት እንደሚያስከትል የታወቀ ነው፤ ትዳር ከመሠረትክ ግን እንዲህ ያለ ስሜት ሳይሰማህ በፆታ ግንኙነት መደሰት ትችላለህ።—ምሳሌ 7:22, 23፤ 1 ቆሮንቶስ 7:8, 9

ዋናው ነጥብ፦ ትዳር ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ነው። (ያዕቆብ 1:17) እሱ ያወጣቸውን መመሪያዎች የምትከተል ከሆነ የትዳር ሕይወትህ አስደሳች እንደሚሆን መጠበቅ ትችላለህ።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ የሌሎችን መጥፎ ትዳር (ምናልባትም በቤተሰብህ ውስጥ) መመልከትህ ለትዳር ጥሩ አመለካከት እንዳይኖርህ አድርጎህ ይሆን? ከሆነ ልትመስላቸው የሚገቡ ጥሩ አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች የት ማግኘት ትችላለህ?

ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥምሃል

መጽሐፍ ቅዱስ ለትዳር ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንድትይዝ ይረዳሃል። (1 ቆሮንቶስ 7:28) በትዳር ውስጥ ሊያጋጥሙህ የሚችሉ አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል።

አለመግባባት፦ ሁለት ሰዎች፣ ፍጽምና የጎደላቸው በመሆናቸው ካልሆነ በቀር በሌላ በምንም መንገድ ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት ሊሆኑ አይችሉም። (ሮም 3:23) ስለዚህ አንድ ባልና ሚስት የቱንም ያህል የሚጣጣሙ ቢሆኑ አልፎ አልፎ አለመግባባት ያጋጥማቸዋል። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በኋላ ላይ የሚጸጽታቸውን ተገቢ ያልሆነ ነገር ሊናገሩ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በንግግሩ የማይሳሳት፣ እርሱ . . . ፍጹም ሰው ነው” ይላል። (ያዕቆብ 3:2 የ1980 ትርጉም) ስኬታማ ትዳር ያላቸው ሰዎች አለመግባባቶች ሲያጋጥሙ ጉዳዩን ተወያይተው እንዴት መፍታት እንደሚችሉ ይማራሉ እንጂ እውን ሊሆን የማይችል አስተሳሰብ በመያዝ ምንም ዓይነት አለመግባባት እንዳይፈጠር ለማድረግ አይሞክሩም።

የጠበቁት ሳይሆን ሲቀር፦ “ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ አንዲት ወጣት ‘ለእሷ የተፈጠረውን’ አቻዋን እንዳገባችና ከዚያ በኋላ በሰላምና በደስታ እንደኖሩ በሚገልጹ ታሪኮች የተሞሉ ናቸው” በማለት ካረን የተባለች ወጣት ተናግራለች። በመሆኑም የትዳር ጓደኛሞች ትዳራቸው በመገናኛ ብዙኃን እንዳዩት ሳይሆን ሲቀር ግራ ሊጋቡ ይችላሉ። በዚያ ላይ ደግሞ ሁለቱም ተጋቢዎች ከጋብቻቸው በኋላ ቀድሞ የማያውቋቸውን ጉድለቶችና እንግዳ የሆኑ ጠባዮች በትዳር ጓደኛቸው ላይ መመልከታቸው አይቀርም። በዚህ ወቅት መፍትሔው፣ የጠበቁት ሳይሆን ቢቀርም እንኳ እውነተኛ ፍቅር “ሁሉን ነገር በጽናት [እንደሚቋቋም]” ማስታወስ ነው።—1 ቆሮንቶስ 13:4, 7

ጭንቀት፦ መጽሐፍ ቅዱስ ያገቡ ሰዎች ‘ስለ ዓለም ነገር እንደሚጨነቁ’ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 7:33, 34) እንዲህ ዓይነቱ ጭንቀት የሚጠበቅ ሲሆን እንዲያውም ብዙ ጊዜ ተገቢ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የምታገኙትን ገቢ ከወጪያችሁ ጋር ማብቃቃት ተፈታታኝ ሊሆንባችሁ ይችላል። ባልና ሚስት የምግብ፣ የልብስ እንዲሁም የመጠለያ ወጪያቸውን ለመሸፈን ሁለቱም መሥራት ሊኖርባቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ለቤተሰባችሁ የሚያስፈልገውን ለማቅረብ ሁለታችሁም ተደጋግፋችሁ የምትሠሩ ከሆነ ሊሳካላችሁ ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 5:8

ዋናው ነጥብ፦ መጠናናትን ወላንዶ (ካይት) በማብረር ብንመስለው ትዳር መያዝ አውሮፕላን ከማብረር ጋር ይመሳሰላል። ትዳር ከመሠረታችሁ በኋላ የሚያጋጥማችሁን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመወጣት የበለጠ ብልሃት እንደሚያስፈልጋችሁና ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባችሁ ግልጽ ነው፤ ያም ቢሆን ሊሳካላችሁ ይችላል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ከወላጆችህ እንዲሁም ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር አለመግባባት ሲያጋጥምህ የምትፈታው እንዴት ነው? የጠበቅኸው ነገር ሳይሆን ቢቀር ነገሮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መመልከት ትችላለህ? የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥምህ የምትቋቋመው እንዴት ነው?

በሚቀጥለው እትም የሚወጣው “የወጣቶች ጥያቄ” . . . ያልጠበቅኸው ነገር ሊያጋጥምህ እንደሚችል በማሰብ ራስህን እንድታዘጋጅ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች የሚረዱህ እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

 

^ አን.17 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።