በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

እምነት

እምነት

አንዳንድ ሰዎች ሃይማኖተኛ እንደሆኑ ቢናገሩም “እምነት” ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ይከብዳቸዋል። ለመሆኑ እምነት ምንድን ነው? አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

እምነት ምንድን ነው?

አንዳንድ ሰዎች ምን ይላሉ?

ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት አንድ ሰው እምነት አለው የሚባለው አንድን ነገር ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ የሚቀበል ከሆነ ነው። “በአምላክ አምናለሁ” የሚልን አንድ ሃይማኖተኛ ሰው እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህ ሰው “በአምላክ የምታምነው ለምንድን ነው?” ተብሎ ቢጠየቅ “ከልጅነቴ ጀምሮ በአምላክ መኖር አምናለሁ” ወይም “ከልጅነቴ ጀምሮ እንዲህ ተብዬ ነው የተማርኩት” በማለት መልስ ይሰጥ ይሆናል። ይህ ሐሳብ አንድን ነገር በጭፍን በመቀበልና በእምነት መካከል እምብዛም ልዩነት የሌለ እንዲመስል ሊያደርግ ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“እምነት ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ነው፤ በተጨማሪም የምናምንበት ነገር በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።” (ዕብራውያን 11:1) አንድ ሰው አንድን ነገር በእርግጠኝነት ሊጠብቅ የሚችለው ይህን ለማድረግ የሚያበቃ አሳማኝ ምክንያት ካለው ነው። እንዲያውም “በእርግጠኝነት መጠበቅ” የሚለው ሐረግ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ከስሜት ወይም ከምኞት ያለፈ ትርጉም ያስተላልፋል። ስለዚህ እምነት በማስረጃ ተመሥርቶ ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ መሆንን ያመለክታል።

“[የአምላክ] የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።”ሮም 1:20

እምነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታልና።”—ዕብራውያን 11:6

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ብዙ ሰዎች በአምላክ የሚያምኑት እንዲህ ብለው ማመን እንዳለባቸው ስለተማሩ ነው። ‘ከልጅነቴ ጀምሮ እንዲህ ተብዬ ነው የተማርኩት’ ይሉ ይሆናል። ሆኖም አምላክ የሚፈልገው ሰዎች እሱ መኖሩንና አፍቃሪ አምላክ መሆኑን በራሳቸው አረጋግጠው እንዲያመልኩት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን በትክክል ማወቅ እንድንችል እሱን ከልብ መፈለግ እንዳለብን አጥብቆ የሚናገረው ለዚህ ነው።

“ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።”ያዕቆብ 4:8

እምነት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ “እምነት የሚገኘው ቃሉን ከመስማት ነው” ይላል። (ሮም 10:17) ስለዚህ በአምላክ ላይ እምነት ለማዳበር የሚረዳን የመጀመሪያው እርምጃ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሱ የሚያስተምረውን ነገር “መስማት” ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጨምሮ ለበርካታ አንገብጋቢ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ለማግኘት ይረዳሃል፦ አምላክ ማን ነው? አምላክ መኖሩን እንዴት እናውቃለን? አምላክ በእርግጥ ያስብልኛል? አምላክ ለወደፊቱ ጊዜ ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

አምላክ መኖሩን የሚያሳይ በርካታ ማስረጃ በዙሪያችን አለ

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንድትማር ሊረዱህ ዝግጁ ናቸው። jw.org የተባለው ድረ ገጻችን እንደሚገልጸው “የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር በጣም ያስደስታቸዋል፤ ይሁን እንጂ ማንንም ሰው የሃይማኖታቸው አባል እንዲሆን አይጫኑም። ከዚህ ይልቅ ሁሉም ሰው የሚያምንበትን ነገር የመምረጥ መብት እንዳለው ስለምንገነዘብ ለሰዎች የምናስተምረው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ትምህርት ብቻ ነው።”

ጉዳዩን ስናጠቃልለው፣ እምነትህ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል፤ ይህን ማስረጃ የምታገኘው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምታነበውን ነገር እውነተኝነት በራስህ ስታረጋግጥ ነው። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ “የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት” የተቀበሉትን በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምሳሌ መከተል ትችላለህ።—ሥራ 17:11

“የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው።”ዮሐንስ 17:3