በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የታሪክ መስኮት

ኢግናትዝ ዜመልቫይስ

ኢግናትዝ ዜመልቫይስ

ኢግናትዝ ዜመልቫይስ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ሰው ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም ሥራው በአሁኑ ጊዜ ላሉ በርካታ ቤተሰቦች ጥቅም አስገኝቷል። ኢግናትዝ ዜመልቫይስ የተወለደው ቡዳ (በአሁኗ ቡዳፔስት) ውስጥ ሲሆን በ1844 ከቪየና ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ዲግሪውን ተቀበለ። ዜመልቫይስ በ1846 በቪየና አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ በነበረው የማዋለጃ ክሊኒክ የአንድ ፕሮፌሰር ረዳት ሆኖ ሥራውን ሲጀምር አሰቃቂ ሁኔታ ገጠመው፤ በክሊኒኩ ውስጥ ከሚወልዱት ሴቶች መካከል 13 በመቶ የሚሆኑት የአራስነት ትኩሳት (ቻይልድቤድ ፊቨር) ተብሎ በሚጠራ በሽታ ሳቢያ ይሞቱ ነበር።

የዚህን በሽታ መንስኤ በተመለከተ የተለያዩ ንድፈ ሐሳቦች ቢቀርቡም ትክክለኛውን መንስኤ ማወቅ የቻለ አንድም ሰው አልነበረም። በተጨማሪም የሟቾቹን ቁጥር ለመቀነስ የተደረጉት ጥረቶች በሙሉ አልተሳኩም። ዜመልቫይስ አሠቃይቶ በሚገድለው በዚህ በሽታ የተያዙትን በርካታ ወላዶች በማየቱ ክፉኛ ስለተረበሸ የበሽታውን መንስኤ ለማግኘትና መከላከያ ለመፈለግ ቆርጦ ተነሳ።

ዜመልቫይስ የሚሠራበት ሆስፒታል ሁለት የተለያዩ የማዋለጃ ክሊኒኮች ነበሩት፤ የሚገርመው ነገር በመጀመሪያው ክሊኒክ የነበረው የሟቾች ቁጥር በሁለተኛው ክሊኒክ ከነበረው በጣም ከፍ ያለ ነው። በሁለቱ ክሊኒኮች መካከል የነበረው ብቸኛው ልዩነት በመጀመሪያው ክሊኒክ ውስጥ የሚማሩት የሕክምና ተማሪዎች ሲሆኑ በሁለተኛው ክሊኒክ ውስጥ የሚማሩት ግን አዋላጆች መሆናቸው ነው። ታዲያ በሟቾች ቁጥር ላይ ይህን ያህል ልዩነት የኖረው ለምንድን ነው? ዜመልቫይስ ለዚህ በሽታ መንስኤ ይሆናሉ ብሎ ባሰባቸው ነገሮች ላይ ምርምር ቢያደርግም የበሽታው ትክክለኛ መንስኤ አልተገኘም።

ዜመልቫይስ በ1847 መጀመሪያ ላይ አንድ ወሳኝ ፍንጭ አገኘ። የሥራ ባልደረባውና ወዳጁ የነበረው ጃኮብ ኮሌጽካ አስከሬን ሲመረምር ከደረሰበት ቁስል ጋር ተያይዞ በመጣበት የደም መመረዝ የተነሳ ሕይወቱ አለፈ። ዜመልቫይስ በኮሌጽካ አስከሬን ላይ የተደረገውን ምርመራ ውጤት ሲያነብ ለጓደኛው ሞት መንስኤ በሆነው ነገርና በአራስነት ትኩሳት ምክንያት ለሚመጣው ሞት መንስኤ በሆነው ነገር መካከል ተመሳሳይነት እንዳለ ተገነዘበ። በዚህም ምክንያት ዜመልቫይስ፣ በነፍሰ ጡሮች ላይ የአራስነት ትኩሳት የሚያስከትልባቸው ከአስከሬን የሚመጣ “መርዝ” ሊሆን እንደሚችል አሰበ። ለካስ ወደ ማዋለጃ ክፍል ከመሄዳቸው በፊት የአስከሬን ምርመራ የሚያደርጉ ሐኪሞችና የሕክምና ተማሪዎች፣ ሊወልዱ በተቃረቡ ነፍሰ ጡሮች ላይ የማህፀን ምርመራ በሚያደርጉበት ወይም እነሱን በሚያዋልዱበት ጊዜ ሳያስቡት በሽታውን ያስተላልፉ ነበር! በሁለተኛው ክሊኒክ ውስጥ የሚደርሰው ሞት በጣም አነስተኛ የሆነው ለአዋላጅነት የሚሠለጥኑት ተማሪዎች የአስከሬን ምርመራ ስለማያደርጉ ነበር።

ዜመልቫይስ ወዲያውኑ የሕክምና ባለሙያዎች እጃቸውን እንዲታጠቡ የሚያስገድድ መመሪያ ሰጠ፤ ይህም በነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ ምርመራ ከማድረጋቸው በፊት እጃቸውን ከጀርም ነፃ ለማድረግ ክሎሪን በተጨመረበት ኬሚካል መታጠብን ያካትታል። ውጤቱ አስደናቂ ነበር፦ የሟቾች ቁጥር በሚያዝያ ወር ላይ 18.27 በመቶ የነበረ ሲሆን በዓመቱ መጨረሻ ላይ ግን 0.19 ደረሰ።

“የእኔ ደንቦች ዓላማ የማዋለጃ ሆስፒታሎችን ከሰቆቃቸው መገላገልና የሚስትን ሕይወት ለባሏ እንዲሁም የእናትን ሕይወት ለልጇ ማቆየት ነው።”—ኢግናትዝ ዜመልቫይስ

በዜመልቫይስ ግኝት የተደሰተው ግን ሁሉም ሰው አልነበረም። የእሱ ግኝት አለቃው የአራስነት ትኩሳትን በተመለከተ ሲያምንባቸው የነበሩ ንድፈ ሐሳቦች ላይ ጥያቄ ያስነሳ ከመሆኑም ሌላ የዜመልቫይስ ውትወታ አለቃውን አበሳጨው። የኋላ ኋላ ዜመልቫይስ በቪየና የነበረውን ሥራ በማጣቱ ወደ ሀንጋሪ ተመለሰ። እዚያም ፔስት ውስጥ በሚገኘው በሴንት ሮከስ ሆስፒታል የማህፀን ምርመራ ክፍል ኃላፊ ሆነ፤ በዚያም እሱ ያቀረበው ሐሳብ በአራስነት ትኩሳት የሚሞቱትን እናቶች ቁጥር ከ1 በመቶ በታች እንዲሆን አድርጓል።

በ1861 ዜመልቫይስ በሕይወቱ ውስጥ ያከናወነውን ሥራ የያዘ ዘ ኮዝ፣ ኮንሴፕት ኤንድ ፕሮፊላክሲስ ኦቭ ቻይልድቤድ ፊቨር የሚል መጽሐፍ አሳተመ። የሚያሳዝነው የእሱ ግኝት እውቅና ያገኘው ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ነው። በዚህ መሃል ግን ሕይወታቸው ሊተርፍ ይችል የነበረ በርካታ እናቶች በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወታቸው አልፏል።

ዜመልቫይስ በእሱ ቁጥጥር ሥር ባሉ የሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚሠሩት የሕክምና ባለሙያዎች እጃቸውን እንዲታጠቡ የሚያስገድድ ደንብ አውጥቷል።—በሮበርት ቶም የተሳለ ሥዕል

በመጨረሻ ግን ዜመልቫይስ ቁስል እንዳይመረዝ የሚደረግበት ዘመናዊ ፀረ ተሕዋስያን ዘዴ አባት ተብለው ከሚጠሩት ሰዎች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል። የእሱ የምርምር ውጤት፣ በዓይን የማይታዩ ረቂቅ ነገሮች በሽታን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ለማረጋገጥ ረድቷል። በዚህም ምክንያት በሽታ የሚመጣው በጀርም እንደሆነ የሚገልጸው ንድፈ ሐሳብ ሲነሳ ስማቸው ከሚጠቀስ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፤ ይህ ንድፈ ሐሳብ “ለሕክምና ሳይንስና ሥራ እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ” አበርክቷል። የሚገርመው ነገር፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተተው የሙሴ ሕግ ከ3,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት አስከሬን እንዴት መያዝ እንዳለበት የሚገልጽ ጠቃሚ መመሪያ ሰጥቶ ነበር።