በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በስሜታችን መመራት ሁልጊዜ ያዋጣል?

ትክክል ወይስ ስህተት? ብዙዎች የሚመሩት በምንድን ነው?

ትክክል ወይስ ስህተት? ብዙዎች የሚመሩት በምንድን ነው?

ሁሉም ሰዎች ማለት ይቻላል አንዳንድ ድርጊቶች ትክክል እንደሆኑ፣ አንዳንድ ድርጊቶች ደግሞ ስህተት እንደሆኑ ይስማማሉ። ለምሳሌ ነፍስ ማጥፋት፣ አስገድዶ መድፈርና በልጆች ላይ ፆታዊ ጥቃት ማድረስ በብዙዎች ዘንድ የተወገዙ ድርጊቶች ናቸው። ፍትሐዊነት፣ ደግነትና ርኅራኄ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ባሕርያት ናቸው። ሆኖም ከሌሎች የሕይወት ዘርፎች ጋር በተያያዘ ብዙዎች ትክክል ወይም ስህተት የሚባል ነገር እንደሌለ ይሰማቸዋል። ከእነዚህ መካከል ከፆታ ግንኙነት፣ ከሐቀኝነት ወይም ከልጆች አስተዳደግ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች እንዲህ ካሉት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ምርጫ ቢያደርግ ምንም ችግር እንደሌለው ይሰማቸዋል። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ውሳኔ የሚያደርጉት በራሳቸው ስሜት ወይም በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ባላቸው ስሜት ላይ ተመሥርተው ነው። ይሁንና እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ያዋጣል?

በስሜታችን መመራት

ብዙውን ጊዜ በስሜታችን ማለትም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በሚነግረን ውስጣዊ ስሜት እንመራለን። ይህ ስሜት በተለምዶ ሕሊና ተብሎ ይጠራል። (ሮም 2:14, 15) ልጆችም እንኳ ተገቢ የሆነንና ያልሆነን ምግባር መለየት ይችላሉ፤ አልፎ ተርፎም የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል። በጊዜ ሂደት ሕሊናችን ከቤተሰቦቻችን፣ ከእኩዮቻችን፣ ከአስተማሪዎቻችን፣ ከማኅበረሰባችን፣ ከሃይማኖታችን እና ከባሕላችን በምንማራቸው እሴቶች እየተቀረጸ ይሄዳል። ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ሕሊናችን ያደረግነው ውሳኔ ከተማርናቸው እሴቶች ጋር የሚስማማ መሆን አለመሆኑን ይነግረናል።

ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የሚነግረን ውስጣዊ ስሜት ለሌሎች አዘኔታ፣ አመስጋኝነት፣ ፍትሕና ርኅራኄ እንድናሳይ ሊያነሳሳን ይችላል። ከዚህም ሌላ የምንወዳቸውን ሰዎች ሊጎዳ ወይም ለኀፍረትና ለጥፋተኝነት ስሜት ሊዳርገን የሚችል ነገር ከማድረግ እንድቆጠብ ሊያነሳሳን ይችላል።

በስሜታችን መመራት ሁልጊዜ ያዋጣል? ጌሪክ ወጣት ሳለ ‘የራሱን መሥፈርት ለማውጣት የሚያስችለው’ የሕይወት ጎዳና ይከተል ነበር። ይሁንና ለራሱ ትክክል መስሎ የታየውን ነገር ማድረጉ ጥሩ ውጤት እንዳላስገኘ ተመልክቷል። የተከተለው የሕይወት ጎዳና ያስከተለውን ውጤት ከጊዜ በኋላ ሲገልጽ “ሕይወቴ በሥነ ምግባር ብልግና፣ በዕፅና በአልኮል ሱሰኝነት እንዲሁም በዓመፅ ተሞላ” ብሏል።

በሌሎች ስሜት መመራት

ከራሳችን ስሜት ባለፈ ብዙውን ጊዜ ሌሎች ለውሳኔያችን በሚኖራቸው አመለካከት እንመራለን። ይህም ከእነሱ ተሞክሮና ጥበብ እንድንጠቀም ሊረዳን ይችላል። በቤተሰቦቻችን፣ በጓደኞቻችን ወይም በማኅበረሰቡ ዘንድ ትክክል ተደርጎ የሚቆጠረውን ነገር ማድረጋችን የእነሱን አክብሮት ለማትረፍ ይረዳናል።

በሌሎች ስሜት መመራት ሁልጊዜ ያዋጣል? ፕሪሲላ ወጣት ሳለች በእኩዮቿ ዘንድ ተቀባይነት የነበረውን አካሄድ በመከተል ገና ሳታገባ የፆታ ግንኙነት ትፈጽም ነበር። ይሁንና በሌሎች ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረጓ ደስታ እንዳላስገኘላት ተገነዘበች። እንዲህ ብላለች፦ “ብዙኃኑ የሚያደርገውን ነገር ማድረጌ ደስተኛ አላደረገኝም። አደገኛና ሞኝነት የሚንጸባረቅበት አካሄድ እንድከተል አድርጎኛል።”

የተሻለ አማራጭ ይኖር ይሆን?

ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በምንወስንበት ጊዜ የራሳችንም ሆነ የሌሎች ስሜት የሚጫወተው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። ሆኖም ይህ ብቻውን ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ላይረዳን ይችላል። አርቆ ማስተዋል የሚጎድለን ከሆነ በራሳችንም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት የሚያስከትል ውሳኔ ልናደርግ እንችላለን። (ምሳሌ 14:12) ከዚህም ሌላ እኛም ሆንን በዙሪያችን ያሉት ሰዎች የምንመራባቸው እሴቶች ዘላቂ ጥቅም እንደሚያስገኙልን ዋስትና የለንም። ምናልባትም እነዚህ እሴቶች በጊዜ ሂደት ሊለወጡ ይችላሉ። ደግሞም እንደምናውቀው፣ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ስህተት ተደርገው የሚቆጠሩ አንዳንድ ምግባሮች በአሁኑ ጊዜ ተቀባይነት ያላቸው ሆነዋል፤ ቀደም ሲል ተቀባይነት የነበራቸው አንዳንድ ምግባሮች ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ስህተት እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ።

በሌሎች ስሜት መመራት ሁልጊዜ ያዋጣል?

ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመወሰን የሚረዳን የተሻለ መመሪያ ማግኘት እንችል ይሆን? ልንከተለው የሚገባንን የሥነ ምግባር መሥፈርት የሚነግረንና ከዓመታት በኋላ ለጸጸት የማይዳርገን አስተማማኝ የመመሪያ ምንጭ ይኖራል?

ደስ የሚለው፣ በየትኛውም ቦታ ለሚኖሩ ሰዎች በሙሉ የሚሆን ጠቃሚ ምክር የሚሰጥ አስተማማኝ የመመሪያ ምንጭ አለ። የሚቀጥለው ርዕስ፣ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት የሚረዳ አስተማማኝ መመሪያ ማግኘት የምንችለው ከየት እንደሆነ ያብራራል።