በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከነቢያት ስለ አምላክ ምን እንማራለን?

ከነቢያት ስለ አምላክ ምን እንማራለን?

በጥንት ዘመን አምላክ በነቢያት አማካኝነት አስፈላጊ መልእክቶችን ለሰው ልጆች አስተላልፏል። እነዚህ መልእክቶች፣ የአምላክን በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ይጠቁሙናል። ከሦስት ታማኝ ነቢያት ምን እንደምንማር እስቲ እንመልከት።

አብርሃም

አምላክ አያዳላም፤ ሁሉም የሰው ልጆች በረከቱን እንዲያገኙ ይፈልጋል።

አምላክ ለነቢዩ አብርሃም “የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በአንተ አማካኝነት ይባረካሉ” ብሎ ቃል ገብቶለት ነበር።—ዘፍጥረት 12:3

ምን ትምህርት እናገኛለን? አምላክ በጣም ይወደናል፤ የምድርን ሕዝቦች ይኸውም እሱን የሚታዘዙ ወንዶችን፣ ሴቶችንና ልጆችን ሁሉ መባረክ ይፈልጋል።

ሙሴ

አምላክ መሐሪ ነው፤ እሱን ለማወቅ የሚጥሩ ሰዎችን ይባርካል።

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ፣ ለነቢዩ ሙሴ ታላላቅ ተአምራትን እንዲያከናውን ኃይል ሰጥቶታል። ያም ቢሆን ሙሴ “እንዳውቅህና በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንድኖር መንገድህን አሳውቀኝ” በማለት ጸልዮአል። (ዘፀአት 33:13) አምላክ፣ ሙሴ ባቀረበው ጸሎት ስለተደሰተ የእሱን መንገድና ባሕርያቱን ይበልጥ እንዲያውቅ በማድረግ ባርኮታል። ለምሳሌ፣ ፈጣሪ “መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነ አምላክ” መሆኑን ሙሴ ተገንዝቧል።—ዘፀአት 34:6, 7

ምን ትምህርት እናገኛለን? አምላክ እሱን ይበልጥ ለማወቅ የሚጥሩ ወንዶችን፣ ሴቶችንና ልጆችን መባረክ ይፈልጋል። እሱን እንዴት ማምለክ እንዳለብን በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ገልጾልናል፤ እንዲሁም ለእኛ ሞገሱን ማሳየትና እኛን መባረክ እንደሚፈልግ አሳውቆናል።

ኢየሱስ

ኢየሱስ ማንኛውም ዓይነት ሕመም ያለባቸውን ሰዎች በመፈወስ ርኅራኄ አሳይቷል

ስለ ኢየሱስ እንዲሁም እሱ ስላደረገውና ስላስተማረው ነገር መማራችን የአምላክን ዘላለማዊ በረከት ያስገኝልናል።

የአምላክ ቃል ስለ ኢየሱስ ሕይወትና ትምህርቶች ብዙ መረጃ ይዟል። አምላክ፣ በርካታ ታላላቅ ተአምራትን የመፈጸም ኃይል ለኢየሱስ ሰጥቶታል፤ ለምሳሌ ኢየሱስ ዓይነ ስውራንን፣ መስማት የተሳናቸውን እንዲሁም አንካሶችን ፈውሷል። የሞቱ ሰዎችን እንኳ አስነስቷል። ኢየሱስ ይህን ማድረጉ አምላክ ወደፊት ለሰው ልጆች ምን ዓይነት በረከቶች እንደሚያመጣ የሚያሳይ ነው። እነዚህን በረከቶች ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ነው።”—ዮሐንስ 17:3

ኢየሱስ ሩኅሩኅ፣ አዛኝና ደግ ነበር። “ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ” የሚል ሞቅ ያለ ግብዣ አቅርቦ ነበር፤ ወንዶችና ሴቶች፣ ወጣቶችና አረጋውያን ይህን ግብዣ ተቀብለው ወደ እሱ ጎርፈዋል። (ማቴዎስ 11:29) በእሱ ዘመን ሴቶች ዝቅ ተደርገው ይታዩ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ሴቶችን በደግነትና በአክብሮት ይዟቸዋል።

ምን ትምህርት እናገኛለን? ኢየሱስ ለሰዎች ጥልቅ ፍቅር አሳይቷል፤ አንዳችን ሌላውን እንዴት ልንይዝ እንደሚገባም ግሩም ምሳሌ ትቷል።

ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር አይደለም

ቅዱሳን መጻሕፍት “አንድ አምላክ . . . አለ” ይላሉ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የአምላክ መልእክተኛ መሆኑን ይገልጻሉ። (1 ቆሮንቶስ 8:6) ኢየሱስ፣ አምላክ ከእሱ እንደሚበልጥና ወደ ምድር እንደላከው በግልጽ ተናግሯል።—ዮሐንስ 11:41, 42፤ 14:28 *

^ አን.17 ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይበልጥ ለማወቅ እውነተኛ እምነት ደስታ ያስገኝልሃል የሚለውን ብሮሹር ክፍል 8 እና 9⁠ን ተመልከት፤ ብሮሹሩን www.pr418.com/am ላይ ማግኘት ትችላለህ።