በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው?

ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የኢየሱስ ተቃዋሚዎች፣ ‘ራሱን ከአምላክ ጋር እኩል አድርጓል’ በማለት ኢየሱስን ከስሰውታል። (ዮሐንስ 5:18፤ 10:30-33) ይሁን እንጂ፣ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እኩል እንደሆነ አንድም ጊዜ ተናግሮ አያውቅም። “አብ ከእኔ ይበልጣል” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 14:28

 የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች፣ ኢየሱስን ሁሉን ቻይ አምላክ አድርገው አልተመለከቱትም። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ አምላክ ‘ለኢየሱስ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ እንዳደረገው’ ሐዋርያው ጳውሎስ ተናግሯል። ታዲያ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ከሆነ አምላክ ‘የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አደረገው’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ አያምንም ነበር።—ፊልጵስዩስ 2:9