በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

“በምድር ወገብ መረግድ” የሚኖሩ መስማት የተሳናቸው ሰዎችን መርዳት

“በምድር ወገብ መረግድ” የሚኖሩ መስማት የተሳናቸው ሰዎችን መርዳት

ኢንዶኔዥያ “የምድር ወገብ መረግድ” (አረንጓዴ ቀለም ያለው የከበረ ድንጋይ) በመባል ትታወቃለች፤ ኢንዶኔዥያ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ይኖራሉ። የይሖዋ ምሥክሮች፣ እነዚህን ሰዎች ለመርዳት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ በርካታ ጽሑፎችንና የትምህርት ፕሮግራሞችን በኢንዶኔዥያ የምልክት ቋንቋ አዘጋጅተዋል። ያደረጉት ጥረትም የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።

በምልክት ቋንቋ የተደረገ ትልቅ ስብሰባ

በ2016 የይሖዋ ምሥክሮች በሰሜናዊ ሱማትራ በምትገኘው በሜዳን ውስጥ በኢንዶኔዥያ የምልክት ቋንቋ ትልቅ ስብሰባ አድርገው ነበር። በክልሉ የደህንነት ክፍል ውስጥ የሚሠሩ አንድ ባለሥልጣን በስብሰባው ላይ የተገኙ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች ይህን የትምህርት ፕሮግራም በነፃ በማዘጋጀታቸው ያላቸውን አድናቆትም ገልጸዋል። እንዲያውም የተመለከቱት ነገር ልባቸውን ስለነካው በምልክት ቋንቋ መዝሙር ሲዘመር እሳቸውም አብረው ለመዘመር ጥረት ሲያደርጉ ነበር።

የስብሰባው ቦታ ሥራ አስኪያጅ ስብሰባው “በተረጋጋና በተሳካ መንገድ” መካሄዱን ከገለጹ በኋላ “የይሖዋ ምሥክሮች፣ መስማት የተሳናቸው ጎረቤቶቻችንን የሚጠቅሙ እንዲህ ያሉ ፕሮግራሞችን ወደፊትም ማዘጋጀታቸውን እንደሚቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል። አክለውም የስብሰባ ቦታው ባለቤት ስብሰባው መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ተብሎ የሚደረግ መሆኑን ሲያውቁ “ለይሖዋ ምሥክሮች አንድ ጥሩ ነገር ማድረግ ፈለጉ። ስለዚህ በስብሰባው ለተገኙት [300 ሰዎች] በሙሉ ምሳ እንዳዘጋጅ አዘዙኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

በምልክት ቋንቋ የተዘጋጁት ቪዲዮዎች አድናቆት አትርፈዋል

የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማካፈል፣ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች በግለሰብ ደረጃም ያነጋግራሉ። ለሚያነጋግሯቸው ሰዎችም በኢንዶኔዥያ የምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ ቪዲዮዎችን ብዙውን ጊዜ ያሳያሉ፤ እነዚህ ቪዲዮዎች ሰዎች አስደሳችና አርኪ የሆነ ሕይወት እንዲኖራቸው ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው።

በማዕከላዊ ጃቫ ባለችው በሰማራንግ ከተማ፣ የኢንዶኔዥያ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ማኅበር የክልሉ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ማሄንድራ ተጉ ፕሪስዋንቶ “መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ለመርዳትና የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት የምታከናውኑት ሥራ በአድናቆት ሊታይ የሚገባው ነው” ብለዋል። አክለውም እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦ “ለምሳሌ፣ ደስተኛ ቤተሰብ ሊኖርህ ይችላል የተባለው ቪዲዮ በጣም ጠቃሚ ነው። በሥራችሁ ብትገፉ በጣም ደስ ይለናል።”

“ፍቅር ያሳያሉ”

ያንቲ የምትባል መስማት የተሳናት ሴት፣ የይሖዋ ምሥክሮች ባደረጉት ጥረት ልቧ በጥልቅ ተነክቷል። እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች መስማት በተሳናቸው ሰዎች ላይ ብዙውን ጊዜ ያሾፋሉ፤ የይሖዋ ምሥክሮች ግን ፍቅር ያሳያሉ። በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች፣ መስማት የማይችሉ ሰዎች ፈጣሪን እንዲያውቁና የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ለመርዳት ሲሉ የምልክት ቋንቋ ተምረዋል። ያደረጉት ልባዊ ጥረት በጥልቅ ነክቶኛል።”

ያንቲ ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር የሆነች ሲሆን አሁን በኢንዶኔዥያ የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎችን በሚያዘጋጀው የትርጉም ቡድን ትሠራለች። እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “የምናዘጋጃቸው ቪዲዮዎች፣ የምልክት ቋንቋ ችሎታቸው ውስን የሆኑ ሰዎች ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ይረዳሉ። ከዚህ በተጨማሪ ሰዎች ደስተኛና ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ያስተምራሉ።”