በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ፓስተሩ እሱ መስሏቸው ነበር

ፓስተሩ እሱ መስሏቸው ነበር

 ኦስማን ከባለቤቱና ከሴት ልጁ ጋር ሆኖ ቺሊ ውስጥ በሚገኝ አንድ የመቃብር ስፍራ አካባቢ የጽሑፍ ጋሪ ተጠቅሞ እየሰበከ ነበር። በድንገት፣ ለቀብር የመጡ ብዙ ሰዎች ሙዚቃ እያሰሙ ቦታው ደረሱ። ከሰዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ኦስማን ፓስተር ስለመሰላቸው ወደ እሱ መጥተው አቀፉትና “ፓስተር፣ በጊዜ ስለመጣህ እናመሰግናለን፤ እየጠበቅንህ ነበር” አሉት።

 ኦስማን እንደተሳሳቱ ሊነግራቸው ቢሞክርም ጫጫታ ስለነበር ሰዎቹ ሊሰሙት አልቻሉም። ለቀስተኞቹ ወደ መቃብሩ ከሄዱ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የተወሰኑ ሰዎች ተመልሰው በመምጣት “ፓስተር፣ መቃብሩ ጋር ሆነን እየጠበቅንህ ነው” አሉት።

 በቦታው የነበረው ጫጫታ ሲቆም፣ ኦስማን ራሱን አስተዋወቃቸውና እዚያ ቦታ የተገኘው ለምን እንደሆነ ነገራቸው። ሰዎቹም ፓስተራቸው ባለመምጣቱ ብስጭታቸውን ከገለጹ በኋላ “ወደ መቃብሩ መጥተህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያጽናና ሐሳብ ልታካፍለን ትችላለህ?” ብለው ጠየቁት። ኦስማንም በሐሳባቸው ተስማማ።

 ወደ መቃብሩ እየሄዱ ሳሉ ኦስማን ስለ ሟቿ አንዳንድ ጥያቄዎችን ከጠየቃቸው በኋላ የትኞቹን ጥቅሶች ሊያነብላቸው እንደሚችል አሰበ። መቃብር ቦታው ጋ ሲደርስ ለሕዝቡ ራሱን አስተዋወቀ፤ እንዲሁም የይሖዋ ምሥክር እንደሆነና ለሰዎች ወንጌልን እንደሚሰብክ ነገራቸው።

 ከዚያም ራእይ 21:3, 4ን እና ዮሐንስ 5:28, 29ን በመጥቀስ አምላክ ሰዎች እንዲሞቱ ዓላማው እንዳልነበር አብራራላቸው። እንዲሁም አምላክ በቅርቡ ሙታንን እንደሚያስነሳና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንደሚሰጣቸው ነገራቸው። ኦስማን ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ ብዙዎቹ ወደ እሱ መጥተው አቀፉትና “የይሖዋን ወንጌል” ስለነገራቸው አመሰገኑት። ከዚያም ኦስማን ወደ ጽሑፍ ጋሪው ተመለሰ።

 ከቀብር ሥርዓቱ በኋላ ከለቀስተኞቹ መካከል አንዳንዶቹ ወደ ጽሑፍ ጋሪው መጥተው ኦስማንን እና ቤተሰቡን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎችን ጠየቋቸው። ረጅም ውይይት ካደረጉ በኋላ በጋሪው ላይ የነበሩትን አብዛኞቹን ጽሑፎች ወሰዱ።