በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከእስረኞች ተምሯል

ከእስረኞች ተምሯል

 በ2011 አንድ ኤርትራዊ በስደት ወደ ኖርዌይ ሄደ። በዚያም የይሖዋ ምሥክሮች ሲያነጋግሩት አገሩ እያለ የይሖዋ ምሥክሮችን ያውቅ እንደነበር ነገራቸው። ወታደር ቤት በነበረበት ወቅት በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ የይሖዋ ምሥክሮች የውትድርና ሥልጠና እንዲወስዱ ከፍተኛ ጫና ቢደረግባቸውም ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ተመልክቶ ነበር።

 በኋላ ግን ሰውየው ራሱ እስር ቤት ገባ። በዚያም ጳውሎስ እያሱ፣ ነገደ ተኽለማርያም እና ይስሃቅ ሞገስ ከተባሉ ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ታሰረ፤ እነዚህ ሰዎች በእምነታቸው ምክንያት ከ1994 ጀምሮ በእስር ቆይተዋል።

 ይህ ሰው በእስር ቤት ቆይታው የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩትን ትምህርት በሕይወታቸው እንደሚተገብሩት በዓይኑ የማየት አጋጣሚ አገኘ። ሐቀኞች እንደሆኑ እንዲሁም ምግባቸውን እንኳ ለሌሎች እስረኞች እንደሚያካፍሉ አየ። አብረውት የታሰሩት የይሖዋ ምሥክሮች በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን አብረው እንደሚያጠኑና ሌሎችም አብረዋቸው እንዲያጠኑ እንደሚጋብዙ ተመለከተ። እምነታቸውን እንደካዱ የሚገልጽ ሰነድ ላይ ከፈረሙ ከእስር እንደሚለቀቁ ቢነገራቸውም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበሩም።

 ይህ ልበ ቅን የሆነ ሰው ይህን ሁሉ ነገር ሲያይ ልቡ በጥልቅ ተነካ። ከዚያም ኖርዌይ መኖር ከጀመረ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለ ጠንካራ እምነት ሊኖራቸው የቻለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ተነሳሳ። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮችን ሲያገኝ ወዲያውኑ ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት ጀመረ።

 መስከረም 2018 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በአሁኑ ወቅት ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ ከኤርትራና ከሱዳን የመጡ ሰዎችን ለማግኘት ብሎም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑና ጠንካራ እምነት እንዲያዳብሩ ለመርዳት ጥረት ያደርጋል።